1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮትዴቩዋር ምርጫ እና የተቃዋሚዎች ጥሪ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 7 2013

ሁለቱ ዋነኛ የኮትዴቩዋር ፕሬዚዳንት አላሳን ዋታራ ተቀናቃኞች እጎአ ከፊታችን ጥቅምት 31 ቀን ሊደረግ በታቀደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል። በቀድሞው ፕሬዚዳንት ሄንሪ ኮናን ባዴይ እና አፊ ንጉዌሳን የተጀመረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለሦስተኛ የስልጣን ዘመን ለመወዳደር ቆርጠው የተነሱትን አላሳን ዋታራን እየተገዳደረ ነው።

https://p.dw.com/p/3k4vK
Elfenbeinküste I Politik I Wahlboykott
ምስል Sia Kambou/AFP/Getty Images

የኮትዲቯር ምርጫ እና የፖለቲካ ትኩሳቱ

የኮትዴቩዋር ምርጫ እና የተቃዋሚዎች ጥሪ
ሁለቱ ዋነኛ የኮትዴቩዋር ፕሬዚዳንት አላሳን ዋታራ ተቀናቃኞች እጎአ ከፊታችን ጥቅምት 31 ቀን ሊደረግ በታቀደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል። በቀድሞው ፕሬዚዳንት ሄንሪ ኮናን ባዴይ እና ሌላኛው ተቀናቃኝ አፊ ንጉዌሳን የተጀመረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለሦስተኛ የስልጣን ዘመን ለመወዳደር ቆርጠው የተነሱትን አላሳን ዋታራን እየተገዳደረ ነው። ይጭብረበራል ከሚለው ስጋት ተነስተውም ተቀናቃኞቹ በምርጫው እንዳይሳተፉ ደጋፊዎቻቸው ከወዲሁ ግፊት እያደረጉ ነው። የፕሬዚዳንቱ ለሦስተኛ ጊዜ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ሆነው ለውድድር መቅረባቸው ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይጣረሳል ሲሉ ይከሳሉ። ባለፈው የነሐሴ ወር ፕሬዚዳንት አላሳን ዋታራ ለሦስተኛ ዙር ራሳቸውን ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ አድርገው ማቅረባቸው እንደተሰማ የተነሳው ብርቱ ተቃውሞ አልበረደም። በወቅቱ በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ከአስር በላይ ሰዎች እንዲገደሉ እና  በዓለም ከፍተኛ የካካዎ አምራቿ ሀገር አዲስ ፖለቲካዊ ውዝግብ እንድታስተናግድ አስገድዷታል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሎራን ባግቦ እጎአ ከ2010 ምርጫ በኋላ በአሁኑ ፕሬዚዳንት አላሳን ዋታራ የደረሰባቸውን ሽንፈት ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከ3,000 በላይ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ እና ከሀገሪቱም አልፎ በምዕራባዊ የአፍሪካ ሃገራት ኢኮኖሚ ጭምር ተጽዕኖ ማሳደር የቻለ የእርስ በእርስ ጦርነት አስነስቶ አልፏል። በሀገሪቱ ተመሳሳይ ነገር እንዳይፈጠር እንሻለን የሚሉት የኮትዴቩዋር ሕዝባዊ ግንባር ዕጩ አፊ እጎአ ከ1993 – 1999 ድረስ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ከነበሩት ከሄንሪ ኮናን ባዲዬ ጋር በተወያዩበት ወቅት ተከታዩን መልዕክት ለደጋፊዎቻቸው አስተላልፈዋል። 
« ፕሬዚዳንት ዋታራ በምርጫ ስም ሊያደርጉ የተዘጋጁበትን አዲስ መፈንቅለ መንግሥት ለመግታት በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ደጋፊዎቻችንን እንጋብዛለን።» አፊ አያይዘውም ከምርጫው ጋር በተገናኘ በሀገሪቱ የሚከናወኑ ተግባራትን ለመከላከል የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ተቃዋሚዎቹ ፕሬዚዳንት ዋታራ የሚመሩት ገዢ ፓርቲ ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ምርጫ ማዘጋጀቱ ብቻ ሳይሆን የምርጫውን ሂደትም አጭበርብሯል ብለው ይከሳሉ። ተቃዋሚዎቹ በጠሩት በዚህ ቀጣዩን ምርጫ ተግባራዊነት የማሳጣት እንቅስቃሴ ከተቃዋሚዎች ወገን አንድ ዕጩ ብቻ ሲቀሩ ሌሎች ራሳቸውን አግልለዋል። ገዢው ፓርቲ ግን ተቃዋሚዎች ራሳቸውን ቢያገልሉም አሁንም ምርጫው በተያዘለት ቀን እንደሚከናወን እያሳወቀ ነው። ፕሬዚዳንት ዋታራ እጎአ ተሻሽሎ የጸደቀው የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት የጊዜ ገደቡን አንስቶ የመወዳደር መብት እንዳጎናጸፋቸው ይከራከራሉ። ነገር ግን ቀደም ሲል በመጋቢት ወር በቀጣዩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደማይሳተፉ እና ይልቁኑ ጠቅላይ ሚንስትራቸው አማዱ ኩሊባሊ ዕጩ ፕሬዚዳንት ሆነው ለውድድር እንደሚቀርቡ አስታውቀው ነበር። ያ  ሳይሆን ቀርቶ እርሳቸውም ሆኑ ብዙዎች ተስፋ ጥለውባቸው የነበሩት አማዱ ኩሊባሊ ሞት ቀደማቸው እና ሀገሪቱን ወደሌላ ቀውስ ሊያስገባ ይችላል ተብሎ የተሰጋበት ፕሬዚዳንት አላሳን ዋታራ ራሳቸውን በዕጩነት እንዲያቀርቡ አድርጓቸዋል። በእርግጥ ምርጫው በተያዘለት ቀን እንዳይደረግ የሚከለክል ነገር ይፈጠር ይሆን ወይስ የፕሬዚዳንት አላሳን ዋታራ ምኞት እንዳሉት ምርጫው ይደረግ ይሆን? በሁለቱም ጫፍ የሚጠበቁ ነገሮች ለኮትዴቩዋር ምን ይዘው እንደሚመጡ ከወዲሁ መተንበይ ይከብዳል ።የዛሬን ላብቃ ። ከዝግጅቱ ጋር ታምራት ዲንሳ ነበርኩኝ ጤና ይስጥልኝ።

Elfenbeinküste Wahlkampf 2020 | Alassane Ouattara
ምስል Issouf Sanogo/AFP
Elfenbeinküste Wahlkampf 2020 | Kouadio Konan Bertin
ምስል Issouf Sanogo/AFP
Elfenbeinküste I Politik I Wahlboykott
ምስል Sia Kambou/AFP/Getty Images
Elfenbeinküste Wahlkampf 2020 | Kouadio Konan Bertin
ምስል Issouf Sanogo/AFP