1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዉኃ አቅርቦት በኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 15 2007

«ዉኃና ዘላቂ ልማት» ከአንድ ቀን በፊት በመላዉ ዓለም የታሰበዉ የዘንድሮዉ የዓለም የዉኃ ቀን መሪ ቃል ነዉ። ለጤና፤ ለአካባቢ ልማት፤ ለኢንዱስትሪ ባጠቃላይ ለዕለት ከዕለት ኑሮ ወሳኝ መሆኑን በተለያዩ መድረኮች ለማሳየትም ተሞክሯል።

https://p.dw.com/p/1EwL4
Wasser Trinkwasser Wasserhahn läuft
ምስል Fotolia/Dev

እርግጥ ስለዉኃ ወሳኝ የሕይወት ሚና ከሰዉ በላይ ማን ሊናገር ይችላል? የሰዉ ልጅ ካለምግብ ቀናት ካለ ዉሃ ሰዓታትን ብቻ መታገስ መቻሉ አይነተኛ ምስክር ነዉና። ከዓለማችን ሶስት አራተኛዉ እጅ ዉኃ ነዉ ብሎ ሳይንሱ ቢነግረንም ዛሬም በተለያዩ ደሀ ሃገራት ዉኃ ፍለጋ አዋቂና ትናንሽ ሴቶች መንገድ መጓዝ አልቀረላቸዉም። ሕይወት በተስፋ ይለመልማልና እስከመጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2030 ድረስ ይህ ችግር ታሪክ ሆኖ እንደሚቀር ተስፋ ይደረጋል።

በዓለማችን ንፁሕና በቂ የመጠጥ ዉኃ ከማያገኙ 750 ሚሊዮኖች 90 በመቶዉ የሚገኙት እስያ እና አፍሪቃ ዉስጥ ከሰሃራ በስተደቡብ ባሉ ሃገራት መሆኑን የተመ የሕፃናት መርጃ ድርጅት UNICEF የዓለም የዉኃ ቀን በሚታሰብበት ዕለት ዋዜማ ባወጣዉ መረጃ ይፋ አድርጓል። በዚህ ይዞታም በየቀኑ 1,000 ሕፃናት ንፁህ ዉኃ፤ መጸዳጃ፤ የግል እና የአካባቢ ንፅህና ጉድለት በሚከሰቱ በሽታዎች ሕይወታቸዉ እንደሚቀጠፍም ድርጅቱ አመልክቷል። የተመድ አዲስ ጥናት እንደሚያመለክተዉ ሰዎች ዉኃን ቆጥቦ እና በአግባቡ መጠቀምን መልመድ ይኖርባቸዋል። ይህ ካልሆነ ግን በጎርጎሪዮሳዊዉ 2050 55 በመቶ ሊጨምር ይችላል ተብሎ የሚገመተዉን የንፁሕ ዉኃ ፍላጎት ለማሟላት ከወዲሁ ችግር ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት አለ። ዛሬም በዓለማችን ከፍተኛ የዉኃ እጥረት ችግር የሚታይባቸዉ ታላላቅ ከተሞች አሉ። የህንዷ ዴሊህ አንዷ ናት።

Dürre/extreme Wasserknappheit in Neu Delhi
የንፁሕ ዉኃ እጥረት በሕንድምስል DW

ስለንፁሕና በቂ የዉኃ አቅርቦት ሲነገርም የግልና የአካባቢ ንፅሕና መጠበቂያ እንዲሁም የመጸዳጃ ጉዳይም አብሮ ይጠቀሳል። በተመድ በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2015 ድረስ እንዲሳኩ ካለማቸዉ የልማት ግቦች አንዱም ይህን ይመለከታል። በዘንድሮዉ የዓለም የዉኃ ቀንም ኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት እጅግ ዝቅተኛ የነበረዉን የንፁሕ የመጠጥ ዉኃ አቅርቦት ወደ57 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሏ ተነግሯል። በUNICEF ኢትዮጵያ ንፁሕ ዉኃና የግልና የአካባቢ ፅዳት ዘርፍ ኃላፊ ሳሙየል ጎድፍሬ ይህ መሻሻልም ሀገሪቱን ከጎረቤቶቻ የተሻለች አድርጓታል ይላሉ፤

