1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወጣቶች የስራ አሳብ እና ገንዘብ ፍለጋ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 30 2007

ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የትውልድ ቀያቸውን ጥለው የሊቢያ በረሐና የሜድትራኒያን ባህርን ከሚያቋርጡባቸው ምክንያቶች መካከል የተሻለ የስራ እና የኑሮ ሁኔታ እንደሆነ ይነገራል። በኢትዮጵያ የሚገኙ ወጣቶችም በሙያና ክህሎታቸው ስራ ለመጀመር የሚያደርጉት ጥረት በገንዘብ እና የመስሪያ ቦታ እጥረት እንደሚስተጓጎል ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/1FN39
Addis Ababa (Äthiopien)
ምስል picture alliance/landov

ዮናታን በቀለ የልብስ ቅድ ባለሙያ ነው። አልባሳት፤ቦርሳ እና ጌጣ ጌጦችን ከቆዳ መስራት የሚችልበትን ሙያም ሰልጥኗል። ዮናታን ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመሆን የራሱን ድርጅት ለማቋቋም ሙከራ አድርጎም ያውቃል። መንገዱ ግን አልጋ ባልጋ አልሆነለትም። ዋንኛው ፈተና ደግሞ የገንዘብና የመስሪያ ቦታ እጦት ነው።

የኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ጌታቸው ተ/ማርያም የኢትዮጵያ ባንኮች እና የገንዘብ ተቋማት እንደ ዮናታን ላሉ ወጣቶች አዲስ ሃሳብን ተቀብለው ለመደገፍ ቸልተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ። «አንድ ሰው ከባንክ ብድር ለማግኘት የሚፈልግ ከሆነ እዳውን እንደሚከፍል የሚያረጋግጡት ተሽጦ ዋጋ ሊያወጣ የሚችል አንድ አይነት ማስያዣ በሚያሲዝበት ጊዜ ነው።» ይህ ደግሞ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው በእውቀትና ክህሎታቸው ስራ ለመጀመር ለሚፈልጉ ወጣቶች እንዲህ ቀላል አይሆንም። የኢኮኖሚ ባለሙያው «አንድን ሃሳብ ወይም የንግድ እቅድ መሰረት አድርገው የሚሰጡት የብድር አይነት አሁን ዝቅተኛ ሊባል የሚችል ነው።» ሲሉ ያስረዳሉ።

Hauptcampus der Universität Addis Abeba AAU
ምስል DW

መስፍን ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ በታክሲ ስራ ላይ የተሰማራ ወጣት ነው። ከታክሲ አገልግሎት በተጨማሪ የሰርግ እና ሰራተኛ የማመላለስ ስራ ይሰራል። መስፍን በድሬደዋ ለታክሲ አገልግሎት የሚጠቀምባት መኪና ሬድ ስታርስ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ በተባለ የንግድ ድርጅትና በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ስምምነት በብድር የተገዛች ነች። «ስራውን የጀመርኩት ድርጅቱ የብድር አገልግሎቱን አመቻችቶልኝ ነው።» የሚለው መስፍን በህዝብ ትራንስፖርት ስራው በየወሩ ያለበትን ብድር ከፍሎ እቁብ እስከ መጣል አስችሎታል። «በቀን ከስምንት እስከ ዘጠኝ መቶ ብር ከወጪ ገቢ አገኛለሁ። ስራውን ከጀመርኩ አሁን አምስት ወር ሆኖኛል። የብድር ስምምነታችን በወር 4,800 ብር እንድከፍል ነው። ለእነሱ ከምከፍለው ውጪ በሳምንት 2,000 ብር እቁብ እጥላለሁ።»

አቶ ደመቀ ዘውዴ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ናቸው። ባንካቸው አሁን በህዝብ ማመላለስ ስራ ላይ መሰማራት የሚፈልጉትን ጨምሮ የተለያዩ ሙያ ባለቤት ለሆኑ ወጣቶች የብድር አገልግሎት ያቀርባል። ገቢና ወጪያቸውን ይከታተላል። እገዛም ያደርጋል። አቶ ደመቀ ዘውዴ የራሳቸውን ስራ መጀመር ለሚፈልጉ ወጣቶች ላቀረቡት የብድር አገልግሎት ያቀረቧቸው መስፈርቶች ውስብስብ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በአብዛኛው በገጠር የሚኖር ከፍተኛ የሆነ ወጣት ህዝብ ያላት አገር ናት። 80 በመቶው ኢትዮጵያዊ በአነስተኛ የእርሻ ስራዎች ላይ የተሰማራ ነው። በአለም አቀፉ የስራ ድርጅት( International Labour Organization) መረጃ መሰረት በየአመቱ በ4 በመቶ ከሚያድገው የከተማ ህዝብ ውስጥ እድሜያቸው ከ15 እስከ 30 የሆኑ መካከል 50 በመቶው ስራ አጥ ናቸው።

Karte Äthiopien englisch

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በፍጥነት ቢስፋፉም አሁንም ለወጣት ተመራቂ ተማሪዎች የስራ እድል እጥረት መኖሩ ይታያል። እንደ ዮናታን በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ የራሳቸውን ስራ ለመስራት የሚታትሩት ደግሞ የገንዘብ እና የመስሪያ ቦታ እጥረት ይፈታተናቸዋል። እንደ መስፍን ከግል የገንዘብ ተቋማት የብድር አገልግሎት የማግኘቱ ነገር እምብዛም የተለመደ አይደለም። አቶ ጌታቸው ተ/ማርያም የግል የገንዘብ ተቋማት ለአዳዲስ የስራ ሃሳቦች ገንዘብ ለማበደር እና ለመደገፍ የሚገጥማቸውን ፈተና ለመውሰድ ዝግጁ አለመሆናቸውን ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ የመንግስት ባንኮች ግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። የዘርፉ ባለሙያዎች በመንግስትና ባለወረቶች የሚከወኑት ትልልቅ ስራዎች በርካታ ለበርካቶች የስራ እድል ይፈጥራል የሚለውን አቋም የፖሊሲ ስህተት ሲሉ ይተቻሉ። የግል ባንኮች ደግሞ ለአክሲዮን ባለድርሻዎች የትርፍ ፍላጎት ቅድሚያ ይሰጣሉ። የገንዘብ ድጋፋቸውም በሚያውቋቸው እና ከፍተኛ ትርፍ በሚያገኙባቸው የስራ ዘርፎች የተወሰነ ነው።

እሸቴ በቀለ

ተክሌ የኋላ