1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋማት ጉባዔ

ረቡዕ፣ መስከረም 27 2002

የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋምና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ጉባዔ ትናንት ሣምንት ከፈጀ ዝግጅት በኋላ ኢስታምቡል ላይ ተከፍቷል።

https://p.dw.com/p/K1Kn
የአደባባይ ተቃውሞ የጋረደው ጉባዔ
የአደባባይ ተቃውሞ የጋረደው ጉባዔምስል AP

አያሌ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሐብት፣ የፊናንስና የኩባንያ ተጠሪዎች በሚሳተፉበት የሁለት ቀናት ጉባዔ ዓበይቱ የውይይት ርዕስ ዓለምአቀፉ የፊናስን ቀውስና የምንዛሪው ተቋም ለአዳጊ አገሮች የበለጠ ድምጽ የሚሰጥ ሆኖ በአዲስ መልክ የመቀናጀቱ ጉዳይ ናቸው። ተደማጭነት እያጣ ሄዶ የነበረው የምንዛሪ ተቋም በፊናንሱ ቀውስ ሳቢያ በወቅቱ መልሶ ክብደት እያገኘ ሲሄድ ነው የሚታየው። በመፍትሄ ፍለጋው ረገድ ሚናው እንዲጠነክርም ተደርጓል።
የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋምና የዓለም ባንክ የሁለት ቀናት ጉባዔ ትናንት የተከፈተው ዓመጽ የተዋሃደው የአደባባይ ተቃውሞ በጋረደው ሁኔታ ነበር። ተቃዋሚዎች የባንኮችን መስታወቶች ሲሰባብሩና በርካታ አውቶሞቢሎችን ሲያቃጥሉ ከፖሊስ ጋር በደረሰ ግብግብ ብዙዎች ተይዘው ታስረዋል። የምንዛሪው ተቋም በዓለምአቀፉ የካፒታል ስርዓት ተቃዋሚዎች ዘንድ ለታዳጊ አገሮች የሚሰጠውን ዕርዳታ ጥብቅ በሆኑ የኤኮኖሚ ለውጦች ላይ ጥገኛ አድርጎ ሳለ በአንጻሩ የበለጸገው ዓለም ጥቅም አስከባሪ ሆኖ ሲታይ ቆይቷል። የተቋሙ አስተዳዳሪ ዶሚኒክ-ሽትራውስ-ካህን ባለፈው ሣምንት በኢስታምቡል ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ጥያቄዎችን በመመለስ ላይ እንዳሉ ከአንድ ተማሪ ጫማ ሲወረወርባቸው ይሄም ተቋሙ በአዳጊው ዓለም ውስጥ በጎ ዝና እንዳልነበረው የሚያመለክት ነው።

ይህን እንመለስበታለን፤ በቅድሚያ በጉባዔው ዋና ርዕስ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ላይ እናተኩርና የምንዛሪው ተቋምና የዓለም ባንክ ከወዲሁ ያስገነዘቡት በቀውሱ ለጊዜው መገታት ሁሉም ነገር አልፏል ከሚል ችኩል ድምዳሜ ላይ እንዳይደረስ ነው። እርግጥ ዓለምአቀፉ ቀውስ ተገትቷል፤ ግን ያስከተላቸው ችግሮች እንዳሉ ናቸው። እንደ IMF አስተዳዳሪ እንደ ዶሚኒክ-ሽትራውስ-ካህን ችኩልነት አደገኛ ነው።

“አሁንም በማደግ ላይ በሚገኘው ሥራ አጥነት የተነሣ በጣሙን እሰጋለሁ። ዕድገት መልሶ መቀጠሉ አንድ ነገር ነው። ግን ይህ ቀውስን አልፈናል ማለት አይደለም። እርግጥ ዕድገት መልሶ መታየቱ የመጀመሪያው መልካም ዜና ነው። ሆኖም በሥራ እጦት ማደግ ገና ለወራት ተጠምደን እንቀጥላለን። ይህ ደግሞ በማገገሙ ሂደት ላይ ለረጅም ጊዜ ጥላውን የሚያሳርፍ ጉዳይ ነው”

