1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዋጋ መናር በጋና ያስከተለው ተቃውሞ

ሐሙስ፣ ጥር 12 2008

በጋና የአገልግሎት እና የነዳጅ ዋጋ መናር በሰራተኛው መደብ ዘንድ ብርቱ ተቃውሞ ቀሰቀሰ። ሰራተኞች የዋጋውን ንረት ለመቋቋም እንዲችሉ የደሞዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ መንግሥት ጥያቄአቸው አዎንታዊ መልስ ሳያገኝላቸው ቀርቷል።

https://p.dw.com/p/1Hhqr
GOIL Ölgesellschaft Ghana Oil Company Limited
ምስል DW/S. Duckstein

[No title]

በዚህም የተነሳ፣ አይዜክ ካልዴዚ እንዳመለከተው፣ ብዙ ሰራተኞች የጋና ሙያ ማህበራት ኮንግረስ በዋና ከተማይቱ አክራ በትናንቱ ዕለት በጠራው የአደባባይ ሰልፍ በመገኘት ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል።


በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ጋና መዲና አክራ በትናንቱ ዕለት በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰራተኞች በሀገሪቱ የአገልግሎት እና በነዳጅ ዋጋ ላይ የተደረገውን ጭማሪ በመቃወም አደባባይ ወጥተው ዋሉ። ተቃውሞውን በቀሰቀሰው ርምጃ መሰረት፣ የውኃ ዋጋ በ59%፣ የኮሬንቲ ዋጋ በ67%፣ እንዲሁም፣ የነዳጅ ዋጋ በ27% ጭማሪ ታይቶበታል። በዚህም የተነሳ ብዙ የጋና ተወላጆች ቀጣዩን ክፍያ ማሟላት እንደማይችሉ ነው የገለጹት። መንግሥት በነዚህ መሰረታዊ አገልግሎቶች ላይ የተደረገውን ጭማሪ እንዲቀንስ ለማስገደድ የሙያ ማህበራት ዛሬን እና ነገን በሀገር አቀፍ ደረጃ ጠቅላላ የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ እቅድ ይዘዋል። ሰራተኞቹ በዚሁ እቅዳቸው እንዳይገፉበት ባለስልጣናት ተማጽነዋል። ይሁንና፣ ተቃውሞውን የጠራው የጋና ሙያ ማህበራት ኮንግረስ ዋና ጸሐፊ ኮፊ አሳሞአ የሰራተኞቹ ጥያቄ እና ርምጃ ትክክለኛ መሆኑን ነው አስረድተዋል።


« የተደራጀው የሙያ ማህበራት ቡድን በአገልግሎት የተደረገው የዋጋ ጭማሪ እንዲቀነስ እና በአንቀጽ 899 በኃይሉ ምንጭ ዘርፍ ላይ የታወጀው ቀረጥ እንዲሻር ጥሪ አቅርቦዋል። ለችግሩ ማስወገጃ ሁሉን ወገን የሚያስማማ አዎንታዊ መፍትሔ እንዲያስገኝ የተቋቋመው ቡድን ግን እስካሁን አጥጋቢ ውጤት ማስገኘት ሳይሳካለት ቀርቷል። »
እርግጥ፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ መርህ ድርጅት ለሀገሪቱ መንግሥት የሰጠውን ብድር ተከትሎ በመንግሥት ላይ ያሳረፈው ጫና ቀላል አለመሆኑን ቢረዱትም፣ የዋጋው ንረት ከሕዝቡ አቅም በላይ መሆኑን አሳማዎ አስታውቀዋል።
የስራ ግንኙነት ሚንስትር ሀሩና ኢድሪሱ የሰራተኞቹን ጥያቄ ማሟላት አዳጋች መሆኑን በማመልከት፣ ምንም እንኳን መንግሥት ለችግሩ መፍትሔ ለማስገኘት ጥረት ቢጀምርም፣ የሙያ ማህበራቱ ኮንግረስ ተቃውሞውን ለመቀጠል የደረሰው ውሳኔ ቅር መሰኘታቸውን አስታውቀዋል።
« የተደራጀው የሙያ ማህበር በኃይሉ ምንጭ ዘርፍ ላይ በአንቀጽ 899 የታወጀው ቀረጥ እንዲሻር እና የዋጋው ንረትም በ50% ዝቅ እንዲል ባቀረበው ጥያቄ ላይ መንግሥት ድርድር በያዘበት በአሁኑ ጊዜ ፣ቡድኑ ተቃውሞውን እና የስራ ማቆሙን አድማ ለመቀጠል መወሰኑ ነው ቅር ያሰኘኝ። ይህን ርምጃውን ራስህ ላይ ጠመንጃ ተደቅኖብህ ድርድር እንደማካሄድ ነው የምመለከተው። »
የአገልግሎት እና የነዳጅ ዋጋ መናር የብዙዎቹን የጋና ተወላጆችን በጀት እያቃወሰ ነው። በመሆኑም፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያቀዱትን የስራ ማቆም አድማ ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይሉ ያስታወቁት የሙያ ማህበራቱ ኮንግረስ መሪዎች ከመንግሥት ጋር የጀመሩትን ድርድር በዚህ ሳምንት እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። ይኸው ርምጃቸው የዋጋው መናር በሰራተኞቹ የዕለት ከዕለት ኑሮ ላይ ምን ያህል ችግር እንደፈጠረባቸው የሚያሳይ ትክክለኛ ርምጃ መሆኑን አንዳንዶቹ ተቃዋሚዎች አመልክተዋል።
« ችግሩ ከአቅም በላይ ስለሆነብን ነው እንጂ እኛ በመንግሥት አንጻር ሆነን አይደለንም ። »
« ፕሬዚደንት ጆን ድራማኒ ማሀማ ችግራችንን እንዲረዱልን እንፈልጋለን። እኛ የጋና ተወላጆች እየተሰቃየን ነው። የኮሬንቲ ሂሳባችንን መክፈል አልቻልንም። አሁን ደግሞ የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ሸክሙ ከብዶናል። በዚህ ስርዓት ውስጥ ኑሮን መቋቋም አልቻልንም። »
የአደባባዩ ተቃውሞ በችግር ላይ የሚገኘውን የሀገሪቱን ኤኮኖሚ ይበልጡን እንዳይጎዳው ማስጋቱን የቀድሞ የጋና ብሔራዊ የስራ ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር ክዌዚ ዳንሶ አቺ አምፖንግ ገልጸው፣ ይኸው ስጋት ሊወገድ የሚችልበት ሁኔታ የጋና መንግሥት እስከ ሳምንቱ መጨረሻ በሚወስደው ርምጃ ላይ ጥገኛ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

Future Now Projekt Viren2 Bushmarket Bild 7
ምስል DW/A. Cizmecioglu

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