1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዑጋንዳ መንግስትና የግል ፕሬስ ፍጥጫ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 10 1997

በዑጋንዳ ይታይ የነበረዉ የፕሬስ ነፃነት አደጋ እያንዣበበበት ነዉ። በተለይም በቅርቡ ህይወታቸዉ ካለፈዉ ከደቡብ ሱዳን ህዝቦች ንቅናቄ መሪ ዶክተር ጆን ጋራንግ ሞት ጋር በተገናኘ በሚዘገቡት ዘገባዎች የአገሪቱ መንግስት አልተደሰተም። በዚህ ሳቢያም የአገሪቱ መንግስትና በተለይ የግል መገናኛ ብዙሃን ዘርፉ ተፋጠዋል።

https://p.dw.com/p/E0jb

በመንግስት በኩል የግል ጋዜጦችና ራዲዮዎችን የማገድ እርምጃ መወሰድ ተጀምሯል። ይህም በአገሪቱ የጋዜኞች ሙያ ማህበራት፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል። በጋራንግ አሟሟት እንቆቅልሽ ዙሪያ የሚዘገበዉ ዘገባ እንዳልስደሰታቸዉ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የተናገሩት ከጋራንግ ጋር አብረዉ ህይወታቸዉ ያለፈዉ ዑጋንዳዉያን ስርዓተ ቀብር የተፈፀመ ዕለት ነዉ።
በተለይ ሬድ ፔፐር የተባለዉ አንድ የዑጋንዳ የግል ጋዜጣ በዘገባዉ ሄሊኮፕተሯ ከመከስከሷ በፊት ጋራንግ ጭንቅላታቸዉ ላይ በሁለት ጥይት መመታታቸዉን ለንባብ አብቅቷል።
ይህም ለ21ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት ስትማገድ በቆየችዉ ሱዳን የአገሪቱ መንግስት በጋራንግ ሞት እጁ አለበት የሚለዉን ጥርጣሬ ከፍ እንደሚያደርግ ከዑጋንዳ መንግስት በኩል ተነግሯል።
ጋራንግ በዑጋንዳ ሄሊኮፕተር ሲጓዙ ነዉ አደጋዉ የደረሰዉ የእኛ እጅ የለበትም በማለት የሱዳን ባለስልጣናትም ክሱን ዉድቅ ማድረጋቸዉ አይዘነጋም።
ሙሴቪኒም ይህን መሰል ዘገባ የሚዘግቡ ከሆነ ሬድ ፔፐርን፤ ዘ ዴይሊ ኦብዘርቨርንና ዘ ዴይሊ ሞኒተር የተባሉትን የግል ጋዜጦች አግዳለሁ በማለት እያስፈራሩ ነዉ።
የዑጋንዳ ፕሬዝደንት ሆኜ ተመርጫለሁ ያሉት ሙሴቪኒ ይህን መሰሉን ተግባር የመፈፀም መብት አለኝ ሲሉም ዝተዋል።
እንደጥንብ አንሳ አሞራ ያሉ ጋዜጦችን ከእንግዲህ የምታገስበት ምክንያት አይኖርም የብዙዎች ሃዘን ለእነሱ ሰርግና ምላሽ ነዉ በመሆኑንም በአጭሩ እንዳይታተሙ አግዳለሁ። ይኸዉ ነዉ ይህን መሰሉን ስራ እንዲያቆሙ ማድረግ ወይንም እነሱን ማገድ አሉ ሙሴቪኒ።
በፕሬስ ነፃነት ጉዳይ የረባ እንቅስቃሴ በሚታይባት ዑጋንዳም በተለይ በሚያቀርባቸዉ ጠንካራ የፓለቲካ ዉይይት ዝግጅቶች በአገሪቱ የሚታወቀዉ በዴይሊ ሞኒተር ስር የሚገኘዉ K-FM የተባለዉ ራዲዮ ጣቢያም ወዲያዉ ተዘግቷል።
የፓለቲካ ዉይይቱን ያዘጋጅ የነበረዉ ጋዜጠኛ አንድሪዉ ሙኤንዳም ዋስ የሚጠራበት ፋታ ሳይጠዉ ህገ ወጥ ዘገባ ማቅረብ በሚል ክስ በቁጥጥር ስር ዉሏል።
በጋራንግ ሞት ዙሪያ ባቀረበዉ ዝግጅቱም ለሞታቸዉ ምክንያት የሆነዉ የዑጋንዳ መንግስት ካልጠፋ አዉሮፕላን ባረጀ ሄሊኮፕተር እንዲጠቀሙ በማድረጉ ነዉ ማለቱም ተጠቅሷል።