ሽትራውስ-ካህን አያይዘው እንዳስረዱት ለዓለም ኤኮኖሚ መልሶ ማንሰራራት ታላቁን አስተዋጽኦ ያደረገው የመንግሥታቱ የማነቃቂያ የበጀት ፖሊሲ ነው። ይሄው በችኮላ መቋረጥ የለበትም። የምንዛሪው ተቋም አስተዳዳሪ ዓለምአቀፉ የለውጥ ዕርምጃዎች የቀውሱ ምላሽ ሆነው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል። በቅርቡ አሜሪካ-ፒትስበርግ ላይ ተካሂዶ የነበረው የቡድን-ሃያ መንግሥታት የመሪዎች ጉባዔ ያስተላለፈው ውሣኔ ለዚሁ መርህ የሚሆን ነው። መቼና በምን መጠን ገቢር ይሁን፤ እርግጥ በትክክል መተንበዩ ለጊዜው ያዳግታል። ቢቀር በአጭር ጊዜ ጭብጥ ዕርምጃ መታየቱ እርግጠኛ ነገር አይደለም። የመጪውን ዓመት ሁኔታ ከፍተኛ በሆነ ጥርጣሬ ከሚመለከቱት መካከል የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ሮበርት ዞሊክም አንዱ ናቸው።

“የፊናንሱ ቀውስ ያስከተለውን ውድቀት ለማቆም ችለናል። ግን ስኬት ተገኝቷል ብሎ ለመናገር ጊዜው ገና አፍላ ነው። 2009 አስቸጋሪ ዓመት እንደሆነ ይቀጥላል። 2010ም እንዲሁ አብዛኛው የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕቅድ የሚያበቃ በመሆኑ አስተማማኝ አይደለም”

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ባለፈው ሐሙስ ኢስታምቡል ላይ ባወጣው የዓለም ኤኮኖሚ ይዞታ ዘገባ የቀውሱን መገታት በማረጋገጥ የዕድገት ትንበያውን ከፍ አድርጓል። በመረጃው መሠረት በዚህ ዓመት የዓለም ኤኮኖሚ ብቃት በ 1,1 ከመቶ የሚያቆለቁል ቢሆንም በተከታዩ 2010 እንደገና የ 3,1 በመቶ ዕድገት እንደሚታይ ነው የሚጠበቀው። ተቋሙ አፍሪቃን በተመለከተም በትንበያው ጠንቀቅ ይበል እንጂ ቀውሱ ቀደም ያሉ ጊዜያትን መሰል ጥልቅ ጉዳት አይኖረውም ባይ ነው። ዓለምአቀፉ ቀውሱ በተለይ ክፉኛ የመታው ኤኮኖሚያቸው በጥሬ ዕቃ የውጭ ንግድና በቱሪዝም ላይ ጥገኛ የሆነ የአፍሪቃ አገሮችን ነው።
ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኙት የአፍሪቃ አገሮች ከዚሁ በተጨማሪ ቀጥተኛው የግል መዋዕለ ነዋይና በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻቸው የሚልኩት ገንዘብ በሰፊው ማቆልቆሉም ፈታኝ መሆኑ አልቀረም። በምንዛሪው ተቋም ወቅታዊ መረጃ መሠረት የአካባቢው የኤኮኖሚ ዕድገት በዚህ ዓመት 1,1 ከመቶ ቢደርስ ነው። ይህ ደግሞ ካለፉት ዓመታት 5,5 እስከ ሰባት ከመቶ ዕድገት አንጻር ከባድ ውድቀት ይሆናል። እርግጥ በተከታዮቹ ዓመታት በ 2010 አራት ከመቶ፤ ከዚያም በ 2011 አምሥት ከመቶ ዕድገት ይኖራል ተብሎ ነው የሚታመነው።

