1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወባ በሽታን በሽንት ምርመራ

ረቡዕ፣ ግንቦት 3 2008

የወባ በሽታ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪቃ ገዳይ ከሆኑ በሽታዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ይኽ ገዳይ በሽታ ሰውነት ውስጥ መኖሩን በፍጥነት ለማወቅ ለመጀመሪያ ጊዜ የሽንት ናሙና ምርመራ አገልግሎት ላይ ውሏል። በአዲሱ ስልት ወባን በሽንት ናሙና ለመመርመር የጤና ባለሙያ አያስፈልግም።

https://p.dw.com/p/1IlIl
Mücke Stechmücke sticht Gene Sperrfrist bis 20 Uhr 22.4.2015
ምስል picture-alliance/dpa/Patrick Pleul

የወባ በሽታን በሽንት ምርመራ

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙ የናይጀሪያ ሣይንቲስቶች የወባ በሽታን ከሰውነት ውስጥ በቀላል ዘዴ መለየት የሚያስችል አዲስ መላ ዘይደው ብቅ ብለዋል። ሣይንቲስቱ እስካሁን ከተለመደው የወባ በሽታን በደም ምርመራ የማግኘት ስልት ባሻገር በሽታውን በሽንት ምርመራ ማወቅ የሚቻልበትን ስልት ነው የቀየሱት። ቀደም ሲል የወባ በሽታን ለመለየት ወደ ጤና ማዕከል በማቅናት በባለሙያ የደም ናሙና ምርመራ ማከናወን የግድ ያስፈልግ ነበር። አሁን በአፍሪቃውያኑ ተመራማሪዎች ጥረት እና ግኝት መሠረት የወባ በሽታን ማንኛውም ግለሰብ በቀላሉ ቤት ውስጥ በሽንት ናሙና መርምሮ ማወቅ ይችላል።

በናይጀሪያዋ የሌጎስ ከተማ የተለመደ አይነት የክሊኒክ ድባብ ነው የሚሰማው። እዚህም እዚያም የጤና ባለሙያዎች የወባ በሽታን በደም ናሙና ለመመርመር በመርፌ ክንዶቻቸውን ሲወጓቸው በሚፈጠረው የኅመም ስቃይ ህፃናቱ ያለቅሳሉ። ሆኖም አዲሱ የምርመራ ስልት የነዚህን ህጻናት ስቃይ እና ለቅሶ የሚያስቆም ነው።

በአነስተኛ የሽንት መቀበያ ውስጥ መመርመሪያዋ ላይ የሽንት ጠብታን በማኖር የወባ በሽታ መኖር አለመኖሩን ማወቅ ይቻላል። የመመርሪያ ቁራጭዋ (strip) ላይ መስመር ከታየ ግለሰቡ የወባ በሽታ አማጭ ተሐዋሲው አለበት ማለት ነው። ዶክተር ኤዲ አግቦ መቀመጫውን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያደረገው ፊዮዶር ባዮቴክኖሎጂ ኩባንያ ሊቀ-መንበር ናቸው። የደም ናሙና ከመጠቀም ይልቅ ይኼኛው የበለጠ ጠቀሜታ አለው ይላሉ።

«ይኽ የደም ናሙናን የማይጠቀም የመጀመሪያው መመርመሪያ ነው። አንዳች እመርታ ነው። የመመርመሪያ ቁራጭዋን የሽንት መቀበያዋ ውስጥ በማስገባት ለ25 ደቂቃ መጠበቅ ነው። ምንም አይነት ነገር መቀላቀል አለያም አንዳችም ኬሚካል መቀየጥ አያስፈልግም። ምንም ተጨማሪ መሣሪያ ሊኖርህ አይገባም። እጅግ ሲበዛ ቀላል ነው። በሽንት ጠብታ እርግዝናን ከሚመረምረው ቁራጭ ጋር እጅግ ይመሳሰላል። እናም በቤት ውስጥ የወባ በሽታን በትክክል መመርመር የሚያስችል የመጀመሪያው መሣሪያ ነው። እናም ይኽ በእርግጥም ታላቅ እመርታ ነው።»

ከከተሞች እጅግ በራቁ አካባቢዎች የሚኖሩ አፍሪቃውያን የወባ በሽታ ምርመራ ለማድረግ ሳይችሉ ለኅልፈት ሲዳረጉ ይታያል። መመርመሪያው ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ አንዳንዶች ሲያመነቱ ይስተዋላል። በተለምዶ በርካታ ናይጄሪያውያን ለወባ በሽታ ምርመራ ወደ ሐኪም ቤት ላለመሄድ ያመነታሉ። ይኽ ማለት የወባ በሽታ እንዳለባቸው ሳያረጋግጡ መድሐኒት ለመውሰድ ይሞክራሉ ማለት ነው። ቪቪያን አዴቦላ ከእነዚህ ናይጀሪያውያን አንዷ ናቸው። የደም ናሙና ሰጥቶ ለመመርመር በሐኪም ቤቶች ጊዜን ከማባከን ራስን በራስ ማከሙ የበለጠ ተስማሚ ነው ይላሉ።

