1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንሶ ባህላዊ ይዞታ በአለም የቅርሥ ማህደር

ሐሙስ፣ ሰኔ 23 2003

የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት UNESCO በአለም ዙርያ በ25 የተለያዩ አገራት የምገኙ ተፈጥሮዋዊ እና ባህላዊ ይዞታዎችን በአለም ቅርሥነት መዘገበ።

https://p.dw.com/p/RWkt

ድርጅቱ በአለም ቅርሥነት በማህደሩ ከያዛቸዉ ነገሮች መካከል ከአፍሪቃ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በሱዳን እና በሴኔጋል ያሉ የህዝብ ባህላዊ መገልገያዎች እና ተፈጥሮዋዊ ቦታዎች ይገኙበታል። የለቱ የባህል መድረክ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት ዘንድሮ በአለም ቅርሥነት የመዘገባቸዉን አንዳንድ ነገሮች በማንሳት በኢትዮጵያ በአለም ቅርሥነት የተመዘገበዉን የኮንሶን የመኖርያ አካባቢ ይቃኛል፣ ለጥንቅሩ አዜብ ታደሰ መልካም ቆይታ።

የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት UNESCO ከትናንት በስትያ የኮንሶ ህዝብ ባህላዊ የመኖርያን አካባቢ በተባበሩት መንግስታት ስር እንደተመዘገበ ይፋ አድርጎአል። ድርጅቱ ከሰኔ አስራ ሁለት እስከ ሰኔ ሃያ ሁለት አመታዊዉን እና ሰላሳ አምስተኛዉን ጉባኤ በዋና ጽፈት ቤቱ ፓሪስ ላይ ያደረገ ሲሆን ከአለም አገራት የተሰባሰቡ የባህልና ቅርጽ ጥበቃ ባለሞያዎችም ተካፋይ ነበሩ። ድርጅቱ ከአፍሪቃ ዘንድሮ በአለም ቅርሥነት የመዘገባቸዉ ነገሮች በአምስት አገራት የሚገኙ ሲሆኑ፣
፩.ከኢትዮጵያ፣ የ400 አመት እድሜ እንዳለዉ የተነገረለት የኮንሶ ማህበረሰብ ባህላዊ የመኖርያ ስፍራ
፪.ከኬንያ፣ በሞንባሳ የወደብ ከተማ ፎርት ጂሰስ በመባል የሚታወቀዉ 418 አመት እድሜ ያለዉ በፖርቱጋሎች የተገነባዉ ምሽግ እና በአስራ አረተኛዉ ክፍለ ዘመን በዘመናዊ መልክ እንደተገነባ የተነገረለት ሆ የተሰኝዉ የቬትናም ጥንታዊ ሥርወ-መንግስት ቤተ መንግስት
፫.ከሱዳን፣ ሰሜን ምዕራብ ሱዳን ሜሮይ ከተማ የሚገኙት ጥንታዊ ፒራሚድ እና የምርምር ቦታ
፬.ከሴኔጋል፣ 76,000 ሄክታር ክልል ያለዉ ሳሉም ዴልታ ብሄራዊ ፓርክ ይገኙበታል።

የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት UNESCO በኢትዮጵያ የ400 አመት እድሜ እንዳለዉ የተነገረለት የኮንሶ ማህበረሰብ የማምረቻ አካባቢ ባህላዊ የካብ ግንብ በአለም ቅርሥነት እንዲመገዘገብ ጥረት ከተጀመረ ብዙ አመታት እንደሆነዉ በኢትዮጵያ በባህል ቱሪዝም ሚኒስቴር በቅርሥና ጥበቃ ባለስልጣን የብሄራዊ ሙዚየም ዳሪክተር ወይዘሪት ማሚት ይልማ ገልጸዉልናል።

