1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም መሪዎች ጉባኤና የጦርነት ዘመቻ

ሰኞ፣ መስከረም 19 2007

ዘንድሮ የተስፋ አድማሥ ጨልሟል።ለመግለፅ በሚከብድ እርምጃ የዋሐን በመገደላቸዉ ልባችን ደምቷል።የቀዝቃዛዉ ጦርነት የጣረ ሞት ድባብ ተምልሶ በዚሕ ዘመንም እያደነን ነዉ።የአረብ አብዮት በሁከት ሲደመደም አየን።ዓለም ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ አይታዉ በታዉቀዉ ሥደተኛ፤ተፈናቃይና ጥገኝነት ጠያቂ ሕዝብ ተጥለቅላቀች---

https://p.dw.com/p/1DNIi
ምስል Reuters/Eduardo Munoz

ኢራቅ፤ ሶሪያ፤ዩክሬን፤በቦምብ ሚሳዬል ይታረሳሉ።ሶማሊያ፤ደቡብ ሱዳን፤ ናይጄሪያ፤ ሊቢያ፤ አፍቃኒስታን፤ፍልስጤም በመድፍ ጥይት ያርራሉ።ምዕራብ አፍሪቃ በኤቦላ ተሕዋሲ ያልቃል።ከድብደባ፤ጦርነት፤ ኤቦላ የራቀዉ አብዛኛዉ ዓለም በጨቋኝ ገዢዎች ክርን፤ በድሕነት፤በረሐብ፤በሽታ በትር ይሸነቆጣል፤ይሰደዳል ወይም ይማቅቃል።የዓለም መሪዎች ኒዮርክ ላይ ጠላት የሚሉትን ሊያጠፉ ዝተዉ ለተጨማሪ ጦርነት ጦር ሊያጠምቱ ወደየሐገራቸዉ ተመለሱ።ዛቻ ዘመቻዉ ኢራቅና ሶሪያ የሸመቁ ፅንፈኛ ጦረኞችን በጦርነት ለማጥፋት ነዉ።ተጨማሪ ጦርነት።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ መነሻ፤የዓለም ግርድፍ እዉነትማጣቃሻ የአዲሱ ጦርነት እንዴትነት መድረሻችን ነዉ፤

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን የድርጅታቸዉን ሥልሳ ዘጠነኛ የመሪዎች ጉባኤ ሲከፍቱ እንዳሉት ያግዙፍ አዳራሽ በየዓመቱ የተስፋ ፀዳል ይላበሳል።በመሪዎች መልካም ቃል ይሞላልም።

«በየዓመቱ በዚሕ ወቅት ይሕ አዳራሽ በተስፋ ይሞላል።የዓለም አቀፉ ድርጅት ደንብ ባቀፈዉ ተስፋ፤ ከዚሕ መድረክ የሚናገሩ መሪዎች በሚሰጡት ተስፋ እና በሚገቡት ቃል-ይሞላል።መሪዎቹ የሚገቧቸዉን ቃላት በሚሰማዉ ሕዝብ ተስፋ።»

እርግጥ ነዉ የዓለም በጣሙን የሐያላኑ ሐገራት መሪዎች የአየር ንብረት ለዉጥ ያስከተለዉን ሥጋት ለማቃለል ቅንደሚጥሩ ቃል ገብተዋል።«የአየር ንብረት ለዉጥ ዓለማችንን ከገጠሙ በጣም ከባድ ሥጋቶች አንዱ ነዉ።ለከባቢ አየር ብቻ ሳይሆን ለብሕራዊ ፀጥታችን፤ለዓለም ፀጥታ፤ ድሕነትን ለማስወገድ እና ለምጣኔ ሐብት ዕድገትም ታላቅ ሥጋት ነዉ።»

የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን።የዩናይትድ ስቴትስ፤ የፈረሳይም ሆኑ የሌሎቹ ሐያል ሐብታም ሐገራት መሪዎች ሥለአየር ንብረት ለዉጥ ጎጂነት፤ ከካሜሩን የተለየ መልዕክት አልነበራቸዉም።