የዴይሊሞኒተር የፓለቲካ አምድ ዋና አዘጋጅ የሆነዉ ሙዌንዳ የግል ጋዜጦችን እዘጋለሁ የሚለዉን የሙሴቪኒን ማስፈራራት የተቸ ሲሆን ክሱም እንደማይመለከተዉና አግባብ እንዳልሆነ ነዉ የገለፀዉ።
ለሬዲዮና ለቴሌቪዥን ፈቃድ የሚሰጠዉ የዑጋንዳ ብሮድካስቲንግ ካዉንስል በበኩሉ K-FM ራዲዮ ሊዘጋ የቻለዉ የአገሪቱ ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ህግን የሚፃረር ዘገባ በማቅረቡ ነዉ ይላል።
ይህ እርምጃ እንደተወሰደ በአገሪቱ የሚገኙ የመብት ተሟጋቾች፤ የመገናኛ ብዙሃን ማህበራት እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ወዲያዉ ነበር ድርጊቱን ያወገዙት።
የዑጋንዳ ጋዜጠኞች ብሄራዊ ተቋም ፕሬዝደንት ሊንዳ ናቡሳይ ዋምቦካ ከፕሬዝደንቱና ከሌሎች የፓለቲካ መሪዎች በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚሰነዘረዉ ዛቻና ማስፈራራት በዑጋንዳ ዲሞክራሲ ወደፊት እንዳይራመድ የሚያሰናክልና የሚያሰጋ ነዉ በማለት አሳስበዋል።
በተለይ አገሪቱ ወደመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዓት ለመሸጋገር ጉዞ በጀመረች ማግስት ይህን መሰሉ ድርጊት መፈፀሙ አደጋ አለዉ ያሉት ዋምቦካ የመገናኛ ዘዴዎችን በመዝጋት የአገርን ደህንነት መጠበቅ እንደማይቻል ነዉ የተናገሩት።
በመቀጠልም የአገሪቱ የብሮድካስቲንግ ካዉንስል የጋዜጠኛ ሙኤንዳን ጉዳይ ከማጣራቱ ሂደት ጎን ለጎን K-FM ራዲዮ ስራዉን እንዲሰራ እገዳዉን እንዲያነሳ ጠይቀዋል።
የዑጋንዳ ጋዜጠኞች ብሄራዊ ተቋምም ሃላፊነት የጎደለዉ ስራ የሚሰሩ ጋዜጠኞችን እንደማያበረታታና እንደማይደግፍ ገልፀዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም ምክትል ፕሬዝደንት ሚካኤል ዋካቢም በበኩላቸዉ ድርጊቱን በዑጋንዳ ያለዉን ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትና መገናኛ ብዙሃንን የሚለጉም ጋዜጠኞችን የሚያሰቃይ በማለት ኮንነዉታል።
በአንፃሩም የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ናስባ ቡቱሮ የሙዌንዳ የሰነዘረዉ ሃሳብ በሱዳን ፍጅትን ሊቀሰቅስ ይችላል በማለት በባለስልጣናቱ የተወሰደዉ እርምጃ ትክክል ነዉ ብለዋል።
ምንም እንኳን ዑጋንዳ ከአንድ መቶ በላይ ራዲዮና በርካታ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲሁም ቁጥራቸዉ ቀላል የማይባል ጋዜጦች ያሉባት አገር ብትሆንም የመገናኛ ብዙሃኑና የመንግስት ግንኙነት ሰምና ወርቅ የሚባል አይደለም።
ባለፈዉ ዓመት በሰሜን ዑጋንዳ ስላለዉ የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይዘግቡ በርካታ ጋዜጠኞች በፓሊስ ተይዘዉ ነበር።
የዛሬ ሶስት ዓመትም እንዲሁ ዘ ዴይሊ ሞኒተር ጋዜጣ በሰሜን ዑጋንዳ የሚገኙት ሽምቅ ተዋጊዎች የአገሪቱን የጦር ሄሊኮብተር መትተዉ መጣላቸዉን በመዘገቡ ለአንድ ሳምንት ተዘግቶ ሰንብቷል።
በአገሪቱ በዚያዉ ዓመት የወጣዉ የፀረ ሽብር ህግ ሽብርን የሚደግፍ ዘገባ ያቀረበ ጋዜጤኛ በሞት እንዲቀጣ የሚደነግግ አንቀፅ አለዉ።