1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ንግድ ድርድርና ታዳጊው ዓለም

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 26 1998

የታዳጊ አገሮችን ልማት ለማፋጠን ታስቦ የተጸነሰው የዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ የንግድ ማለዘቢያ ድርድር እስካሁን የተፈለገውን ውጤት አላስገኘም። ለዚህም ብዙ ምክንያቶች አሉት። በተለይ ዋነኛው ግን የበለጸጉት መንግሥታት ችግሩን ለማለዘብ በቂ አስተዋጽኦ አለማድረጋቸው ነው።

https://p.dw.com/p/E0dn
የዓለም ንግድ ድርጅት መለያ ዓርማ
የዓለም ንግድ ድርጅት መለያ ዓርማ

የዓለም ንግድ ድርድር ተሥፋ ሰጭ በሆነ መልክ ማሰሪያ ሊያገኝ አለመብቃቱ የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም የልማት ዕቅድ ከግቡ በማድረሱ በኩልም ጎጂ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የብዙዎች ታዛቢዎች ዕምነት ነው። የድርድሩ ፍሬ ቢስነት በታዳጊ አገሮች ልማት ላይ ከባድ ግፊት እንደሚኖረው ዓለምአቀፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ኦክስፋም-ኢንተርናሺናል ከአንድ ሣምንት በፊት አስጠንቅቆ ነበር።

ብሪታኒያ ላይ ተቀማጭ የሆነው ዓለምአቀፍ ድርጅት የኦክስፋም ኢንተርናሺናል አስተዳዳሪ ጀረሚይ ሆብስ በዓለም ንግድ ድርድር መጓተት ጉዳይ ሃብታም አገሮችን ከታዳጊዎቹ ብዙ እየጠየቁ ራሳቸው ግን የሚሰጡት እጅግ ጥቂት ነው ሲሉ ተጠያቂ አድርገዋል። ሆብስ ባለፈው ሣምንት ለጋዜጠኞች እንዳስረዱት ይህ የበለጸጉት መንግሥታት የያዙት ዘይቤ ለውድቀት የሚዳርግ ነው። የታዳጊ አገሮች አምራቾችን እጅግ የሚጎዳ፣ የሥራ አጡን መንጋ ሲበዛ የሚያበራክትና ለእርሻው ዘርፍ አዲስ የውጭ ገበያ ዕድል እንዳይፈጠርም መንገድ የሚዘጋ ነው የሚሆነው።

ኦክስፋም 149 ዓባል መንግሥታትን ያቀፈው የዓለም ንግድ ድርጅት በዚህ መሰሉ የድርድር ሂደት ድሆች አገሮችን መጥቀሙን አጠያያቂ ያደርጋል። በመሆኑም ሰሞኑን ባወጣው አዲስ ዘገባ እንዳመለከተው ታዳጊ አገሮች አሁን ካለው የድርድር ይዘት የሚወጣ ስምምነትን መፈረም የለባቸውም። “የዶሃ የልማት አጀንዳ” በሚል ይፋ መጠሪያ የሚታወቀው የዓለም ንግድ ድርጅት የድርድር ዙር የተጀመረው ከአምሥት ዓመታት ገደማ በፊት፤ በ 2001 ዓ.ም. ነበር። ዓላማው በተለይ የበለጸጉትን መንግሥታት የቀረጥና የድጎማ ፖሊሲ መሰናክሎችን በማስወገድ ንግድን ለታዳጊ አገሮች ልማት መጠቀም እንደነበርም አይዘነጋም።

ግን እስካለፈው 2004 ዓ,ም, ግቡን ዕውን ከሚያደርግ ከአንድ ዓለምአቀፍ ውል ለመድረስ የጣለው ዕቅድ ገቢር አይሆንም። ድርድሩ በሃብታምና ድሆች አገሮች አለመግባባት የተነሣ ከተጣለለት ጊዜ እንዲያውም አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ነበር የተቋረጠው። እርግጥ ከዚያን ወዲህ ድርድሩን ሕያው አድርጎ ለማቆየት ከአሜሪካም ሆነ ከአውሮፓ ሕብረት አኳያ አንዳንድ ማሻሻያ የተባሉ ሃሣቦች በየጊዜው መሰንዘራቸው አልቀረም።