UN Generalsekretär Ban Ki Moon, UN-Vollversammlung
ምስል AP

የዓለም መሪዎች በተመሳሳይ ቃላት «ታላቅ ሥጋት» ያሉትን የአየር ንብረት ለዉጥን ለማቃለል ይረዳል የተባለ ተቋም ተሰየሟል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት «አረንጓዴ የአየር ንብረት» ያለዉ ተቋም በአየር ንብረት ለዉጥ የተጎዱ የደሐ ሐገራትን ሕዝብ የሚረዳ፤ ጉዳቱ እንዳይደገም የሚያስተምርና የሚያስተባብር ነዉ።ተቋሙ የመጀመሪያ ዘመን ዕቅዱን ገቢር ለማድረግ አስር ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገዋል።

የአየር ንብረት ለዉጥን አደገኛነት እየተቀባበሉ የገለጡ፤ ያስጠነቀቁት የዓለም ሐያል ሐብታም መንግሥታት እስከ ጉባኤዉ ማብቂያ ለዚያ ድርጅት ለመስጠት ቃል የገቡት ግን 2,3 ቢሊዮን ዩሮ ነዉ።ከዚሕ ዉስጥ ሁለት ቢሊዮኑን ለመስጠት ቃል የገቡት ሁለት ሐገራት ናቸዉ።ፈረንሳይና ጀርመን።

አጠቃላዩን ሥጋት ለማቃል ደግሞ ከባቢ አየርን በመበከል የከበሩት መንግሥታት ገና ወጥ አቋም ወይም ስምምነት የላቸዉም።ጠቅላይ ሚንስትር ካሜሩንም «ለዓለም ፀጥታ» ሳይቀር አስጊ ያሉትን ሥጋት ለማቃለል ከጥር በኋላ እንስማማ ነዉ-ያሉት።«በመጪዉ ዓመት ፓሪስ ላይ ዓለም አቀፍ ስምምነት ማድረግ አለብን።ከእንግዲሕ ጉዳዩን ልናራዝመዉ አንችልም።»

ፓን እንዳሉት ቃል ተገባ።ቃሉ ካንገትነት ይሁን ካንጀት ለመለየት ግን አስተንታኝ አያስፈልገዉም።የሐያል-ሐብታሙ ዓለም መሪዎች ምዕራብ አፍሪቃን ወደ እልቂት ምድርነት የሚገፋዉን የኤቦላ ተሕዋሲ ሥርጭትን ለመግታት የሚደረገዉን ጥረት እንደሚረዱም ተስፋ ሰጥተዋል።

«ላይቤሪያ፤ጊኒ እና ሴራሊዮን የሕዝብ ጤና ሥርዓቱ ፈርሷል።የምጣኔ ሐብቱ እድገት ባስደናቂ ፍጥነት አሽቆልቁሏል።ይሕ ወረርሽኝ ካልቆመ፤ በሽታዉ በአካባቢዉ በሙሉ ሰብአዊ ቀዉስ ያስከትላል።አካባቢዉ፤ አካባቢያዊ ቀዉስ በፍጥነት ወደ ዓለም ስጋትነት የሚቀየርበት በመሆኑ ኤቦላን ማቆም የኛም ፍላጎት ነዉ።»

ዩናይትድ ስቴትስ ዜጋ ለየአንድ ሺዉ ሰዉ ፤ ሁለት መቶ አርባ ሐኪም አለዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የሚፈፀምባቸዉን ጭቆና ሸሽተዉ ላይቤሪያ የሠፈሩት አፍሪቃዉያን ጥቁሮች ለየአንድ ሺዉ ሰዉ፤ አንድ ሐኪም ማግኘት ከቅንጦት የሚቆጠር ነዉ።ኤቦላ ደግሞ ኦባማ እንዳሉት ከመኖር የማይቆጠረዉን የጤና ሥርዓት አሽመድምዶታል።

