1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኹዋንታናሞ-እስርቤት፥ የኦባማ እቅድና ተቃዉሞዉ

ዓርብ፣ ግንቦት 14 2001

ተጠርጣሪዎቹ አሜሪካን ያሸብራሉ ከሚሉት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት አንዳዶቹን በስም ጠቅሰዉ የእንደራሴዎቹን አስተያየት በአሳማኝ ምክንያት ያልተደገፈ በማለት አጣጥለዉ ነቅፈዉታል

https://p.dw.com/p/HvMY
ምስል AP/DW

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ አሸባሪ ተጠርጣሪዎች የታሰሩበትን የኹዋንታኖሞ ደሴት-ኩባ ማጎሪያ ጣቢያን ለመዝጋት በያዙት አቋም እንደሚፀኑ አስታወቁ።ኦባማ ጣቢያዉን እንዲዘጋ ከዚሕ ቀደም ያሳለፉትን ዉሳኔ ገቢር ለማድረግ የጠየቁትን የሰማንያ ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሐገሪቱ የሕግ-መወሰኛ ምክር ቤት ባለፈዉ ማክሰኞ አግዶባቸዋል።ፕሬዝዳንቱ ትናንት ባደረጉት ንግግር እንዳሉት ግን እስካሁን ያልተለቀቁት ተጠርጣሪዎች ወደ ሌላ እስር ቤት መዛወር አለባቸዉ በሚለዉ አቋማቸዉ እንደፀኑ ነዉ።ተጠርጣሪዎቹ አስፈላጊ ከሆነ ዩናይትድ ስቴትስ ፍርድ ቤት መቅረብ አለባቸዉም ብለዋል።የንስ ቦርሸርስ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።


የዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ባለፈዉ ማክሰኞ የሰጠዉ ድምፅ፥ዝናቸዉ ላልቀዘቀዘዉ፥ ለሐገሪቱ ፕሬዝዳት የመጀመሪያዉ ታላቅ ፈተና ነዉ። የኹዋንታናሞን ማጎሪያ ጣቢያ ለማዘጋት የሚያስፈልገዉን ገንዘብ ካገዱት እንደራሴዎች አብዛኞቹ የራሳቸዉ የኦባማ ፓርቲ አባላት መሆናቸዉ ደግሞ-ለፕሬዝዳቱ አሳማሚ ፖለቲካዊ በትር አይነት የሆነዉ።

ኦባማ ሥልጣን በያዙ በሁለተኛ ቀናቸዉ ባፀደቁት ደንብ መሠረት ጣቢያዉ ሲዘጋ እስካሁን ያልተለቀቁት-ያልተፈረደባቸዉም ሁለት መቶ አርባ ተጠርጣሪዎች እንድም ወደ ሌሎች ሐገራት፥ ሁለትም ዩናትድ ስቴትስ ዉስጥ ወደሚገኙ መደበኛ እስር ቤቶች ይዛወራሉ፥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ይዳኛሉም።ይህን ለማስፈፀሚያ የተጠየቀዉን በጀት ያገዱት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እንደራሴዎች እንደሚሉት ግን ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት ከለቀቃቸዉ ወይም ከእስር ቤት ካመለጡ አሜሪካን ያሸብራሉ።

ኦባማ እንዲሕ አይነቱን የሩቅ ፍርሐት በፊትም-ትናንትም አልተቀበሉትም።እንደሚያዉም በተቃራኒዉ ፕሬዝዳቱ ትናንት እንዳሉት አሜሪካን የሚያሰጋዉ የማጎሪያ ጣቢያዉ መዘጋት ሳይሆን-አለመዘጋቱ ነዉ።
«በርግጥ የኹዋንታናሞ (ማጎሪያ ጣቢያ) መኖር ምናልባት ከተያዙት ይልቅ ብዙ አሸባሪዎችን በአለም ላይ ፈጥሯል።»
ተጠርጣሪዎቹ ገና ለገና ከማጎሪያ ጣቢያዉ ሌላ እስር ቤት ወይም ሌላ ሐገር ተዛዉረዉ፥ ከተዛወሩበት እስር ቤት ወይም ሐገር አምልጠዉ፥ወይም በፍር ቤት ተለቀዉ፥ የማሸበር ፍላጎት ኖራቸዉ፥አቅም ችሎታ አዳብረዉ አሜሪካ ተመልሰዉ አሜሪካንን ያሽብራሉ-የሚሉ ወገኖች ኦባማ ጭንቀት ፈጣሪዎች-ነዉ-ያሏቸዉ።

«እነዚሕን ችግሮች መፍታት እፈልጋለሁ።ከአሜሪካዉያን ጋር በጋራ መፍታት እፈልጋለሁ።በዚሕ ጉዳይ ላይ በተወያየን ቁጥር ፍራቻ የሚነዙ ወገኖች አስተያየት አይጠቅመንም።»
ኦባማ ሁለት-መቶ አርባዎቹን ተጠርጣሪዎች በአምስት ደረጃ ፈርጀዋቸዋል።መደበኛ ፍርድ ቤት መቅረብ የሚችሉ፥ ከዚሕ ቀደም በጦር ወንጀለኝነት ተከሰዉ ከአዋዛጋቢዉ የጦር ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረጉ፥ ነፃ ሊለቀቁ የሚችሉና ወደ ሌሎች ሐገራት የሚዛወሩ-ሐምሳ ተጠርጣሪዎች እያሉ።ከነዚሕ መሐል-በመረጃ እጥረት የማይፈርድባቸዉ ሊኖሩ እንደሚችሉም ፕሬዝዳቱ አልሸሸጉም።
«ከዚሕ ቀደም በፈፀሟቸዉ ወንጀሎች የማይፈረድባቸዉ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል።አንዳዶቹ የአሜሪካን ፀጥታ የሚያሰጉ ሆነዉ ሳለ በመረጃ ላይረጋገጥባቸዉ ይችላል።በአልቃዲ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ቦምብ የማፈንዳት ሥልጠና የተሰጣቸዉ፥ወይም በዉጊያ አዉድ የታሊባን ወታደሮች መርተዉ ያዋጉ፥ ለኦስማ ቢን ላደን ፍፁም ታማኝነታቸዉን የሚገልፁ ለዚሕ ምሳሌ ይሆናሉ።

USA Kuba Guantanamo Oberster Gerichtshof
ማጎሪያ ጣቢያዉምስል AP

በዚሕም ብሎ በዚያ ኹዋንታናሞን ከመዝጋት ሌላ የተሻለ አማራጭ የለም ባይ ናቸዉ ፕሬዝዳቱ።ተጠርጣሪዎቹ አሜሪካን ያሸብራሉ ከሚሉት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት አንዳዶቹን በስም ጠቅሰዉ የእንደራሴዎቹን አስተያየት በአሳማኝ ምክንያት ያልተደገፈ በማለት አጣጥለዉ ነቅፈዉታል። ይሁንና ጉዳዩ የአሜሪካ ፖለቲከኞችን እንዳከራከረ ነዉ።እስካሁን ድረስ ተጠርጣሪዎቹን ተቀብሎ ለማሰር ፍቀደኛ የሆነ የአሜሪካ ክፍለ-ግዛትም የለም።የኦባማ እቅድ ከተሳካ ኹዋንታናሞ እስከሚቀጥለዉ ጥር-ማብቂያ ድረስ መዘጋት አለበት።

የንስ ቦርሸርስ /ነጋሽ መሀመድ /ሂሩት መለሰ