1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ባንክና የዓለምአቀፉ ገንዘብመርሕ ድርጅት ዓመታዊ ጉባኤ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 4 1997

የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ ገንዘብመርሕ ድርጅት/ኣይኤምኤፍ ከቅርብ ጊዜ በፊት ዋሽንግተን ውስጥ ያካሄዱት የጋራው ዓመታዊ ጉባኤ፥ እጅግ ድሆቹ የሦሥተኛው ዓለም ሀገሮች የተሸከሙት ከባዱ የውጭ እዳ ለሚቃለልበት ጥያቄና የነዳጅ ዘይት ዋጋ አለቅጥ እየተወጣጣ ለተገኘበት ሂደት ነበር የተለየውን ትኩረት የሰጠው።

https://p.dw.com/p/E0fI

በእንዱስትሪያዊው ዕድገት የበለፀጉት መላው መንግሥታት ድሆቹ የሦሥተኛው ዓለም ሀገሮች የተሸከሙት ከባዱ የውጭ እዳ መቃለል እንዳለበት በመሠረቱ ቢስማሙበትም፣ በእዳ ቅነሳው ይዘትና አሠራር ረገድ የተለያየ አስተያየት ነው የሚንፀባረቅባቸው። ዓለምአቀፉ ገንዘባዊ ድርጅት/ኣይኤምኤፍ ያስቀመጠው የወርቁ ክምችት አዲስ ግምገማ ተደርጎበት የተመዘገበው ትርፍ ለእዳ ስረዛው ዓላማ እንዲውል ብሪታንያ ያቀረበችውም ሐሳብ በቂ ድጋፍ ሳያገኝ ቀርቷል። አንዳንድ ሀገሮች ዓለምአቀፉን ገንዘባዊ ድርጅትና የዓለም ባንክን በመሳሰሉት ዓለምአቀፍ ድርጅቶች አኳያ ያለባቸው እዳ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ ዩኤስ አሜሪካ ያቀረበችውም ሐሳብ ድጋፍን ለማግኘት አልበቃም። ጉዳዩን የሚመለከተው ኮሚቴ ስለ ሥርነቀሉ የእዳ ማቃለያ ርምጃ ገና ብዙ የዝግጅት ሥራ አስፈላጊ እንደሚሆን ነው የገለፀው።

የዓለም ባንክ ሊቀመንበር ጄምስ ዎልፈንዘን በዓመታዊው ጉባኤ ፍፃሜ ላይ በሰጡት መግለጫ፥ በሽብርፈጠራ አንፃር የሚደረገው ትግል በሦሥተኛው ዓለም ውስጥ በድህነት አንፃር የሚካሄደውን ዘመቻ ማዳከም እንደሌለበት በጥብቅ ነው ያስገነዘቡት። በእርሳቸው አመለካከት መሠረት፥ የድህነት ውገዳ በዓለም ውስጥ ለሚኖረው እርጋታና ሰላም ወሳኝ ነው የሚሆነው።

በዚያው በዋሽንግተኑ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ የሰባቱ ዓበይት እንዱስትሪ-ሀገራት ገንዘብ-ሚኒስትሮችና የማዕከላይ ባንክ ገዥዎች ያጎሉት የጋራው መግለጫ፥ ነዳጅዘይት ላኪዎቹ ሀገሮች የምርታቸውን መጠንና አቅርቦት በማበርከት የዋጋውን ምጥቀት እንዲገቱት በጥብቅ ነው የሚጠይቀው። ሰሞኑን እንደታየው፥ የየበርሜሉ ነዳጅዘይት ዋጋ የሃምሳ ዶላሩንም ድንበር እያለፈ የሚመጥቅበት ሁኔታ ለዓለም ኤኮኖሚ ሂደት ከባድ እንቅፋት ነው የሚሆነው። በአንድ በኩል የነዳጅዘይት ላኪዎቹ ሀገሮች ድርጅት ኦፔክ የምርቱን አቅርቦት ለቀቅ እንዲያደርገው፣ በሌላው በኩል ደግሞ በሸማቾቹ እንዱስትሪ-ሀገሮች ውስጥ የሚጋነነው የኃይል ምንጭ ፍጆታ እንዲቀነስ እና ገበያዎችን የሚያተራምሱት አረጠኞችም አድራጎት እንዲወገድ ጉባኤው ጥብቅ ማሳሰቢያ ነው ያቀረበው።

