1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዐቢይ አሕመድ የኖቤል ሽልማትና የኤርትራ ሁኔታ! 

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 1 2012

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥም እንዲህ እንደትላንቱ በደስታ እና በሙገሳ ተነስቶ አያውቅም። ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያዊ ዜጋን ደጃፍ ያንኳኳው እና በዓለም በትልቅነቱ ወደር የማይገኝለት የኖቤል የሰላም ሽልማት ብዙዎች ዳግም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ተስፋ እንዲያጭሩ አድርጓቸዋል።

https://p.dw.com/p/3RBFe
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

በፍቃዱ ኃይሉ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥም እንዲህ እንደትላንቱ በደስታ እና በሙገሳ ተነስቶ አያውቅም። ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያዊ ዜጋን ደጃፍ ያንኳኳው እና በዓለም በትልቅነቱ ወደር የማይገኝለት የኖቤል የሰላም ሽልማት ብዙዎች ዳግም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ተስፋ እንዲያጭሩ አድርጓቸዋል። ለመሆኑ የሰላም ኖቤል ሽልማቱ እና የኢትዮ-ኤርትራ እርቀ ሰላም ለኢትዮጵያውያን እና ለኤርትራውያን ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?

ስለ ኖቤል ሽልማት ብዙ ተብሏል። ነገር ግን ዝናውን የሚያወርድ ነገር አልተገኘም። የዐቢይ አሕመድ መሸለምም የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ክብር ተደርጎ ነው በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የተወሰደው። ብዙ ጊዜ ችግሮቻቸው ብቻ የዓለም መነጋገሪያ የሚሆንባቸው ኢትዮጵያውያን እንዲህ ባለ ሽልማት መሪያቸው ሲከብር መደሰታቸው አያስገርምም። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኖቤል ተሸላሚ የሆኑበት ምክንያት ሲገለጽ "ለሰላምና ዓለም ዐቀፍ ትብብር ያደረጉት ጥረት" እንዳስመረጣቸው ተነግሯል፤ ይህንን በተመለከተ "ይገባቸዋል" ለማለት የሱዳን ተቃዋሚዎችን እና ወታደራዊ አመራሩን በማሸማገል የሔዱበትን ርቀት ማስታወስ ይበቃል። ሱዳናውያን በሁለቱ ጎራዎች ሥምምነት ላይ ሲደረስ ደስታቸውን ሊገልጹ አደባባይ ሲወጠ የኢትዮጵያን ባንዲራ የያዙት ለዚያ ነበር። በመቀጠልም ሽልማቱ የተሰጣቸው "በተለይ ከጎረቤታቸው ኤርትራ ጋር የነበረውን ግጭት ለመፍታት የወሰዱት ቆራጥ ተነሳሽነት" ታይቶ እንደሆነ ተገልጿል። 

በአጭሩ ለማስታወስ ያህል የኢትዮ-ኤርትራ እርቀ ሰላም ፍፁም አስገራሚ ነበር። ለሁለት ዐሥርት ዓመታት በኩርፊያ የነበሩት አገራት ድንገት በጠቅላይ ሚኒስትር በር አንኳኪነት ተሰበረ። ባልተጠበቀ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስመራ ሔደው የተደረገላቸው ሕዝባዊ አቀባበል በቴሌቪዥን ሲተላለፍ ብዙዎችን በደስታ እምባ አራጭቷል። የስልክ መሥመር ሲከፈት ሰዎች በደስታ አቅላቸውን አጥተው የማያውቁት ሰው የኤርትራ ቁጥር ላይ ደውለው አውርተዋል። የተጠፋፉ ቤተሰቦች ዳግም ተገናኝተው ተላቅሰዋል። ሰዎች በአፈና የዘነጉትን የእህትማማች፣ ወንድማማችነት ትዝታ ከተዳፈነበት ቆስቁሰው አውጥተውታል። በድንበር አካባቢ ያለው ጉርብትና ታድሶም በአጭር ጊዜ ገበያው ሲደራም ታይቶ ነበር። እናም ድርጊቱ በቅርብ ጊዜ በቀጠናው ከታዩ ክስተቶች ሁሉ እጅግ ትልቅ ተስፋ ሰጪ ነበር። 

ለኤርትራውያን ግን…

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሰላም ባወረዱ ባጭር ጊዜ ውስጥ እልፍ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ የስደተኛ ካምፖች በገፍ ይጎርፉ ጀመር። በዚህ የተደናገጡት ኢሳይያስ ድንበሩን መልሰው ዘጉት። ድንበሩ ድጋሚ ቢከፈትም ድጋሚ ተዘግቷል። 

