1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዌስትጌት የገበያ ማዕከል ስራ ሊጀምር ነው

ሐሙስ፣ ሐምሌ 9 2007

ከሁለት አመታት በፊት ከአሸባብ ታጣቂ ቡድን በተጣለ ጥቃት 67 ሰዎች የተገደሉበት የዌስትጌት የገበያ ማዕከል በሚቀጥለው ቅዳሜ ተከፍቶ ስራ ይጀምራል። የኬንያ መንግስት ወታደሮች ለአራት ቀናት የገበያ ማዕከሉን የተቆጣጠሩትን የአሸባብ ታጣቂዎች ለመደምሰስ ባቀጣጠለው እሳት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት የነበረው

https://p.dw.com/p/1G0FJ
Kenia Nairobi Gedenken Westgate 2014
ምስል Simon Maina/AFP/Getty Images

[No title]

የህንጻው አካል እንደገና መገንባቱን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

በኬንያ ዋና ከተማ የሚገኘው የዌስትጌት የገበያ ማዕከል ለሁለት አመታት ከተዘጋ በኋላ ቅዳሜ ይከፈታል። ለአራት ቀናት በአሸባብ ታጣቂዎች ተይዞ የቆየውና 67 ሰዎች የተገደሉበት የገበያ ማዕከል በደረሰበት ፍንዳታና የእሳት አደጋ ከፍተኛ ውድመት ደርሶበት ነበር። በአንድ ወቅት የኬንያ እድገት መገለጫ የነበረው የገበያ ማዕከል ከእንግሊዛዊቷ ሳምንታ እና የአሸባብ ታጣቂዎች አሰቃቂ ጥቃት በኋላ የአገሪቱ የደህንነት ስጋት መገለጫ ወደ መሆን ተቀይሮ ነበር።

በገበያ ማዕከሉ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል በመገናኛ ብዙሃን ከተሰራጨ በኋላ ወደ ኬንያ ለመጓዝ በሚሹ አገር ጎብኚዎች ላይ ስጋትና ፍርሃት በማሳደሩ የቱሪዝም ኢንደስትሪውን ብሎም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ ጎድቷል። በጥቃቱ መጠናቀቂያ የአሸባብ ታጣቂዎች ከተገደሉ በኋላ የአገሪቱ ወታደሮች የገበያ ማዕከሉን ሲዘርፉ መታየታቸው ደግሞ ኬንያን ክፉኛ አስተችቷታል።
የናይሮቢ ከተማ አስተዳዳሪ ኢቫንስ ኪዴሮ ከሁለት አመታት በፊት የተፈጸመውን ጥቃት የሚያስታውሱት በሐዘን ነው።
«ልክ ከ22 ወራት በፊት በዚህ ቦታ በመጥፎ አጋጣሚ በዕለተ ቅዳሜ የገጠመንን አሰቃቂ አደጋ ጊዜ ስናስታውስ በሐዘን ትዝታ ነው።ነገር ግን ከ22 ወራት በኋላ ተመልሰናል።»

Westgate mall in Nairobi Kenia
ምስል DW/A. Kiti

ከ22 ወራት በኋላ እንደገና ታድሶ ቅዳሜ ለአገልግሎት በሚከፈተው የዌስትጌት የገበያ ማዕከል ፈጣን ምግብ በማቅረብ የሚታወቁት ሰብዌይና ኬኤፍሲ የጫማ አምራቹ ኮንቨርስን የመሳሰሉ የምዕራቡ አገራት ኩባንያዎች እንዲሁም ከኬንያ ናኩማት የተባለው ሱፐር ማርኬት አገልግሎት ይጀምራሉ ተብሏል።

አሸባብ የዌስትጌት የገበያ ማዕከልንና የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጥቃት ጨምሮ በኬንያ ምድር ከ400 በላይ ሰዎች ገድሏል። የታጣቂ ቡድኑ ተከታታይ ጥቃቶች የኬንያ መንግስትን የጸጥታ ተቋማት ድክመት በግልጽ አሳይተዋል። ባለስልጣናቱ በጸጥታው ዘርፍ ሹም ሽር ቢያካሂዱም የፈየዱት አንዳች ነገር የለም። የአሜሪካኑ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ወደ ኬንያ ለመጓዝ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው የዌስትጌት የገበያ ማዕከልን የጎበኙት የናይሮቢ አስተዳዳሪ ኢቫንስ ኪዴሮ አገራቸውም ከምንጊዜውም በላይ ደህንነቷ የተረጋገጠ ነው ሲሉ ተናግረዋል። እንደ አስተዳዳሪው አባባል ከሆነ አለበለዚያ የአሜሪካኑ ፕሬዝዳንት ኬንያን ባልጎበኙ ነበር።

የጽዳት ሰራተኛዋ ዲቪና ሞሰ ከሁለት አመታት በፊት በአሸባብ ታጣቂዎች የተፈጸመውን ግፍ በአይኗ አይታለች። ወደ ዌስትጌት የገበያ ማዕከል ተመልሳ የመጣችው ዲቪና የስራ ባልደረቦቿን በዚያ ጥቃት አጥታለች።

«በጥቃቱ ወቅት በምግብ ማብሰያው ክፍል ተደብቀን ነበር። የምንሰማው የጥይት ተኩስ ብቻ ነበር። ከጥቃቱ በኋላ በርካታ ሰዎች ሞተው ተመልክተናል። ከስራ ስራ ባልደረቦቻችን መካከል የወሰኑትን አስከሬን መሬት ላይ ተጋድሞ አይተናል። ወደዚህ ተመልሼ የመጣሁት በስራዬ ምክንያት ነው።»

World Press Photo 2014 Tyler Hicks EINSCHRÄNKUNG
ምስል Reuters/Tyler Hicks/World Press Photo

አሁን አዲስ የሚከፈተውን የገበያ ማዕከል የጥበቃ ስራ «አይአርጂ» የተባለ የእስራኤል ኩባንያ ተረክቦታል። የገበያ ማዕከሉ 25 ልዩ የቢሮ ሰራተኞችና 55 የጥበቃ ጓዶች ተመድበውለታል።ዘመናዊ የፈንጂና የሻንጣ መመርመሪያዎች የጥይት መከላከያ የተገጠመላቸው የጥበቃ ማማዎችም አሉት።
የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ኬንያ ከጎርጎሮሳዊው 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ በመላኳ ጥቃቶቹ የበቀል መሆናቸውን አስታውቋል።

እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