1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንጎ ምርጫ እና የአውሮፓ ህብረት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 19 1998

የኮንጎ የምርጫ ዘመቻ

https://p.dw.com/p/E0iM
ምስል AP
የፊታችን ዕሁድ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ለሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የፀጥታ ጥበቃ እገዛ ለማድረግ ቁጥራቸው ወደ አንድ ሺህ የሚጠጋ የአውሮፓ ህብረት ወታደሮች ዋና ከተማይቱ ኪንሻሳ ይገኛሉ ። ከአውሮፓ ህብረት አባል አገራት የተውጣጡት እነዚህ ወታደሮች ኮንጎ ከሚገኘው አስራ ሰባት ሺህ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አሰከባሪ ሀይል ጋር ነው የሚቀላቀሉት ። ሌሎች አንድ ሺህ ሁለት መቶ የሚሆኑ የህብረቱ ተጠባባቂ ሀይሎችም በጎረቤት አገር ጋቦን ሰፍረዋል ። ይሁንና የአውሮፓ ወታደራዊ ሀይል ወደሀገራቸው የመጣበትን ምክንያት የሚረዱ የኮንጎ ዜጎች ግን ጥቂቶች ናቸው ። አብዛኛዎቹም ወታደሮቹን በጥርጣሬ ነው የሚመለከቱዋቸው ።
ዕሁዱ ፕሬዝዳንታዊና የህዝብ ዕንደራሴዎች ምርጫ በሚካሄድባት ኮንጎ እአአ ከሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ስምንት እስከ ሁለት ሺህ ሶስት በተካሄደው የርስ በርስ ጦርነት ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አልቀዋል ። በዚህ ወቅት ህዝቡን የፈጀው ጦርነቱ ብቻ ሳይሆን ረሀብና በሽታም ነበር ። ምንም እንክዋን ጦርነቱ የዛሬ አራት ዓመት አበቃ ቢባልም ደም መፍሰሱ ግን አሁንም አልቆመም ። በተለይ ራቅ ያለው የሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል አሁንም አልተረጋጋም ። በዚህ አካባቢ አማፅያንና የከዱ ወታደሮች ሰላማዊ ሰዎችን ይገድላሉ ይዘርፋሉ ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዕርዳታ ሰራተኞች እንደሚናገሩት በኮንጎ ከየቀያቸው የተፈናቀሉት ዜጎች ቁጥር አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ይጠጋል ። እነዚህ ሁሉ ችግሮች መፍትሄ ባላገኙበት ሁኔታ ነው የዕሁዱ ምርጫ የሚካሄደው ። ለዚህ ምርጫ ማስፈፀሚያም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ከአራት መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው ያወጣው ። ዋናከተማይቱ ኪንሻሳ የሚገኙት እስከ አፍንጫቸው የታጠቁት የአውሮፓ ወታደሮች ግጭት እንዳይነሳ መጠበቅ ብቻ ነው ተልዕኮአቸው ። ከዚህ ውጭ በሌሎች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ መግባት አይችሉም ። ስለወታደሮቹ ተልዕኮ በቅርብ የሚያውቁ አንድ የህብረቱ ባለስልጣን እንደተናገሩት የአውሮፓ ወታደሮች በኪንሻ የአራት ወራት ቆይታቸው ተልዕኮዋቸውን የማስተዋወቅ ጠንካራ ዘመቻ ማድረግ ነው ዓላማቸው ።