በጠቡ ጊዜ በኢትዮጵያ መንግሥት እየተደገፉ የኤርትራን መንግሥት ይቃወሙ የነበሩት ኤርትራውያን የደኅንነት ሥጋት ገባቸው። ተቃዋሚዎቹ ዐቢይ አሕመድ ለእርቁ ካላቸው ጉጉት የተነሳ ለፕሬዚደንት ኢሳይያስ አሳልፈው እንደማይሰጧቸው እርግጠኛ መሆን አልቻሉም። ድንጋጤ ወደ ሌላ አገር እንዲሸሹ ያደረጋቸውም ነበሩ። 

በሌላ በኩል ፕሬዚደንት ኢሳይያስ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ለውጥ ሳያመጡ ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም በማውረዳቸው ብቻ ጥርስ ነክሰው በማዕቀብ ሲያዳክሟቸው የነበሩ ኀያላን አገራት ማዕቀቡን አስነሱላቸው። በርካታ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚ አክቲቪስቶች ኢሳይያስን ዳግም ቅቡልነት አስገኙላቸው በሚል በዐቢይ አሕመድ ቅሬታ ገባቸው። 

ዐቢይ አሕመድ እርቀ ሰላሙን ያወረዱት ዓለም ዐቀፍ ውሳኔ የሆነውን የአልጀርስ ሥምምነት ለማክበር ቃል ገብተው ነው። ይሁን እንጂ ሥምምነቱን መሬት ለማውረድ እና ለማስቀጠል የሚያበቃ ምን ያህል እርምጃ እንደተሔ ግልጽ አይደለም። ብዙዎቹ ሥምምነቶች በሁለቱ መሪዎች እና በምስጢር በመያዛቸው ከጊዜያዊው ሁኔታ ባሻገር ዘለቄታውን መገመት አልተቻለም። 

…አሁንም ተስፋ አለ?

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሰላም ባወረዱ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በስደት ያሉ ኤርትራውያን የመብት ተሟጋቾች "ይአከል" (ይበቃል) የሚል መፈክር ያለውን ትግላቸውን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ አጧጡፈዋል። በሳተላይት ቴሌቭዥኖችም የተቃውሞ ድምፆች ተጋግለው ቀጥለዋል። አልፎ ተርፎም በኤርትራ ምርጫ ላለማካሔድ እንደ ሰበብ የተወሰደው ጦርነት አሁን ስለሌለ "ምርጫ ይደረግ" የሚል ጥሪ አቅርበዋል። የኋላ ኋላ ደግሞ የአፍሪካ ታዋቂ ሰዎች ተሰብስበው ኢሳይያስ በፖለቲካ ሰበብ አስረው ያሰነበቷቸውን ሰዎች እንዲፈቱ የሚጠይቅ ደብዳቤ ጻፉላቸው። አምነስቲ ኢንተርናሽናልም የታሰሩት ይፈቱ የሚል ዘመቻ በቅርቡ ጀምሯል። ኢሳይያስ ግን ለሁሉም "ጆሮ ዳባ ልበስ" እንዳሉ ናቸው። 

ይህ ተቃውሞ እና ግፊት በሁለቱ አገራት እርቀ ሰላም ማውረድ የመጣ ነው። ኢሳይያስ መንግሥታቸው ከዓለም ተቆራርጦ እና በማዕቀብ የኖረበት ዓመታት ችግር ስለማይዘነጋቸው ተመልሰው እዛ ውስጥ ለመግባት የሚፈልጉ አይመስልም። ሆኖም ሥልጣናቸው አደጋ ላይ የወደቀ ከመሰላቸው መልሰው ሰላሙን ከማደፍረስ የሚመለሱ ዓይነት ሰው አይደሉም። 

ይሁንና ሁኔታዎች ኢትዮጵያ ውስጥም አልጋ ባልጋ አይደሉም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቀጠናው ላይ ሰላም ለማምጣት የጣሩትን ያክል አገር ውስጥ ለማምጣት አልቻሉም በሚል በዜጎቻቸው ይታማሉ። ነገር ግን የኖቤል የሰላም ሽልማቱ የበለጠ ጠንክረው እንዲሠሩና ሥማቸውን የሚመጥን ሥራ እንዲሠሩ ጫና ያሳድርባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። በጥቅሉ የኖቤል ሽልማት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ለአገራቸው የምሥራች ነው። ኤርትራውያን ግን የዚህ ደስታ ተቋዳሽ አለመሆናቸው ሳይጠቀስ የማይታለፍ አሳዛኙ ገጽታ ነው።

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ«DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።