ያን የጤና ሥርዓት ለመጠገን እና የኤቦላን ሥርጭት ለማቆም ተስፋዉ ተንቆረቆረ።ተስፋዉን ገቢር ለማድረግ ትንሺቱ፤ ደሐይቱ፤ በዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ የምትማቅቀዉ ደሴቲቱ ሐገር ኩባ ሰወስት መቶ ሐኪሞችና ነርሶችን ወደ ምዕራብ አፍሪቃ ለማዝመት ወሰነች።ዩናይትድ ስቴትስ ባንፃሩ ሰወስት ሺሕ ወታደሮችን ለማዝመት ቃል ገባች።

Syrien US Kampfjet Jet US Air Force F-15E IS Luftangriff
ምስል picture alliance/dpa/Matthew Bruch

ይሕ ነዉ ቃል ተስፋዉ።ብቻ ፓን ጊሙን ያን አዳራሽ የዓለም የተስፋ መፍለቂያ ከማለታቸዉ እኩል ዓለም በቀቢፀ ተስፋ መዋጥዋንም አልሸሸጉም።«ዘንድሮ የተስፋ አድማሥ ጨልሟል።ለመግለፅ በሚከብድ እርምጃ የዋሐን በመገደላቸዉ ልባችን ደምቷል።የቀዝቃዛዉ ጦርነት የጣረ ሞት ድባብ ተምልሶ በዚሕ ዘመንም እያደነን ነዉ።የአረብ አብዮት በሁከት ሲደመደም አየን።ዓለም ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ አይታዉ በታዉቀዉ ሥደተኛ፤ተፈናቃይና ጥገኝነት ጠያቂ ሕዝብ ተጥለቅላቀች።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባንድ ጊዜ ለበርካታ ሕዝብ ምግብና ሌሎች ሕይወት አድን ቁሳቁሶች እንዲረዳ የዘንድሮንዉን ያክል ተጠይቆ አያዉቅም።»

ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዉልደትም ነዉ።የዓለምን ሠላምና ደሕንነት ለማስከበር፤ ዓለምን በጋራ ሕግና ደንብ ያስተዳድራል የተባለዉ ማሕበር ከተመሠረተ እስካሁን በተቆጠረዉ ዘመንም ዓለም ከጦርነት ግጭት ተላቅቃ አታዉቅም።የኮሪያ ጦርነት፤የቬትናም ጦርነት፤የደቡብ አሜሪካኖች ጦርነት፤ የአረብ እስራኤሎች ጦርነት፤የሕንድና የፓኪስታን ጦርነት የአፍቃኒስታን ጦርነት፤ የአንጎላ፤የሞዛምቢክ፤የዛኢር፤ የኢትዮጵያ፤የሶማሊያ ወዘተ ጦርነት እትባለ ሚሊዮኖች አልቀዋል።

የአብዛኞቹ ጦርነቶች ሰበብ ምክንያት የኮሚንስት ካፒታሊስቶቹ ሽኩቻ እንደነበር በሰፊዉ ሲነገር ነበር።ቀዝቃዛዉ ጦርነት በካፒታሊስቱ ዓለም አሸናፊነት መጠናቀቁ ከተነገረ በሕዋላም የዓለም ዘዋሪዎች ጦርነት የሚገጥሙበት ሰበብ አላጡም።ከሶቬት ሕብረት መፈረካከስ እስካሁን በተቆጠረዉ ሩብ ምዕተ-ዓመት ጦርነት ለመጫር አማላዩ ሰበብ ምክንያት ደግሞ አሸባሪነት ነዉ።

የቀድሞዉ የዩናትድ ስቴትስ ፕሬዝዳን ቢል ክሊንተን በ1998 (ዘመኑ በሙሉ እጎአ ነዉ) ናይሮቢና ዳሬ ኤ ሠላም የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎችን በቦም እንዳጋየ የሚታመነዉን የአልቃኢዳ ቡድን መሪ ኦስማ ቢን ላደንን ለመግደል ሱዳንና አፍቃኒስታን ዉስጥ ሁለት ሙከራዎች አድርገዉ ከሸፎባቸዋል።