የምንዛሪው ተቋም እንደሚለው አፍሪቃ ውስጥ ቀደም ባለው ጊዜ ከአንድ ቀውስ የማገገሙ ሂደት ከተቀረው ዓለም ሲነጻጸር ተጎታች ነበር። ዛሬ ግን ክፍለ-ዓለሚቱ ይበልጥ ከዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ስርዓት ጋር በመተሳሰሯ ከዓለም ኤኮኖሚ የማገገም ሂደት ተጠቃሚ ልትሆን ትችላለች። ተቋሙ በበኩሉ ቀውሱን በመታገሉ ረገድ ለአፍሪቃ አገሮች የሚያቀርበውን ብድር ከፍ አድርጓል። በያዝነው 2009 ዓ.ም. ከሶሥት ሚሊያርድ ዶላር የሚበልጥ ብድር ከሣሃራ በስተደቡብ ፈሷል። ይህም ቀደም ካለው ዓመት ሲነጻጸር በአንድ ሚሊያርድ ዶላር ከፍ ያለ መሆኑ ነው።
እርግጥ መጪው ጊዜ ተሥፋ ሰጭ ሆኖ ቢታይም ድህነትን በግማሽ ለመቀነስ የተያዘው የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ግብ ዕውን መሆኑ ግን በቀውሱ የተነሣ ተቋሙን ማሳሰቡ አልቀረም። ሌላው ቀርቶ በጥሩ ዕርምጃ ላይ በነበሩት ጋናን በመሳሰሉ አገሮች እንኳ ድህነትን የመታገሉ ዕርምጃ አዝጋሚ ሊሆን እንደሚችል ነው የሚነገረው። በአጠቃላይ የአፍሪቃ ከቀውሱ መላቀቅ በዓለም ኤኮኖሚ መልሶ የማደግ ሂደት ላይ ጥገኛ ይሆናል። በምንዛሪው ተቋም ገለጻ መሠረት እርግጥ ከሣሃራ በስተደቡብ አፍሪቃ የኤኮኖሚው ማገገም ገና ጭብጥ ሆኖ አልተረጋገጠም። በጎ ነገር ቢኖር የማቆልቆሉ ሂደት የምንዛሪው ተቋም በዓመቱ መጀመሪያ እንደፈራው ሣይሆን ዝቅ እያለ መሄዱ ነው።

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ያደቀቀውን ሲያደቅ “ሙት የተባለ ዕድሜው ረጅም” እንዲሉ ከዓመት ዓመት ትርጉም እያጣ የነበረውን የምንዛሪውን ተቋም IMF-ን በአንጻሩ መወደዱ ቢቀር ተፈላጊ ነው ያደረገው። ያ የቀድሞው ሂደት ቀጥሎ ቢሆን ሕልውናውን አደጋ ላይ እስከመጣል በደረሰ ነበር። ሆኖም የዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ መስፋፋት የተቋሙን ብድር ይበልጥ አስፈላጊ እያደረገ መሄዱ ውድቀቱን ገትቶለታል። ብድር እንዲሰጣቸው በር የሚያንኳኩት የበጀት ኪሣራ የወጠራቸው አገሮች ቁጥር ዛሬ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው።

“ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ወደ ቢዝነሱ ተመልሷል”! አስተዳዳሪው ዶሚኒክ-ሽትራውስ-ካህን እንዳሉት! በዓለምአቀፉ ቀውስ ሂደት የበጀት ኪሣራ ብርቱ ፈተና ላይ ለጣላቸው አገሮች የተሰጠው ብድር ከአሁኑ ከመቶ ሚሊያርድ ዶላር ይበልጣል። ከመጀመሪያዎቹ ተቀባዮች መካከል በባንክ ቀውስ ሳቢያ እንደ መንግሥት ተንኮታኩታ ልትወድቅ የነበረችውን አይስላንድን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ከአይስላንድ ሌላ ሜክሢኮ 47 ሚሊያርድ ዶላር፣ ፖላንድ ሃያ ሚሊያር ሲያገኙ፤ ከዚያም ከቤላሩስ እስከ ፓኪስታን፤ ከቱርክ እስከ ሩሜኒያ፤ ከሁንጋሪያ እስከ ቡልጋሪያ በርካታ አገሮች ለተቋሙ የዕርዳታ ጥሪ ሰንዝረዋል። ሌሎችም እየቀጠሉ ነው።

“ከምንዛሪው ተቋም ጋር መደራደሩን ያከብድ የነበረው የቀድሞው ሁኔታ አልፏል። ምንም እንኳ በከፊል ቢሆንም፥ ግን ጥሩ ጅማሮ ነው። ከ IMF ጋር መተባበሩ ለዓባል ሃገራቱ ጠቃሚ የመሆኑ ግንዛቤ እያየለ ነው የሄደው”

