1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ባንክ፣ ዓለምአቀፉ የልማት ዕርዳታ ፖሊሲና ሙስና

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 12 1998

የልማት ዕርዳታ ክፍፍል ጉዳይ በተነሣ ቁጥር በየጊዜው ተደጋግሞ የሚነገረው አብዛኛው ገንዘብ በሙስና ባክኖ እንደሚጠፋ ነው። የተለያዩ የልማት ፕሮዤዎች ከሞላ-ጎደል ከወረቀት አልፈው ተግባራዊ አይሆኑም። ሃቁ ዕርዳታው ለድሆች ከመድረስ ይልቅ ወደ ጥቂት ባለሥልጣናት የባንክ ሂሣብ መሹለኩ ነው።

https://p.dw.com/p/E0dp
የዓለም ባንክ ባለሥልጣናት
የዓለም ባንክ ባለሥልጣናትምስል AP

ባለፉት አሥር ዓመታት ጸረ-ሙስና ትግል ሲያደርጉ ከቆዩት ወገኖች መካከል የዓለም ባንክም ይገኝበታል። “በልምድ የሚታወቀው የሙስና ትርጉም ይፋ ሥልጣንን ተጠቅሞ ያላግባብ በግል መካበት የሚል ነው። ግን ይህ አገላለጽ በዛሬው ጊዜ አሻሚና አስቸጋሪ ነው። ድርጊቱ ሕገ-ወጥ ነበር ከተባለ እርግጥም ሙስና ነው። በአንጻሩ ሕጋዊ የሚባል ከሆነ ግን ሙስና ተብሎ ሊገለጽ አይችልም። ይህ የሙስና አተረጓጎም እንግዲህ አጠቃላዩን ,ሁኔታ በተሟላ መልክ አይገልጽም ማለት ነው”

ይህን የሚሉት በዓለም ባንክ ተቋም ውስጥ የዓለምአቀፍ አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ ዳኒዬል ካውፍማን ናቸው። ካውፍማን በዴሞክራሲ ግንባታና በልማት ጉዳይ የበርካታ መንግሥታት አማካሪ ሲሆኑ ጸረ-ሙስና ዕቅዶች ተግባራዊ በሚሆኑበት ሁኔታ ሲያተኩሩም ብዙ ዓመታት አሳልፈዋል። በዓለም ባንኩ ባለሥልጣን ዕምነት ሙስናን ስኬታማ በሆነ መንገድ መቋቋም የሚቻለው በአንድ አገር የተሻለ ሕግ ሲኖር፣ የበለጠ የአሠራር ግልጽነትና በጎ አስተዳደር ሲሰፍን፤ በአጠቃላይ ሂስና ቁጥጥርን የማይቀናቀን የዴሞክራሲያዊ ሕብረተሰብ መዋቅር ሲገነባ ይሆናል። ግን ይህ ዛሬ ለታዳጊው ዓለም ሕዝብ የሕልም እንጀራን ያህል ነው።

እርግጥ በሙስና ለተዘፈቁ መንግሥታት ገንዘብ በመስጠቱና በልማት ብድር ምዝበራ የተነሣ የዓለም ባንክም ራሱ በየጊዜው የወቀሣ ዒላማ መሆኑ ይታወቃል። ተቋሙ ለአሠርተ-ዓመታት በየጊዜው በየግል ኪሱ ለፈሰሰው ገንዘብና በዓለምአቀፍ ደረጃ በሕገ-ወጥ መንገድ ለካበቱ ገዢዎች የቅንጦት አናኗር ዘይቤ ተጠያቂ ነው። ይሁንና የዓለም ባንክ ከአሥር ዓመታት ወዲህ የራሱን ጸረ-ሙስና ዘርፍ ከፍቶ በጉዳዩ አርአያ ለመሆን ሲጥር ቆይቷል።

ከዘርፉ መሪዎች አንዱ ጆናታን ሻፒሮ እንደሚያስረዱት ትግሉ ቀላል ባይሆንም ቢቀር በመለሥተኛ ሥልጣን ደረጃ ፍሬ መታየቱ አልቀረም። በሙስና ድርጊት የተደረሰባቸው የባንኩ የራሱ ሠራተኞችም እስከመባረር ደርሰዋል። ቢሆንም ትግሉ ከበፊቱ ይልቅ በመወሳሰቡ እንደቀድሞው ቀላል አልነበረም። የዓለም ባንክ ውስጣዊ ጸረ-ሙስና ዘርፍ በአሁኑ ጊዜ ሥራውን ከማሳደድ ወደ መከላከልና ወደ ማንቃት ደረጃ እያሸጋገረ ነው። የባንኩን የውስጥ ሙስና የሚከታተል የቤቱ ዘርፍ ሲኖር ለውጭ ጉዳይ ተጠሪ የሆነ በዓለም ባንክ ድጋፍ ጭምር የሚራመዱ ፕሮዤዎች ከሙስናና ከማጭበርበር ድርጊት ነጻ መሆናቸውን የሚያጣራ ራሱን የቻለ ክፍልም እንዲሁ አለ።

የዓለም ባንክ የሙስና ጉዳይ ዘርፍ ቀድሞ በጅምሩ በተግባር የሚሰማራው የሙስና ድርጊት ለመፈጸሙ ጠንካራ ጥርጣሬ ሲኖር ብቻ ነበር። ዛሬ ግን አንድ ፕሮዤ ሲወጠን ጀምሮ ዘወትር የባንኩ ተግባር ተሳታፊ ነው። “ዛሬ የምናየው ከግንዛቤ ወደ ተግባር መራመድ የደረስንበትን ሁኔታ ይመስለኛል። ከባልደረቦቻችን ጋር በመሆን ፕሮዤዎችን ገና ከዕቅድ ደረጃቸው አንስተን እንከታተላለን። የተወሰኑ ፕሮዤዎችን መርምረን አስተያየታችንን እንድንሰጥ መጠየቃችንም የተለመደ ነው” ይላሉ ሚስተር ሻፒሮ!
በአሁኑ ጊዜ የዓለም ባንክን ብድር ለመቀበል የሚፈረሙ ውሎች በመሠረቱ ጸረ-ሙስና ግዴታዎችን በውስጣቸው የጠቀለሉ ናቸው። ግን ይህም ሆኖ በርካታ ታዳጊ አገሮች ከምዝባራ በመቆጠቡ ረገድ ሙስናን በሚታገለው ዓለምአቀፍ ድርጅት በ Transparency International ዝርዝር ላይ ቁልቁል ተሰልፈው ነው የሚገኙት። ድርጅቱ ሲበዛ በሙስና የተዘፈቁ ብሎ በተለይ ቀይ ምልክት ያደረገባቸው አገሮች ከአፍሪቃ እስከ እሢያ፤ ከላቲን አሜሪካ እስከ ቀድሞ የሶቪየት ሬፑብሊኮች በርካቶች ናቸው።

የዓለም ባንክ እንግዲህ ባለፉት አሥር ዓመታት የተወሰነ ጥረት ቢያደርግም ዕርምጃው አዝጋሚ እየሆነ ነው የመጣው። ወደፊት ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል ማለት ነው።