1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወርቅ ሽያጭ ለዕዳ ቅነሳ

ሐሙስ፣ የካቲት 3 1997

የድሃ አገሮችን ዕዳ ሙሉ በሙሉ የመሰረዙ ሃሳብ እዳዉ እንዲቀነስ በሚቀሰቅሱት ወገኖች ጥረት በበለፀጉት አገራት ተቀባይነትን ቢያገኝም ተግባራዊነቱን የሚፈልገዉ ዉሳኔ ላይ ለመድረስ ጊዜ እንደሚፈጅ ተገለፀ።

https://p.dw.com/p/E0f0

ሙሉ በሙሉ ዕዳ የመሰረዙ ጉዳይ ለረጅም ጊዜያት ቅስቀሳ የተደረገበት ቢሆንም ሰባቱ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ አገራት ለመጀመሪያ ጊዜ በርዕሱ ለመወያየት በጎ ፈቃድ ያሳዩት ባለፈዉ እሁድ ባደረጉት ስብሰባ ነበር።
እዳ ስረዛዉ ለጠቅላላ ድሃ አገራት ከፓለቲካም ሆነ ከምጣኔ ሃብት ጋር ግንኙነት ሳይኖረዉ ለሁሉም የሚደረግ ሲሆን ተግባራዊ የሚሆንበት መንገድ ግን ገና አልተገለፀም።
በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘዉ የዕዳ ስረዛ አራማጅ ቡድን ጁቢሊ ቅንጅት አስተባባሪ ኒል ዋትኪንስ እንደሚሉት ምንም እንኳን አገራቱ ሃሳቡን ቢደግፉም በአሁኑ ወቅት ዕዳ የመሰረዙን እርምጃ መዉሰድ ከብዷቸዋል።
ፈታኙ ጉዳይ ከዚህ ከተድበሰበሰዉ የዕዳ መሰረዝ ስምምነት የዕዳ ጫና ያጎበጣቸዉን ድሃ አገራት በማይጎዳ መልኩ ወደተግባራዊ እርምጃ እንዴት እንሂድ ነዉ። ያንንም ነዉ እዉነተኛ ለዉጥ የምንለዉ ይላሉ አስተባባሪዉ።
የብሩታንያዉ የገንዘብ ሚኒስትር ጎርደን ብራዉን ከስብሰባቸዉ በኋላ እንደተናገሩት እነዚህ አገራት ለመጀመሪያ ጊዜ ነዉ የድሃ አገራትን እዳ ሙሉ በሙሉ ስለመሰረዝ የተወያዩት ያም ማለት ሃብታም አገራት የድሃ አገራትን ጩኸት መስማት ቻሉ።
ሆኖም በማደግላይ ያሉ አገራትና የድሃ አገራት ዕዳ እንዲሰረዝ የሚታገሉ ወገኖች አፋጣኝ ዉሳኔ ቢጠብቁም በቡድኑ መካከል እንዴት አድርገን እንርዳቸዉ በሚለዉ የመጀመሪያ እርምጃ ልዩነት ተፈጥሯል።
ዋነኟዉ ሃሳብ የአለም አቀፍ የገንዘብ የብድር ተቋም ያለዉን በርካታ የወርቅ ክምችት እንጠቀም በሚለዉ ዙሪያ የሚሽከረከር ሲሆን ከቡድኑ መካከል ከፊሉን ማሳመን ያልተቻለበት አዳጋች ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል።
በአንፃሩ የድሃ አገራት ዕዳ ይሰረዝ የሚለዉን ሃሳብ የሚያራምዱት የሲቪል ተቋማት የአለም ባንክና አለም አቀፍ የገንዘብ ብድር ተቋም ብድሩን በመሰረዝ በኤች አይቪና በሌሎች የተፈጥሮ አደጋዋች ለሚሰቃዩት አገራት ገንዘብ የመለገስ የተጠናከረ አቅም አላቸዉ ባይ ናቸዉ።
እነሱ ያቀረቡት ቀመር እንደሚያሳየዉ የአለም ባንክ ከተቀማጭ ሂሳቡ 10 ቢሊዮን ዶላር ለዕዳ ስረዛዉ ቢያዉልና እስከ 2020 ድረስ የሚተካዉ ተጨማሪ 7.5 ቢሊዮን ዶላር ለብድር ሊያዉል ይችላል።
በዚህ መሃል አለም አቀፍ የገንዘብ ብድር ተቋምም በበኩሉ ለዕዳ ስረዛዉ ካለዉ የወርቅ ክምችት ሽያጭ 35 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ይችላል።
