1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮት ዲቯር ምርጫና ውጤቱ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 16 2008

የኮት ዲቯር ፕሬዝዳንት አላሳኔ ዋታራ ባለፈው እሁድ የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ መሆናቸው በይፋ ይነገራል ተብሎ እየተጠበቀ ነው ።ዋታራ የብዙሃኑን ድምጽ ማግኘታቸው ትናንት ማምሻም ተነግሮ ነበር ። ታዛቢዎች ምርጫውን ሰላማዊና ትክክለኛ ሲሉ አወድሰውታል

https://p.dw.com/p/1Guxm
Elfenbeinküste Wahl
ምስል picture-alliance/dpa/L. Koula

[No title]

ዋታራ የብዙሃኑን ድምጽ ማግኘታቸው ትናንት ማምሻም ተነግሮ ነበር ። በእጩ ተወዳዳሪነት ከቀረቡት 6 የዋታራ ተቀናቃኞች መካከል ቤርቲን ኮናን ኩአድዮ ትናንት ማምሻውን ለዋታራ የእንኳን ደስ ያለዎ መልዕክት አስተላልፈዋል ።
ያለፈው እሁዱ የኮትዲቯር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ ፕሬዝዳንት አላሳኔ ዋታራ እንደሚሆኑ አስቀድሞም በሰፊው ሲነገር ነበር ።ለዚህም ሁለት ምክንያቶች አሉ ትላለች የዶቼቬቬለዋ ዘጋቢ ካትሪን ጌንስለር ። ተቃዋሚዎች ባለፈው ነሐሴ ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸው አንደኛው ምክንያት ነው ። በምርጫው ለመካፈል የወሰኑት የተቀሩት ፓርቲዎች ደግሞ አንድ እጩ ይዘው ለመቅረብ አለመስማታቸው ሁለተኛው ምክንያት ነው እንደ ካትሪን ።ከዚህ ሌላ በየአካባቢው ድምፅ ለመስጠት የወጣው ሰው ቁጥር ማነስም ለዋታራ ማሸነፍ እንዲሁ አስተዋፅኦ ማድረጉ ተገልጿል ።የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ድምፅ ለመስጠት የወጣው ህዝብ ወደ 60 በመቶ እንደሚጠጋ ቢናገርም ተችዎች አልተቀበሉትም ።እነርሱ እንደሚሉት በርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ባዶ ነበሩ ማለት ይቻላል ። አንድ የሲቪል ማህበራት መድረክ ድምፅ ሊሰጥ የወጣውን ሕዝብ ቁጥር ወደ 53 በመቶ ዝቅ አድርጎታል ። ለፕሬዝዳንታዊው ውድድር ሁለት እጩዎችን ያቀረበው በምህጻሩ CNC የተባለው የተቃዋሚዎች ህብረት ደግሞ ድምፅ የሰጠው ህዝብ ከ20 በመቶ ያንሳል ባይ ነው ።ህብረቱ ድምፅ አሰጣጡን «አርአያነት የሌለው» ሲለዉ፤ ምርጫ ቦርድ የሚናገራቸውን ውጤቶች ደግሞ «የማይታመኑ» ነው የሚላቸው ።የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝዳንትና የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማህበረሰብ በምህፃሩ ኤኮዋስ የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ግን ይህን አይቀበሉም ።
«ወጥቼ ተዘዋውሬ አይቻለሁ ። እንዳየሁት በምርጫ የተሳተፈው በግምት ከ40 እስከ 45 በመቶ ይሆናል ። ይህ ግን በአንድ አካባቢ ብቻ ነበር ።በሌላ አካባቢ የተሰማሩት ደግሞ የተለየ ነገር ሊታዘቡ ይችላሉ ።»