«የኢትዮጵያ መንግሥት ከልማት አጋሮቹ በመሆን ሰባተኛዉን የአምዓቱን የልማት ግብ ስኬት አክብሯል። ይህም ሀገሪቱ በዘጠናዎቹ መጀመሪያ ከነበረዉ 17 በመቶ ብቻ ተንስቶ አሁን የንፁሕ ዉኃ አቅርቦቷ 57 በመቶ ደርሷል። በአካባቢዉ በምሥራቅና ደቡብ አፍሪቃ ከሚገኙ ጎረቤት ሃገራት ጋ ሲነፃፀርም ኢትዮጵያ ታላቅና ግሩም መሻሻሎችን አድርጋለች።»

እሳቸዉ የገለጹት ዝርዝር መረጃም የዓለም የጤና ድርጅትና ዩኒሴፍ በጋራ በሚያካሂዱት ንፁሕ ዉኃ የማዳረስና የግለሰብና የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅን የሚመለከት መርሃግብር አማካኝነት በገለልተኛ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ከኅብረተሰቡ የተሰበሰበ መሆኑንም ጨምረዉ አስረድተዋል። የንፁሕ ዉኃ አቅርቦት መሻሻሉና መጨመሩ መልካም ዜና የመሆኑን ያህል አሁንም ግን ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን ጨምሮ በትላልቅ ከተሞችም ሳይቀር ኅብረተሰቡ በተከታታይ አንዳንዴም ለቀናት ዉኃ ማጣቱን ሲገልፅ ይደመጣልና ይህ እንዴት ይታያል ያልኳቸዉ የዩኒሲየፍ ባልደረባ የከተሞች መስፋፋት ጦስ መሆኑን ነዉ የገለፁት።

GMF13 Klick13106 Klick13 Bildergalerie Indien
ምስል Erolina Rodrigues

«ይህ የከተሞች መስፋፋት የሚያስከትለዉ እዉነታ ነዉ። ከተሞች በተስፋፉ ጊዜ የኗሪዎች የዉኃ አቅርቦት ጥያቄና ፍላጎት ከፍ ይላል። በአሁኑ ጊዜ ለአዲስ አበባ ዉኃ የሚያቀርበዉ ምርጭ የተቀረፀዉ 20 ሊትር ወይም አንድ ባልዲ ዉኃ በቀን ለአንድ ሰዉ በሚል ነዉ። ይህም ታሳቢ ያደረገዉ አብዛኞቹ በየቤታቸዉ የቧንቧ ዉኃ ስለሌላቸዉ ይህ በቂ ይሆናል በሚለዉ መነሻ ነዉ። ሆኖም ግን አሁን ብዙዎች ለመጸዳጃ ቤት እና የገላ መታጠቢያ ጭም ብዙ ዉኃ መጠቀማቸዉ በመስፋፋቱ በግለሰብ ደረጃ በቀን ከ20 ሊትር በላይ የሚፈልጉበት ሁኔታ እየታየ ነዉ። ይህ ደግሞ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች በዉኃዉ መሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳረፉ ግልፅ ነዉ።»

በመላዉ ዓለም በየሳምንቱ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ወደከተሞች እንደሚፈልስ የተመድ አመልክቷል። እርግጥም ዉኃ ለከተሞች መስፋፋት አቢይ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል።

የዘንድሮዉ የዓለም የዉኃ ቀን በታሰበ ማግስት ነዉ ኢትዮጵያ ከተመድ የአምዓቱ የልማት ግቦች በተለይ ንፁሕ የመጠጥ ዉኃን ማዳረስን የሚመለከተዉ ላይ ትርጉም ያለዉ መሻሻል ማሳየቷ ይፋ የሆነዉ።