Fasil Schloss Gonder Äthiopien
ምስል DW/Azeb Tadesse Hahn

በዩኔስኮ የአለም አቀፍ ቅርሥዎች ማህደር ዉስጥ የተካተቱት የአገራችን ታሪካዊ እና ተፈጥሮዋዊ ይዞታዎች መካከል አንደኛዉ፣ በመካከለኛዉ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ባህል ነጸብራቅ የሆነችዉ የጎንደር ቤተ-መንግስት ግብረ ህንጻ፣ ሁለተኛዉ፣ የአክሱም ሃዉልት እና የአክሱም የስልጣኔ ቅሪቶች ሶስተኛዉ፣ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በወላይታ ሶዶ መንገድ ላይ የሚገኝዉ የጥያ ከተማ የተክል ድንጋይ፣ አራተኛዉ፣ የወሎዉ የላሊበላ የድንጋይ ዉቅር ህንጻ ቤተ- ክርስትያን፣ አምስተኛዉ፣ የብርቅዪዎቹ ዱር እንስሶች የዋልያ፣ የሰሜን ቀበሮ፣ የጭላዳ እንዲሁም ከሃምሳ በላይ ልዪ የእዋፋት ዝርያ የሚገኙበት የሰሜን ተራራ ብሄራዊ ጥበቃ ስፍራ፣ ስድስተኛዉ፣ በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የታችኛዉ አዋሽ ተፋሰስ የድንቅነሽ ማለት የሉሲ መገኛ፣ የሰዉ ዘር አመጣጥ የተገኝበት የተጠበቀ የምርምር ስፍራ፣
ሰባተኛዉ፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን መስተዳደር ቱርካና ሃይቅ አካባቢ የታችኛዉ ኦሞ ሸለቆ የአኦሞ ተፋሰስ በርካታ የእንስሳት እና የእጽዋት ቅሪት የተገኝበት የአለም ቅሪተ አካል ተመራማሪዎች የሚጎበኙት ስፍራ፣ ስምንተኛዉ፣ የሃረሩ የጀጎል ግንብና ታሪካዊ ስፍራዎች፣ እንዲሁም በዘጠኛነት ከሁለት ቀናት በፊት በአዲስ በዩኔስኮ ማህደር የተመዘገበዉ የኮንሶ የካብ ግንቦች፣ እና ባህላዊ ቅርሶች ናቸዉ።
በፓሪስ ትናንት የተጠናቀቀዉ ሰላሳ አምስተኛዉ የዩኔስኮ ጉባኤ ዘንድሮ በጀርመን የሚገኙ ሶስት ታሪካዊ እና ተፈጥሮዋዊ ይዞታዎችን እንዲሁ በማህደሩ አካቶአል።
የመጀመርያዉ፣ ፋጉስ ቬርክ Fagus Werk የተሰኝዉ በታችኛዉ ዛክሶኔ ግዛት በአልፊልድ ከተማ ዉስጥ እ.አ 1911 አ.ም ከድንጋይ ይልቅ በመስታወት የታነጸዉ ጥንታዊዉ ግን ዘመናዊዉ የፋብሪካ ህንጻ፥
ሁለተኛዉ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ኦስትርያን ጨምሮ ስምንት የአዉሮጳ አገሮችን የሚያካልለዉ ከአዉሮጳ እጅግ ትልቁ አልፐ የተራራ ሰንሰለት ላይ በጀርመን ክልል ዉስጥ የሚገኝዉ ጥንታዊ የእንጨት ቤቶች። ሶስተኛዉ በተለያዩ የጀርመን አምስት ክልሎች ዉስጥ ሰፊ ጋሻ መሪት ላይ የሚገኝዉ ወፍ ዘራሹ ጥቅጥቅ ያለ ደን ነዉ። አገሮች ድንቅ ታሪካዊ እና ተፈጥሮዋዊ ይዞታዎቻቸዉን በዪኔስኮ ማህደር ለማስመዝገብ ቀላል አለመሆኑን፣ ብሎም የተለያዩ መስፈርቶችን ማሟላት እንዳለባቸዉ የሚገልጹት ወይዘሪት ማሚት በኢትዮጵያ በጌዶ አካባቢ የሚገኘዉን የተክል ድንጋይ፣ የሶፎመር አካባቢ በአለም አቀፉ የቅርሥ ማህደር ለማስመዝገብ ጥረት ተደርጎ በ UNESCO ግምገማ ማህደር ዉስጥ እንደሚገኝ ጥቁመዋል።
ሰፊ ሃብት ያላት ኢትዮጵያችን ከያዘችዉ የተፈጥሮ እና የባህል ቅርጽ አኳያ በአለም ቅርሥነት ማስመዝገብ ያለባት ዘጠኝ ብቻ ይዞታዎችን አይደለም! የሚለዉን የባህል ሚኒስቴር ሃሳብ ሁላችንም የምንጋራ ይመስለናል። የሰዉ ዘር መገኛ ኢትዮጽያችን ድንቅነሽ ማለት ሉሲን የመጀመርያዋ የሰዉ ዘር በመሆንዋ ለሰላሳ አመታት ግድም የአለም ምሁራንን በምርምሩ ይዛ ቆይታ፣ አሁን በቅርቡ ደግሞ እዝያዉ አፍር አካባቢ ድንቅነሽን በአንድ ሚሊዮን አመት የምትበልጠዋ የአራት ነጥብ አራት ሚሊዮን እድሜን የተካነችዉ Ardipithecus ramidus በቁልምጫ ስሟ አርዲ፣ የሴት ቅሪተ አካል፣ አሁንም የሰዉ ዘር መፍለቅያዉ አፍሪቃ፣ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያን ጥንታዊነት አመላካች መሆኑ ግልጽ ነዉ። አድማጮች የለቱን መሰናዶ እዚህ ላይ አጠናቀቅን በኢትዮጵያ በባህል ቱሪዝም ሚኒስቴር በቅርሥና ጥበቃ ባለስልጣን የብሄራዊ ሙዚየም ዳሪክተር ወይዘሪት ማሚት ይልማን ለሰጡን ማብራርያ በዶቼ ቬለ ስም እናመሰግናለን። ሙሉዉን መሰናዶ ያድምጡ!

Deutschland Architektur Bauhaus Walter Gropius Fabrik wird UNESCO Weltkulturerbe
ፋጉስ ቬርክ እ.አ 1911 አ.ም በመስታወት የታነጸዉ ጥንታዊዉ የፋብሪካ ህንጻምስል dapd

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