ወደ ሀገራቸው እስኪመለሱም ችግር ውስጥ እንዲገቡም አይፈለግም ። የብዙሀኑን ልብና ዐዕምሮ እንዲገዙ ነው የሚሞከረው ። የኮንጎን ህዝብ ብቻ ሳይሆን የአውሮፓን ህዝብም ማሳመን ከህዝብ ግንኙነቱ ተግባር ከፊሉ ስራ ነው ። የአውሮፓውያኑ ዓላማ ይህ ሲሆን የኮንጎ ዜጎች ግን የአውሮፓን ወታደሮች እንደፈለጉት አልተቀበሉዋቸውም ። በአሁኑ የሀገሪቱ ሁኔታ ከምርጫ ጋር የተገናኙ ብጥብጦች እየተነሱ ነው ። አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከምርጫው አግለዋል ። ጠንካራዋ የሀገሪቱ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም ከመስመር የወጡ ሁኔታዎች እስካልተስተካከሉ ድረስ የዕምነቱ ተከታዮች በምርጫው እንዳይሳተፉ ጥሪ አድርጋለች ። ትናንት የጀርመን ወታደሮች ወደሚገኙበት ወደ ኪንሻ አውሮፕላን ማረፊያ በሚወስደው መንገድ ላይ በፖሊስና በተቃዋሚ ወገን ደጋፊዎች መካከል ግጭት በተቀስቀሰበት ውቅት የጀርመን ሰራዊት አውቶብስ መስታወት ተሰባብሮዋል ። ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ የሰራዊቱን ተልዕኮ አደገኛነት ይጠቁማል ግጭቱ ሌሎች አካባቢዎችም ሊዛመት እንደሚችልም ያሰጋል።
ድምፅ
“በአጠቃላይ ሲታይ በየአካባቢው ጥቃቅን ግጭቶችና ዓመፆች የሚታዩበት ሁኔታ አለ ። የትናንቱም ግጭትም ከዚህ የተለየ አይደለም ። አንዳንዴ ፀጥ ያለ ነው ።አንዳንዴ ይቀሰቀሳል ።ወደሌሎች አካባቢዎችም ሊዛመት ይችላል ።”
ሲሉ ነበር በኪንሻሳ ለረዥም ጊዜ የኖሩት ጀርመናዊትዋ ኦስት ሀይንመር ገልፀዋል ።
አውሮፓውያን ገንዘባቸውን ላፈሰሱበት ምርጫ የሚፈልጉትን ውጤት ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ ነው ወደሀገራችን የመጡት የሚሉ የኮንጎ ዜጎች ጥቂት አይደሉም ። ከዚህ በተጨማሪም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ከውጭ ማዕድን አውጭ ኩባንያዎች ጋር የብዙ ሚሊዮን ዶላር ውል የተፈራረሙትን ካቢላን ነው የሚደግፈው ብለው ነው የሚያምኑት ። ጥርጣሬያቸውንም ይፋ እያወጡ ነው ። የአንድ ቤተክርስቲያን ቄስ ለመሆኑ እነዚህ ወታደሮች የህዝቡንና የምርጫውን ሂደት ፀጥታ ለማስጠበቅ ወይስ አንድ ግለሰብን ለመጠበቅ ነው ወደዚህች ሀገር የመጡት ሲሉ ነበር የጠየቁት ።እነዚህን የመሳሰሉ ፈተናዎች ከፊታቸው የተጋረጡባቸው ወታደሮቹ ህዝቡን ለመማረክ እየጣሩ ነው ። ለምሳሌ በቅርቡ ኪንሻሳ ውስጥ ወታደራዊ አቅማቸውን የሚያሳይ ትርዒት አቅርበው ነበር ። ይሁንና እስካሁን ወታደሮቹ ህዝቡን ለማቅረብ ያደረጉት ሙከራ ውጤት አላመጣም ። አንዳንዶች ደግሞ ጥያቄዎችን እያነሱ ነው ፣ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ሳይቀሩ ፤ ክሪስቶፍ ምቦሶ ከዕጩ ተወዳዳሪዎች አንዱ ናቸው ። በቅርቡ በቴሌቪዥን በተካሄደ ክርክር ላይ የአውሮፓ ወታደሮች የሚሰሩት አልገባኝም ? ምርጫው በጋቦን ነው የሚካሄደው ? ሲሉ ጠይቀው ነበር ። ወታደሮቹ ጋቦን መስፈራቸው ለምን አስፈለገ ከሚል መነሻ ።ምግቦ እንዳሉት ህግ አልባ በሆነው የሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ከተሞች በጎማ በቡካቩም ሆነ በኪሳንጋኒ አንድም የአውሮፓ ወታደር አይታይም ።
የኮንጎ ህዝብ በጥርጣሬ የሚያያቸው የአውሮፓ ወታደሮች የኮንጎ ቆይታ እስከ ህዳር ። በዕሁዱ ምርጫ ከዕጩ ተወዳዳሪዎቹ አንዳቸውም ከሀምሳ በመቶ በላይ ድምፅ ካላገኙ ሁለተኛ ዙር ምርጫ መደረጉ አይቀርም ። ይህ ምርጫ ደግሞ ከጥቅምት መጨረሻ በፊት አይሆንም ።ያኔ ደግሞ የህብረቱ ወታደሮች ተልዕኮ ወደ መገባደዱ ይቃረባል ። ምርጫው በታቀደው መሰረት ካልሄደ የህብረቱ ወታደሮችን የተልዕኮ ጊዜ ማራዘሙ እጅግ ውስብስብ እንደሚሆን ነው የሚገመተው ።