የቡድን-፯ ገንዘብሚኒስትሮችና የማዕከላይ ባንክ አዛዦች አሁን ሦሥት ጥያቄዎችን በማጉላት በመጣቂው የምድርዘይት ዋጋ ላይ ተጽእኖ ለማሳረፍ ይሻሉ፥ ይኸውም--አንደኛ ነዳጅዘይት አምራቾቹ ሀገሮች አቅርቦቱን ተመዛዛኝ እንዲያደርጉት ይጠየቃሉ። ግን፣ በታዛቢዎች አመለካከት መሠረት፥ የምድርዘይቱ ተጠያቂነት ከአቅርቦቱ መጠን እየላቀ መገኘቱ ነው ችግሩ። ከዚህም በላይ በማዕከላይ ምሥራቅ፣ በናይጀሪያ እና በሩሲያ ያሉት ቀውሶች ገበያውን ይጫኑታል።

ሁለተኛው የቡድን-፯ ማሳሰቢያ በራሱ ዙሪያ ያሉትንም ጨምሮ ነዳጅዘይት ሸማቾቹን ሀገሮች ነው
የሚመለከተው። የሰባቱ ዓበይት እንዱስትሪሀገራት ገንዘብሚኒስትሮች በተለይም በዓለም እጅግ ዋንኞቹ የምድር ዘይት ፍጆተኞች የሆኑትን ሁለቱን ሀገሮች ዩኤስአሜሪካንና ቻይናን በማመላከት ያጎሉት ማሳሰቢያ፥ እነዚያው ሀገሮች የነዳጅ ምንጭን የምርታማነት ኃይል በይበልጥ እንዲያጠናክሩት ይጠይቃል። በመግለጫው መሠረት፣ ዘንድሮ በዓለም ውስጥ የሚኖረው የነዳጅ ፍጆታ መጠን በተድላው ኑሮ ዕድገትና በዳባሪው እንዱስትሪያዊ ሂደት ምክንያት በ3.2 በመቶ የሚያሻቅብ ይሆናል፤ ይኸው የነዳድጅ ፍጆታ ምጥቀት ካለፉት ሃያ ዓመታት ወዲህ አቻ የለውም ነው የሚባለው። ሆኖም፥ የኃይል ምንጭ ፍጆታ ቁጠባና ጠንቃቃ አዋዋል ከታከለበት የፍጆታው ምጥቀት የሚገታ እንደሚሆን የገንዘብ ሚኒስትሮቹ መግለጫ ያስገነዝባል። በሌላው በኩል ግን የምድርዘይት ፍጆታ እየተቀነሰ ለአማራጩና ለታዳሹ የኃይል ምንጭ የበለጠው ትኩረት እንዲሰጥ የሚጠይቀው የብዙዎች ማሳሰቢያ በቡድን-፯ ገንዘብሚኒስትሮች መግለጫ ውስጥ ቦታ አልተሰጠውም።

ሦሥተኛው የቡድን-፯ ማሳሰቢያ ነጥብ በነዳጅዘይቱ ገበያ ላይ አረጠኞች ዋጋን የሚያመሰቃቅሉበት አድራጎት እንዲገታ የሚጠይቅ ነው። “የምድር ዘይት ገበያዎች እንከንአልባ ሂደት ለሸማቾቹም ሆነ ለአምራቾቹ እጅግ አስፈላጊ ነው” ይላል የገንዘብ ሚኒስትሮቹ ማስገንዘቢያ። ማዕከላዊ መሥሪያቤቱ በፓሪስ የሚገኘው ዓለምአቀፉ የኃይል ምንጭ ተመልች ተቋም ስለነዳጅ ዘይት ገበያዎች የሚቀርቡትን መረጃዎች ግልጽነት እንዲያሻሽለው ተጠይቋል። ግን ከሚወጣጣው የነዳጅ ዘይት ዋጋ ትርፋቸውን ለማመንጨት የሚዋትቱትን የፊናንስ አረጠኞች ለመግታት የሚቻል መስሎ አይታይም።


ድሆቹ የሦሥተኛው ዓለም ሀገሮች የተሸከሙት የውጭው ዕዳ መቶ በመቶ እንዲሰረዝላቸው በዓመታዊው የዓለም ባንክና የዓለምአቀፉ ገንዘባዊ ድርጅት ጉባኤ ላይ የቀረበው ሐሳብ የተለያዩትን አቋሞች ሊያቀራርብ አልበቃም፤ ግን ይኸው የዕዳ ማቃለያ ጥያቄ በተለይ የሁለቱን ዓበይት እንዱስትሪ-ሀገሮች--የብሪታንያንና የዩኤስ-አሜሪካን ድጋፍ አግኝቷል።