ይህ ሂደት ባለፉት ዓመታት የሚታይ ነገር አልነበረም። የምንዛሪው ተቋም የ 250 ሚሊያርድ ዶላርና የ 3,200 ቶን ወርቅ ክምችት ቢኖረውም የፊናንስ ድጋፍ ለማግኘትም ሆነ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ምክር ለመስማት ወደ ዋሺንግተን ዘልቆ በር የሚያንኳኳ አልታየም። ለዚህም ምክንያቱ የተቋሙ መድሃኒት ለተቀባዩ መሪር መሆኑ ነበር። ብድር ለመስጠት በተቋሙ የሚጣለው ቅድመ-ግዴታ በቀላሉ የሚወጡት ነገር አልሆነም። ተቀባዮቹ አገሮች ማስተካከያ የተባለ መዋቅራዊ ለውጥ ማካሄድ ነበረባቸው። የበጀት ኪሣራና የማሕበራዊ ድጎማ ቅነሣ መደበኛ ክትትል አልተለየውም። ታዲያ የተቋሙን ምክር በተከተሉ አንዳንድ አገሮች መንግሥታት ረሃብና ድህነት በቀሰቀሰው የሕዝብ ዓመጽ እስኪወጠሩ መድረሳቸው ታይቷል።

የምንዛሪው ተቋም በታዳጊው ዓለም የሃብታም አገሮች ጅራፍ ሆኖ በመቆጠር እጅጉን የተጠላ ነበር። እናም እንደ ሕንድና እንደ ቻይና ራመድ ያሉ አገሮች የዓለም ኤኮኖሚ ጥሩ ዕድገት ባሣየባቸው ዓመታት ከተቋሙ ገሽሽ ማለቱ ብዙም አልከበዳቸውም። በተቋሙ ብድር ላይ ጥገኛ አልሆኑም። ይልቁንም የጊዜውን አመቺነት በመጠቀም በዓለምአቀፉ የመዋዕለ-ነዋይ ገበዮች ላይ በርካሽና ያላንዳች ቅድመ-ግዴታ አስፈላጊውን ገንዘብ ለማግኘት ችለዋል። አንዳንድ ለምሳሌ በነዳጅ ዘይት ሐብት የታደለችውን ቬኔዙዌላን የመሳሰሉ አገሮች እንዲያውም በፖለቲካ ምክንያት የተነሣ በብድር መስጠት የምንዛሪው ተቋም ተፎካካሪ እስከመሆን ደርሰዋል። ይህ ያስከተለውም የምንዛሪውን ተቋም ምክር ጠያቂም ሆነ የራሱን ወጪ ለመሸፈን የሚያስችል ወለድ ማጣት ነው።

በ 2003 አንድ መቶ ሚሊያርድ ይጠጋ የነበረው ብድር ባለፈው ዓመት ወደ 15,6 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ ያቆለቁላል። ይህም በበጀቱ ላይ በያመቱ የ 400 ሚሊያርድ ዶላር ኪሣራ እንዲደርስ ነው ያደረገው። ችግሩን ለመወጣት ከአጠቃላይ ቁጠባ ባሻገር ሠራተኞችን መቀነስና የወርቅ ክምችትን መሸጥ ግድ ነው የሆነው። ከዚህ አንጻር ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ለሕልውናው በጅቶታል ቢባል ብዙም ማጋነን አይሆንም። ጥያቄው ወደፊት በታዳጊ አገሮች ዘንድ የጎደፈ ዝናውን ለማደስና ሚናውንም በተሻለ ሁኔታ ለመወጣት ይችላል ወይ ነው። በወቅቱ ኢስታምቡል ላይ በተያዘው ዓመታዊ ጉባዔ አንዱ የውይይት ነጥብ የራሱ የተቋሙ ጥገኛ፤ ማለት የአዳጊ አገሮች የበለጠ የውሣኔ ተሳትፎ መረጋገጥ ሲሆን የዚሁ ተሃድሶ ገቢርነት ለፍቱንነቱ ወሣኝነት ይኖረዋል።

መሥፍን መኮንን፣

ተክሌ የኋላ፣