«ወባ እንዳለብህ ካወቅህ ቶሎ ብለህ ራስህን ማከም ነው፤ ምክንያቱም ራስህን ሳታስታምም የደም ምርመራ ለማድረግ ልሂድ ብትል እስከዚያ ድረስ ምን እንደሚከሰት አታውቅም። አሁን ለምሳሌ፦ እዚህ ወዳሉት የጤና ማዕከላት ልሂድ ብትል ከጠዋት የጀመርክ እስከ ከሰአት ድረስ መጠበቅ ሊኖርብህ ነው። ምክንያቱም ማዕከላቱ ምርመራ ለማድረግ በሚመጡ ሰዎች ይጨናነቃል። ስለዚህ የሚበጀው ቶሎ መድኃኒት መውሰዱ ነው።»

የወባ ትንኝ ደም እየመጠጠች ተሐዋሲውን ስታስተላልፍ
የወባ ትንኝ ደም እየመጠጠች ተሐዋሲውን ስታስተላልፍምስል picture-alliance/dpa/J.Gathany

እንደ ቪቪያን ያሉ በርካቶች ከፍተኛ ትኩሳት በአጠቃላይ የሚነሳው በወባ በሽታ ብቻ ይመስላቸዋል። በሽንት ናሙና ቤት ውስጥ የወባ በሽታን መመርመር መቻሉ ሰዎች በዘፈቀደ መድሐኒት ከመውሰድ እንዲታቀቡ እና ራሳቸውን በራሳቸውንም ለመመርመር ያበረታታል ሲሉ የሕክምና ባለሙያዎች ተስፋ ሰንቀዋል። ራስን በራስ ቤት ውስጥ በመመርመር በእርግጥም የወባ አማጪ ተሐዋሲ በሰውነት ውስጥ መኖር አለመኖሩን ማወቁ ተገቢውን መድኃኒት ለመውሰድ ይረዳል። የናይጄሪያ ብሔራዊ የጤና አቅርቦት ማኅበራት ፕሬዚዳንት ዶክተር ዑማር ኦሉዋሌ ሳንዳ ለወባ በሽታ እየተባለ ያለአግባብ የሚወሰዱ መድኃኒቶች የወባ ተሐዋሲያን መድኃኒቹን እንዲቋቋሙ ያደርጋሉ ይላሉ። አሁን ግን በአዲሱ የወባ ተሐዋሲ መመርመሪያ ሰዎች በሽንት ናሙና በሽታውን መለየት በመቻላቸው ያለአግባብ መድኃኒቶችን መውሰድ ይቀንሳል እንደ ዶክተር ዑማሌ ገለጣ።

«አንድ ሰው ወባ እንዳለበት ሳይታውቅ የወባ ህክምና አታደርግለትም። ይኽ ክሎሮኪን በተሰኘው የመድኃኒት አይነት ላይ የተከሰተ ነው። ክሎሮኪንን ሰዎች በተደጋጋሚ ያለአግባብ በመውሰዳቸው የወባ ተሐዋሲ ክሎሮኪንን መቋቋም ለምዷል። ስለዚህ ክሎሮኪንን ከእንግዲህ ልንጠቀመው አንችልም። አሁን በጥቅም ላይ ያሉትን፤ አርተሚሲን ከተሰኙ እጽዋት የሚቀመሙ እንክብሎችም ያለአግባብ መውሰድ የለብንም። ይኽ አዲሱ የወባ በሽታን በሽንት ናሙና የሚመረምረው መሣሪያ ለበርካታ የጤና ባለሙያዎች ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው።»

በናይጄሪያውያን ሣይንቲስቶች ምርምር ተግባራዊ የሆነውን ይህን ቀላል፣ ግን ደግሞ በቤት ውስጥ የሚያገለግል የወባ መመርመሪ መሣሪያ ከናይጀሪያ ውጪም በአፍሪቃ እና እስያ ሃገራት ለማዳረስ ታቅዷል። በእነዚህ ሃገራት በወባ የሚያልቀው ነዋሪ ቁጥር በቀላሉ የሚጠቀስ አይደለም።

የወባ በሽታ በዓለማችን የሆነ አንድ ቦታ ላይ በየደቂቃው የአንድ ህፃን ሕይወት ይቀጥፋል። እንደ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት አድን ድርጅት በእንግሊዝኛ ምህፃሩ (UNICEF) ገለጣ በየዓመቱ 219 ሚሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘው በተለይ በአፍሪቃ የሚገኙ 660,000 ህፃናት እስከወዲያኛው ያሸልባሉ። በዓለማችን በወባ በሽታ ሰበብ ከሚሞተው ነዋሪ ኢትዮጵያን ጨምሮ 95 በመቶው በአፍሪቃ ነው የሚገኘው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ

የወባ በሽታ ስርጭት በዓለም ዙሪያ
የወባ በሽታ ስርጭት በዓለም ዙሪያ