የምሥራቅና ደቡብ አፍሪቃ የዩኒሴፍ ዳይሬክተር ትናንት ይህንን አስመልክቶ በተካሄደ ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግርም ይህ ስኬት የዓመታት ጥረት ዉጤት መሆኑን ሳያመለክቱ አላለፉም። ለዚህም ከጊዜ በተጨማሪ ጠቀም ያለወጪ እዉቀትና መዋዕለ ንዋይ በየደረጃዉ ፈስሶበታል። እንዲያም ሆኖ አሁንም 42 ሚሊዮን ሕዝብ ንፁሕ የመጠጥ ዉኃ የማግኘት እድሉ የለዉም እንደዩኒሴፍ። የመሠረተ ልማት አዉታሩ መስፋፋት በሂደት በተለይ በገጠርና ገጠር አካባቢ ለሚኖረዉ ወገን ይህን እድል ሊያመቻችለት እንደሚችል ቢታመንም ቀሪዉ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ንፁሕ ዉኃ ማግኘት እስኪችል ዓመታት እንደሚያስፈልጉ ግልፅ ነዉ።

Symbolbild Wasserknappheit in Asien
ምስል AFP/Getty Images

ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይ ዉኃ ለማግኘት ረጅም መንገድ መጓዝ በሚገደዱ አካባቢዎች ንፁሕ ዉኃ የሚያገኙባቸዉን ዘዴዎች በማመቻቸት ወርልድ ቪዥን የተሰኘዉ መንግሥታዊ ያልሆነዉ የዉጭ ድርጅት ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል። በዚህ ረገድ ባለፉት አራት ዓመታት ባከናወናቸዉ ተግባራት ብቻም ወደ600,000 ሕዝብ ሊጠቀም መቻሉን የድርጅቱ የዉኃና የስነንፅሕ አጠባበቅ በእንግሊዝኛ ምህፃሩ WASH በመባል የሚታወቀዉ የሥራ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደረጀ ዓለሙ ገልፀዉልናል።

ኢትዮጵያ ዉስጥ በጎርጎሪዮሳዊዉ የዘመን ቀመር ከ1970ዎቹ አንስቶ ለእርዳታ የተሰማራዉ ዎርልድ ቪዥን ከመነሻዉም ንፁሕ ዉኃን በየአካባቢዉ በማቅረብ ሥራዉን መጀመሩንም አቶ ደረጀ አስታዉሰዋል። አብዛኛዉ ሥራም ዉኃን ቆፍሮ ማዉጣት ላይ ያተኮረ ነዉ።

ንፁሕ የመጠጥ ዉኃ የማዳረሱ ጥረት ሲታሰብም እንደየኣካባቢዉ በቀን አንድ ሰዉ ስንት ሊትር ዉኃ ይጠቀማል የሚለዉ ከምት እንደሚገባም አቶ ደረጀ ያስረዳሉ። ዩኒሴፍ ይፋ እንዳደረገዉ በመላዉ ዓለም በየቀኑ ንፁሕ ዉኃን በማጣት በሚመጡ የተለያዩ በሽታዎች 1000 ሕፃናት ይቀጠፋሉ። ሁኔታዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ምን ይመስላል ያልኳቸዉ የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ባልደረባ ሳሙኤል ጎድፍሬ በበኩላቸዉ አሉ ያሏቸዉን መሻሻሎች ገልጸዋል።

«ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን ሞት መቀነስን በሚመለከት ከፍተኛ መሻሻሎች ታይተዋል። የአምዓቱ የልማት ግብ በሚታሰብበት በአሁኑ ጊዜም ቁጥሩ በአንድ ሶስተኛ ቀንሷል። ለዚህ ለዉጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ደግሞ የንፁሕ ዉኃ አቅርቦትና የንፅሕና መጠበቂያ ስልቶች መሻሻል ነዉ። እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይ በጤና አገልግሎት ማዕከላትና ባጠቃላይ በጤና ጥበቃዉ ዘርፍ ንፁሕ ዉኃና የንፅሕና መጠበቂያ አቅርቦትን ለማሻሻል ከፍተኛ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።»

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