የወርቅ ክምችቱ ሽያጭ ሊነሳ የቻለዉ የአለም የገንዘብ ብድር ተቋም ያለዉን ክምችትና የሽያጭ ገቢ አጣጥሎ በማቅረቡ ሲሆን የተደበቀ የወርቅ ሽያጭ ትርፍ የሚያሳይ ልዩነት በገበያዉያና ተቋሙ ባቀረበዉ ዋጋ ላይ ታይቷል።
የዕዳ ስረዛዉ ሃሳብ አራማጆች የመከራከሪያ ሃሳብ የሁለቱ ተቋማት አላማ ድህነትን መቀነስ ሆኖ ሳለ ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ ትርፍ በጀት በካዝናቸዉ አስቀምጠዉ በየቀኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምግብ በማጣት መሞት የለባቸዉም የሚል ነዉ።
በስብሰባዉ ወቅት የጁቢሊ ዩናይትድ ስቴትስ ቅንጅትና የለንደን ጁቢሊ ምርምር ከፍተኛ አማካሪ ሶኒ ካፑር ባደረጉት ንግግር የእዳ ስረዛዉ ዉሳኔ በተጓተተ ቁጥር በየቀኑ ከምንገምተዉ በላይ የሰዉ ህይወት የሚያስከፍል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለምሳሌ ዛምቢያ፤ ታንዛኒያና ኒካራጓ በአገራቸዉ ለጤናና ለትምህርት በጋራ ከሚያዉሉት በጀት በላይ ለዕዳ ክፍያ የሚያወጡት ይበልጣል።
የዕዳ ስረዛዉ ሙሉ በሙሉ በአለም የገንዘብ ብድር ተቋም ቢከናወን ድህነትን የመቀነሻ መንገድ ከመሆኑ በላይ ለእሲያ፤ ለአፍሪካና ለላቲን አሜሪካ የምጣኔ ሃብት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ባይ ናቸዉ።
ባለፈዉ አመትም ካፑር የአለም አቀፍ የገንዘብ ብድር ተቋም ከወርቅ ሽያጭ ለዕዳ ስረዛዉ የሚዉል 35 ቢሊዮን ዶላር እንዴት ማትረፍ እንደሚችል የሚያሳይ ጥናት በሰፊዉ አቅርበዉ ነበር።
ግፊቱ በመጠንከሩ የወርቅ ሽያጩን በተመለከተ ለመነጋገር የአለም የገንዘብ ብድር ተቋምና የአለም ባንክ በመጪዉ ሚያዚያ ዋሽንግተ ላይ ይሰበሰባሉ።
የሃሳቡ አራማጆችም የወርቅ ዋጋ ይለዋወጣል የሚለዉ ምክንያት አሳማኝ እንዳልሆነና የበለፀጉት አገራት የወርቅ ዋጋ እንጂ በእዳ የሚሰቃዩት አገራት ጉዳይ የማያስጨንቃቸዉ ከሆነ የተሳሳተ ምርጫ መያዛቸዉን እየተናገሩ ነዉ።
ምንም እንኳን በአገሪቱ በርካታ የሲቪል ተቋማት የዕዳ ስረዛዉን ሃሳብ ቢያራምዱም የወርቅ ሽያጩን በከፍተኛ ሁኔታ ከተቃወሙት የበለፀጉ አገራት ዋነኛዋ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።
የአለም የገንዘብ ብድር ተቋምም ሆነ የአለም ባንክ ከፍተኛ ባለድርሻ ዩናይትድ ስቴትስ ስትሆን ወርቅን የሚመለከት ማንኛዉም ሽያጭ በአገሪቱ ኮንግረስ መፅደቅ ይኖርበታል።
ሰባቱ በኢንዱስትሪ የበለፀጉት አገራት ገንዘብ በማበደር የታወቁት የአለም አቀፍ የገንዘብ ብድር ተቋምንና የአለም ባንክን በበላይ ቦርድነት የሚያስተዳድሩት ካናዳ፤ ጀርመን፤ ፈረንሳይ፤ ጣሊያን፤ ጃፓን፤ ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ ናቸዉ።