በንግድ ፖሊሲያቸው የታዳጊ አገሮች ገበሬዎችን የፉክክር አቅም በማዳከም የተወቀሱት ሁለቱ ወገኖች፤ ዋሺንግተን ለአሜሪካ ገበሬዎች የምትሰጠውን የእርሻ ድጎማ እንደምትቆርጥ ቃል ትገባለች፤ የአውሮፓ ሕብረትም ለታዳጊ አገሮች የእርሻ ምርት የሚጠይቀውን ታክስ እቀንሣለሁ ይላል። እርግጥ ይህ በብዙዎቹ ታዳጊ አገሮች በኩል በስፋቱ በቂ ሆኖ አልታየም። ከዚህም በላይ ሃብታሞቹ አገሮች በምላሹ ለምሳሌ ብራዚልንና ሕንድን የመሳሰሉት ራመድ ያሉ ለሚ አገሮች በአንዱስትሪ ምርቶቻችን ላይ ያስቀመጡትን የቀረጥ መሰናክል ማንሣት ይርባቸዋል ባዮች ናቸው።

እነዚሁ አራት ወገኖች ማለት አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ ብራዚልና ሕንድ ባለፈው ታሕሣስ ወር ሆንግኮንግ ላይ ተካሂዶ በነበረው የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባዔ ቢቀር ድርድሩን እስከዚህ ዓመት መጨረሻ ለማጠቃለል ከስምምነት ቢደረስም ተጻራሪ አቋሞቻቸውን ይዘው እንደቀጠሉ ናቸው። የአውሮፓ ሕብረት በዚሁ ጉባዔ ላይ ለውጭ የእርሻ ንግዱ የሚሰጠውን ድጎማ እስከ 2013 ዓ.ም. እንደሚቀንስ ቃል ገብቷል።
ጉባዔው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በዓለም ላይ የድሃ ድሃ የሚባሉትን አገሮች የሚረዳ የተለየ የንግድ ስምምነት ማስፈኑም አልቀረም። ሆኖም ግን ለታዳጊው ዓለም የቆሙ ተሟጋቾች እነዚህ አገሮች በዚህ ቃል የሚያገኙት ጥቅም በሚገባ ግልጽ አልሆነም ባዮች ናቸው። የኦክስፋም የንግድ ጉዳይ አስተንታኝ ቬርማ ሣመር እንደሚሉት በዓለም ንግድ ድርድር ሂደት በጅምሩ የተነሣው ልማት የሚለው ቃል የሚገባውን ትኩረት አላገኘም። ክብደቱን አጥቷል፤ ሆን ተብሎ ወደ ጎን የተገፋ ነገር ነው። የዶሃ የድርድር ዙር እንግዲህ የተሳሳተ አቅጣጫ ይዞ እያመራ መሆኑ ነው።

ባለፈው ሣምንት የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል መንግሥታት ባለፈው ዕሑድ ለተጠናቀቀው ሚያዚያ ወር መጨረሻ በቀረጥ ቅነሣው አኳያ ካሰቡት ስምምነት ሊደርሱ አለመቻላቸውን አስታውቀው ነበር። ሆኖም በሌላ በኩል በሚቀጥለው ሐምሌ ወር ሁለተኛ አጋማሽ ዘላቂ የዶሃ ዙር ውልን እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ለመስማማት ባላቸው ውጥን የጊዜ ገደብ ችግሩን ለመፍታት በመጪዎቹ ሣምንታት የሚጥሩ መሆናቸውን ቀደምት ባለሥልጣናት መጠቆማቸው አልቀረም።

ለማንኛውም በኦክስፋም ዘገባ መሠረት በወቅቱ በተለይ ከታዳጊው ዓለም አንጻር ለውል ከመቻኮል መቆጠቡ የሚመረጥ ነው። ድርድሩን በሁለትና በሶሥት ዓመታት አራዝሞ ከተሻለ ውጤት መድረሱ ይመረጣል። እርግጥ ይህ መጓተት የበለጸጉት መንግሥታት ገበዮቻቸውን ለታዳጊው ዓለም ምርቶች በመዝጋት የሚያደርጉትን የንግድ ገደብ መልሶ ሊያጠናክር የሚችል ነው። ምዕራባውያኑ መንግሥታት ከድሆቹ አገሮች በተናጠልና በቀጥታ የመደራደር ዕርምጃን ሊወስዱ ይችላሉ። ይህ ደግሞ የታዳጊዎቹን አገሮች የሕብረት ሃይል ሊያዳክም የሚችል እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። ቢሆንም ለስምምነት ሲባል ብቻ የማይረባ ስምምነት ከማድረግ የተሻለው መንገድ ነው።