የዓለምአቀፉ ገንዘብ-መርሕ ድርጅት ሥራ-አስኪያጅ ሮድሪጎ ደ ራቶ በዓመታዊው ጉባኤ ፍፃሜ ላይ ለጋዜጠኞች የሰጡት መግለጫ፥ ጉባኤው ተጨባጭ ውጤት ባያስገኝም ከእዳ ማቃለያው ርምጃ ጎንለጎን የልማት ርዳታውም ይዘት እንዲጨመር በሚያስፈልግበት ጥያቄ አኳያ የተካሄደው ውይይት ፍሬአማ እንደነበር ያስገነዝባል። ገንቢው ውይይት ወደ ፖለቲካዊው ወሳኝነት የሚ,መራ እንደሚሆን ነው ተሥፋ የሚደረገው። የዓለም ባንክ ሊቀመንበር ጄምስ ዎልፈንዘን ደግሞ፥ የዘንድሮው ዓመታዊ ጉባኤ በእዳ ቅነሳው ጥያቄ ረገድ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘት የተሳነው፣ ውሳኔው በሚመለከታቸው ሀገራት አኳያ የፖለቲካው በጎፈቃድ በመጓደሉ ሆኖ ነው የሚያዩት። የድሆቹ ሀገሮች ዕዳ ጥያቄ በዓመታዊው ጉባኤ ላይ ጉልሁን ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ ያስቻሉት ብዙ የኤኮኖሚ ጠበብትና ግብረሠናይ ድርጅቶች ደግሞ፣ በዚሁ የእዳ ማቃለያ ጥያቄ ረገድ አንዳች እመርታ ባለመታየቱ እጅግ እንዳዘኑ ነው የገለፁት።

የዓለም ባንክ “ከባድ እዳ ተሸካሚዎቹ ድሆች ሀገራት” ብሎ የመዘገባቸው ፵፩ መንግሥታት--ከእነዚሁም መካከል ፴፫ቱ በአፍሪቃ--የተከመረባቸው ጠቅላላው የውጭ እዳ አሁን ፪፻፳ ሚሊያርድ ዶላር ነው የደረሰው። ግን፣ ሁኔታውን የሚከታተሉት ታዛቢዎች እንደሚያስገነዝቡት፣ ዛሬ አለቅጥ ከባዱን የውጭ እዳ የተሸከሙት ድሆቹ ሀገራት ችላ እየተባሉ ፩፻፳ ሚሊያርድ ዶላር እዳ ላለባት ኢራቅ ነው የበለጠው ትኩረት የሚሰጠው። ግና ከእነዚያው ድሆቹ ሀገሮች መካከል ብዙዎቹ እዳውን የከመሩት ልክ የቀድሞው የኢራቅ ፕሬዚደንት ሣዳም ሁሴን እንዳደረጉት ሁሉ በአምባገነኖች ተግባር መሆኑ መታወስ ነበረበት ይላሉ የድሆቹ ሀገራት አጋሮች። የሆነ ሆኖ፣ ድሆቹ ሀገሮች የእዳ ምኅረት ቢደረግላቸው እንኳ፣ ከዚሁ የእዳ ምኅረት የሚቆጥቡት ገንዘብ የልማት ግባቸውን ለመፈፀም አያስችላቸውም፤ ከእዳ ቅነሳው ርምጃ ጎንለጎን ተጨማሪውም የልማት ርዳታ ነው አስፈላጊ የሚሆነው፣ ይህ ሲሆን ብቻ ነው እጎአ በ፪ሺ ዓ.ም. በዓለሙ ድርጅት ዘንድ ወደተተለሙት የአሠርቱ ምእት ልማት-ግቦች ለመቃረብ የሚቻለው ይላል ለድሆቹ ሀገሮች የሚቆረቆሩት ዓለምአቀፍ ተቋማት ማስገንዘቢያ። እንግዲህ አሁን የተነቃቃው አዎንታዊው ዕዳነክ ውይይት በተጨባጩ ርምጃ ይደገፍ እንደሆን የሚታወቀው፥ የውሳኔው ባለቤት የሆኑት ዓበይቱ የቡድን-፯ እንዱስትሪ-ሀገሮች በመጭው ሐምሌ ዓቢዩን ጉባኤ በሚከፍቱበት ወቅት ነው።