ከዚያ በኋላ ቢላደንን ተከታትለዉ ለምን እንዳላስገደሉ ሲጠየቁ «ለጥቂት እኮ ነዉ ያመለጠኝ አሉ----» ክሊንተን «ሰላማዊ ሰዎች መሐል በመሸሸጉ ሰላማዊ ሰዎችን መግደል እሱን መሆን ነዉ ብዬ ተዉኩት።» አከሉ።

ለፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ወይም ለጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር ግን ሠላማዊ ሰዎችን የገደለዉ ቢን ላደን አይደለም ቢን ላደንንና ድርጅቱን የሚያሳድዱት ሳዳም ሁሴንም አሸባሪ ነበሩ።ሳዳም ጠፉ።ኢራቅም ጠፋች።አል-ቃኢዳ ግን አፍቃኒስታን ላይ ጠፋ ሲባል-ኢራቅ ላይ ተንሰራፋ።ቢል ላደን ተገድለዋል።

UN Vollversammlung 24.09.2014 - Barack Obama
ምስል Getty Images/A. Burton

አሸባሪ ቡድናት ከፓኪስታን እስከ ሰሜን አፍሪቃ፤ ከፊሊፒንስ እስከ ሶማሊያ፤ከየመን እስከ ማሊ፤ እስከሊቢያ፤ ከናይጄሪያ እስከ ሶሪያ እንደ አሸን የመፍላታቸዉ ሰበብ-ምክንያትን በቅጡ ያስተነተነ፤ ሁነኛ መፍትሔ እንዲበጅለት የጠየቀ በርግጥ አልጠፋ።ግን ሰሚ አላገኘም።

ምክንያቱ፤ የቀድሞዉ ጋዜጠኛና የወታደራዊ ጉዳይ ተንታኝ ጂለስ ሜሪት እንደሚሉት የምዕራቡ ፖለቲካ ከሰከነ ፖለቲካዊ መርሕ ይልቅ ስሜት ስለሚጫነዉ።«የዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የምዕራቡ ዓለም መርሕ በጣም በሕዝብ አስተያየት ላይ የተመሠረተ ነዉ።የሕዝብ አስተያየት ደግሞ በግጮቶችና ዉጥረቶች፤ በሰብአዊ ቀዉስች ምሥል ላይ የተመሠረተ ነዉ።እዉነቱን ለመናገር በየቴሌቪዥን መስኮታችን በምናየዉ ምሥል ላይ የተመረኮዘ ነዉ። ሥለዚሕ አሁን የምናየዉም በቅጡ የተብላላ ፖለቲካዊ መርሕ ሳይሆን በስሜት ክፉኛ የሚነዳ መሆኑን ነዉ።»

በ1980ዎቹ የያኔዋን ሶቭየት ሕብረት ለመምታት አፍቃኒስታን ላይ የተፈፀመዉ ስሕተት እንዳይደገም የመከሩ ነበሩ።ሁለት ሺሕ አንድ ተደገመ።የአፍቃኒስታኑ አልበቃ ያለ ይመስል በ2003 ኢራቅ ላይ አሰለሰ።የኢራቁ ወረራ ያስከተለዉ ጥፋት ጥሩ ማስተማሪያ በሆነ ነበር።አልሆነም። ሊቢያ ቀጠለች።

ፓን ጊሙን እንዳሉት ዲፕሎማሲ ሰሚም፤ሥፍራም አጣ።«ዲፕሎማሲ በሁከት በሚያምኑ ወገኖች እየተገፋ እያፈገፈገ ነዉ።ልዩነት ከነሱ መንገድ ዉጪ ሌላ የለም በሚሉ ፅንፈኞች እየተጠቃ ነዉ።የጦር መሳሪያ ቅነሳ ከጦርነት በሚያተርፉ ሻጥረኞች እዉን የማይሆን ሕልም ሆኗል።ዓለም የምትስነጣጠቅ መስላለች።ቀዉሶች እየተከመሩ፤በሽታ እየተዛመተ ነዉ።»

