1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንጎ ተፋላሚዎች የሠላም ዉል

ማክሰኞ፣ ጥር 13 2000

የአናሳ ጎሳዎች በተለይ ጄኔራሉ የሚቆረቆሩለት ጎሳ መብት እስከየትነት አለየም።የተፈጥሮ ሐብት ክፍፍሉ እንዴትነት አልታወቀም።ሌላ ችግር።

https://p.dw.com/p/E0Zm
ጄኔራል ሎራ ንኩንዳ
ጄኔራል ሎራ ንኩንዳምስል picture-alliance/ dpa

የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ መንግሥት እና ጄኔራል ሎራ ንኩንዳ የሚመሩት አማፂ ቡድን ዛሬ የሰላም ዉል ይፈራረማሉ።ሥምምነቱ ለበርካታ አመታት በርስ በርስ ጦርነት ሥትታወቅ በቆየችዉ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን እንደመጨረሻዉ መሠረታዊ እርምጃ ታይቷል።ይሁንና ከበርካታ ድርድርና ሽምግልና በሕዋላ የሚፈመረዉ ሥምምነት ከዚሕ ቀደም ተደርገዉ እንደነበሩት ሥምምነቶች ሁሉ ይፈርስ ይሆናል የሚል ሥጋት አልተለየዉም። የዶቼ ቬለዉ ባልደባ አሌክሳንደር ገብል የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናክሮታል።


የኮንጎ የቅርብ ዘመን ፖለቲካ ምሥራቃዊ ክፍሏ ላይ ይዘዋረል።የኪንሻሳ መንግሥትና የአማፂያን ዉጊያ ካንዴም-ሁለቴም በላይ የተጫረዉ፣ የቱትሲ-ሁቱዎች ጠብ የተነሳዉ፣ የሩዋንዳ፣ ዩጋንዳ፣ ኮንጎ ጦር ፍልሚያ የተጀመረዉ በጥቅል ዉጤቱ በአስር-አመት አምስት ሚሊዮን ሕዝብ ያለቀበት ምሥቅልቅል የተነሳዉ ከሥራቅ ነዉ።ኮንጎዎች ከአመት እልቂት ፋታ፣ «ሠላም ወረደ-መንግሥት መረጥን» ባሉ ማግሥት እዚያዉ ምሥራቅ ኮንጎ ከሠፈረዉ ከቱትሲ ጎሳ የሚወለዱት ሎራ ንኩንዳ የጄኔራልነት ማዕረግ የጫኑበትን ጦር ትተዉ የሕዝብ መከላከያ ኮንግረስ- CNDP-በፈረንሳይኛ ምሕፃሩ-የሚል ቡድን መሠሥረታቸዉ ከጦርነት ያላገገመችዉን ሐገር ከሌላ ጦርነት-ነዉ የዶላት።


በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት የሥልት ድጋፍ በሚደረግለት የመንግሥት ጦርና በሩዋንዳ ይረዳል በሚባለዉ አማፂ ቡድን መካከል በተደረገዉ ዉጊያ የተገደለዉን ሰዉ ቁጥር «ብዙ ሺሕ» ከሚል ግምት ባለፍ በትክክል የቆጠረዉ የለም።ዉጊያን ፍራቻ ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለዉ በዱር ገደሉ የባዘነዉ ሕዝብ ግን ስምንት መቶ ሺሕ ደርሷል።-በመንፈቅ እድሜ።ዛሬ ሰሜን-ኪቩ ግዛት ዋና ከተማ ጎማ የሚፈረመዉ ዉል መላዋን ጎንጎን ዳግም ያብጣታል የሚል ሥጋት ያሳደረዉን ዉጊያ ለማስቆም እንደ ትልቅ እርምጃ ነዉ-የታየዉ።


ከተከታታይ ድርድር ከዚሕ ቀደም እየተፈረሙ ከፈረሱ ዉሎች በሕዋላ በሚፈረመዉ አዲስ ሥምምነት መሠረት መጀመሪያ ተኩስ ይቆማል።የሁለቱ ወገኖች ጦር የሠፈረበትን አካባቢ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራዊት ይረከባል።ለጋሽ ድርጅቶች ለተፈናቃዮች ርዳታ-ይሠጣሉ።ሥደተኛዉን ወደየቀየዉ ያሠፍራሉ።አምስት ሺሕ የሚሆኑት የጄኔራል ንኩንዳ ተዋጊዎች በመንግሥት ላይ በማመፃቸዉ አይወነጀሉም።ይሁንና ከመሐላቸዉ የጦር ወይም የዘር-ማጥፋት ወንጀል የፈፀመ ካለ ተጠያቂ ነዉ።የማይጠየቀዉ መደበኛዉን ጦር ይቀላቀላል።

ዉሉ ቀስ በቀስ ገቢር ከሆነ ባካባቢዉ ይሸመቁትን የቀድሞ የሩዋንዳ ሁቱ ሚሊሺያዎችና ሌሎች ሽፍቶችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ጥሩ መሠረት፤ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ጠንካራ መደላድል ይሆናል-ነዉ ተስፋዉ።ይሁንና ኮንጎ እስካሁን እንደምትታወቅበት የተኩስ አቁም የሚፀናበት የተኩስ አቁም ዉል የተፈረበት ቀለም እስኪደርቅ ነዉ-ይባላል።ያሁኑን ሥምምነት ከዚሕ አጣብቂኝ የሚከተዉ በርካታ ምክንያቶች አሉ።

የአማፂዉ ቡድን ተዋጊዎች እንጂ የአዛዣቸዉ የጄኔራል ንኩንዳ የወደፊት ሥልጣንና ሐላፊነት በግልፅ አይታወቅም።የአናሳ ጎሳዎች በተለይ ጄኔራሉ የሚቆረቆሩለት ጎሳ መብት እስከየትነት አለየም።የተፈጥሮ ሐብት ክፍፍሉ እንዴትነት አልታወቀም።ሌላ ችግር።