ያም ቢባል ድምፅ ያልሰጠው ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ ነው ።የአይቮሪ ኮስት ህዝብ ቁጥር ወደ 23 ሚሊዮን ይጠጋል ።ለመምረጥ የተመዘገበው ግን 6.3 ሚሊዮኑ ብቻ ነው ።ከመካከላቸው የድምፅ መስጫ ካርዳቸውን ያልወሰዱ አሉ ። ድምፅቸውን ካልሰጡት መካከል ማርየም ኮኔ አንዷ ናቸው ።የ50 ዓመትዋ ማርየም የ4 ልጆች እናት ናቸው ። ከዛሬ አምስት አመቱ ምርጫ በኋላ በተነሳው ግርግር ምክንያት ትክክለኛ መጠሪያቸዋን መናገር አይፈልጉም ።
«ቤቴ እርፍ ብዮ ነው የዋልኩት ።በላሁ ከዚያም በጀርባዮ ተንጋልዮ ተኛሁ ።እኔ አልመረጥኩም ልጆቼንም ከቤት እንዳትወጡ አልኳቸው ።ችግር ቢፈጠር የምቋቋምበት ጉልበት የለኝም ።ለዚህ ነው ቤት ውስጥ የቆየሁት ።እስከ ወሩ መጨረሻም ከልጆቼ ጋር ሌላ ቦታ መቆየትን ነው የምመርጠው ።»
ቀጭንዋ ወይዘሮ የቀድሞው ፕሬዝዳንት የሎራ ግባግቦ ደጋፊ ናቸው ።አሁንም በዚህ አቋሟቸው እንደጸኑ ናቸው ።
«የግባግቦን ሃሳቦችን ስመለከት ሃገራችንን ይጠቅማል ብዮ አሰብኩ ። ለዚህ ነበር የኮት ዲቯር ዲሞክራቲክ ፓርቲ PDCI ን የተወኩት የግባግቦ ራዕይ ለወጣቱ ነበር ፤ለአፍሪቃም ጭምር እንጂ ።»
ሆኖም ግባግቦ በጎርጎሮሳዊው 2010 በተካሄደው ምርጫ ተሸነፉ ።ሽንፈታቸውን በፀጋ ባለመቀበላቸውም ለወራት በዘለቀ ብጥብጥ ከ3ሺህ በላይ የሚሆን ህዝብ ህይወት ጠፍቷል ።የአሁን ምርጫ ከዛሬ 5 ዓመቱ ምርጫ ጋር ሲነፃፀር ደም አላፋሰሰም ። ይህም የእስልምና ሃያማኖት ምሁሩና ምርጫውን የሚታዘበው የኮትዲቯር የሲቪል ማህበራት መድረክ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ኮኔን አስደስቷል ። ኮኔ የሚወክሉት 14 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ነው ።መድረኩ ምርጫውን ለሚታዘቡ 755 ሰዎች ስልጠና ሰጥቷል ።
«በአጠቃላይ በጣም ረክቻለሁ ። የምርጫው ቀን በጣም ሰላማዊ ነበር ። ስሜቱም የተጋጋለ አልነበረም ፤በምርጫ ጣቢያዎችም ረብሻ አልነበረም ።ሰዉ በነፃነት መርጦ ወደ ቤቱ ተመልሷል ።»
የኤኮዋስ የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ኦባሳንጆም ተመሳሳይ አስተያየት ነው የሰጡት ።የቀድሞው ፕሬዝዳንት የግባግቦ ደጋፊዎች ባሉባት የምዕራቡ ክፍል በምርጫው አንሳተፍም የሚሉ ወገኖች ነበሩ ። ሆኖም እዚያ የምርጫው ሂደት አልተጓጎለም እንደ ኦባሳንጆ
«በምዕራባዊ የሃገሪቱ ክፍልም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ምርጫ ተካሂዷል ።ምርጫውም ሰላማዊ ነፃና ተቀባይነት ያለው ነበር ።»

Präsidentschaftswahl in der Elfenbeinküste - Jugendliche
ምስል DW/K. Gänsler
Präsidentschaftswahl in der Elfenbeinküste - Alassane Ouattara
ምስል DW/K. Gänsler

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