በሽታዉ ወባ፤ሳንባ ነቀርሳ፤ ኤድስ፤ እያለ በሽተኛን ለማስታመም፤እስከሬንን ለመቅበር ከማያስቻችለዉ በቅፅበት ከሚገድለዉ ኤቦላ ላይ ደርሷል።ሶማሊያን፤ አፍቃኒስታንን፤ ኢራቅን፤ጋዛን፤ያጠፋዉ ቀዉስ፤ሊቢያን፤ ሶሪያን፤ የመንን፤ደቡብ ሱዳንን፤ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፕብሊክን አዳርሶ ዩክሬንን እየሸራረፋት ነዉ።

አል ቃኢዳ አልጠፋም።አሜሪካ መራሹ ጦር ኢራቅን ከወረረበት ጊዜ ጀምሮ አሸባሪዎችና ሽብር የተንሰራፉባት ኢራቅ እንደ ባቢሎኖች ሥልጣኔ፤ ለዓለም አዲስ አሸባሪ ቡድን አበርክታለች።የኢራቅና የሶሪያ ወይም የሌቫንት እስላማዊ መንግሥት (ISIS)ን።«አመራር ማለት የተስፋ ፍሬን መፈለግ፤ማጽደቅና ማሳደግ ማለት።የኛ ሐላፊነት ይሕ ነዉ።የዛሬዉ የኔ ጥሪም ይሕ ነዉ።»

የተስፋዉ ፍሬ የዓለም ሐያላን ከጉባኤዉ በፊት ጀምረዉ ሶሪያ እና ኢራቅ ላይ የሚወርዱት ቦምብ-ሚሳዬል ከሆነ ፓንን በርግጥ አላሳፈሯቸዉም።እንደሚቀጥል ቃል ገቡላቸዉ።«ISISን ለመቀልበስ ወታደራዊ ሕይላችንን ለአየር ድብደባ ዘመቻችን እናዉለዋለን።ይሕንን አሸባሪ በምድር የሚወጉ ሐይላትን እናሰለጥናለን፤እንስታጥቃለን።የገንዘብ ምንጫቸዉን ለመበጣጠስ እንሰራለን።ቡድኑን ለመቀየጥ ተዋጊዎች ከአካባቢዉ እና ወደ አካባቢዉ እንዳይሔዱ እናግዳለን።ከአርባ የሚበልጡ መንግሥታት ይሕን ጥምረት እንደሚቀየጡ አስታዉቀዋል።ዛሬ ዓለም ይሕን ጥረት እንዲቀየጥ እጠይቃለሁ።»

ለፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ የቀድሞዋ ኢራቅ፤ኢራንና ሰሜን ኮሪያ አንድ ስም ነበራቸዉ።«የሰይጣን ዛቢያ» የሚል።የዓለም ታላቅ የሰላም ሽልማት ኖቤል ተሸላሚዉ ኦባማም-ለስማቸዉ መጠሪያ ሥም አገኙ።«ከዚሕ ከለየለት ሰይጣን ጋር ድርድር የለም።»

Symbolbild Deutsche Frauen im Syrienkrieg
ምስል picture-alliance/landov

ኢራቅና ሶሪያ የሸመቁ አሸባሪዎችን ይዞታ ለመደብደብ አንዲት ዩናይትድ ስቴትስ በአንድ ቀን ከስባት እስከ አስር ሚሊዮን ዶላር ታወጣለች።በዓመት ከ2,5 ቢሊዮን እንሰከ 3,5 ቢሊዮን ዶላር ማለት ነዉ።ድፍን ዓለም በሽታን ለመከላከል የዚሕን ሩብ አያወጣም።አንዲት ዮናይትድ ስቴትስ ለአፍቃኒስታኑ ጦርነት በአንድ ዓመት ብቻ 77,7 ቢሊዮን ዶላር ከስክሳለች።ዓለም ሐብታም ናት።ደግ።ግን ለጦርነት።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