የታዳጊው ዓለም ችግር በዓለም ንግድ ድርድር ዙሪያ የሚታየው ሚዛን ያልጥበቀ የበለጸጉት መንግሥታት ፖሊሲ ብቻ አይደለም። በአብዛኞቹ አገሮች በተለይም በአፍሪቃ የሕብረተሰብ የልማት ዕድልን አንቆ የያዘው ዋናው ችግር ቤት-ሰራሽ ሆኖ ነው የሚገኘው። የበጎ አስተዳደር እጦት፣ የሕብረተሰብ ፍትህ መጓደልና በተለይ በባለሥልጣናት ዘንድ ሥር የሰደደው ሙስና ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኙት የአፍሪቃ አገሮች ድህነትን በግማሽ ለመቀነስ በዓለም ሕብረተሰብ የተያዘው የሚሌኒየም ውጥን በጊዜው ዕውን እንዳይሆን ከአሁኑ ከንቱ ተሥፋ አድርጎታል።
ጉዳዩ የመፍትሄ ያለህ የሚያሰኝ ነው። በወቅቱ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይህንኑ ችግር እንዲቋቋሙ ለመደገፍ የተወጠነ አዲስ “Global Integrity Alliance” ወይም ዓለምአቀፍ የሥነ-ምግባር ሕብረት የተሰኘ አካል ለመመሥረት ከዚህ ቀደም ቀርቦ የነበረ ሃሣብን ገቢር ለማድረግ እየተሞከረ ነው። አዲሱ ሕብረት ከንግዱ ዘርፍ፣ ከዓለምአቀፍ ተቋማትና ከመንግሥታት እንዲሁም ከመንግሥት ነጻ ከሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ የሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ጉዳይ አዋቂዎችን እንዲያቅፍ ይታሰባል። ዓላማውም ብቃትን በማዳበር፣ በምርምር፣ በውይይት፣ በሽርክናና ጸረ-ሙስና ጥረቶች ሁኔታውን ማሻሻል ነው።

ሃሣቡ የተጸነሰው በዓለምአቀፍ ደረጃ ለሕብረተሰብ መሪዎች፣ ሲቪክ ማሕበረሰብ ተወካዮች፣ መንግሥታትና ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች የሚያደርጉትን ጥረት ለማራመድ መደገፍ፣ ማማከርና ጥብቅና መቆም ጭምር ነው። እነዚህም የሕብረተሰብ አገልግሎትን ደረጃ ማሳደግ፣ ለበጎ አስተዳደር መቆም፣ ለለውጥ ዕውቀትና ድጋፍ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

ሕብረቱን የማቆሙ ሃሣብ መጀመሪያ የተጸነሰው ከሁለት ዓመታት በፊት ቱርክ ውስጥ በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ ነበር። ግን ጽንሰ-ሃሣቡ ቅርጽ መያዝ የጀመረው በቅርቡ በብሪታኒያ-ኦክስፎርድ በተዘጋጀ የሥነ-ምግባር መድረክ ላይ ነበር። መድረኩ ይህ የሥነ-ምግባር አራማጅ ሕብረት ምን ባሕርይ ሊኖረው እንደሚችል፣ ምን መሥራት እንደሚገባውና እንዴት? ጭብጥ መልክ የያዘበት ነበር ለማለት ይቻላል።

ቅርጹ፣ አመራሩና ተግባሩ እርግጥ ገና ወደፊት የሚታይ ነው። ዋሺንግተን ላይ ተቀማጭ የሆነው ነጻ የሥነ-ምግባር ምንጭ ማዕከል የኦክስፎርዱን ስብሰባ ውጤትና ጽንሰ-ሃሣብ መርምሮ ለተሳታፊዎቹ የሚሰራጭ የውይይት ሰነድ ያረቃል። የሚታመነው እስካሁን ያለው መቆጣጠሪያ ዘዴ መቀጠሉ አስፈላጊ ቢሆንም በቂ አይደለም የሚል ነው። የሕብረተሰብ አገልግሎት መሠረት ሕብረቱ በሚያስበው መንገድ በሚገባ ቢጠናከር ወደተሻለ የልማት ውጤት እንደሚመራ ይጠበቃል።

የዓለም ባንክ እንደሚያስገነዝበው ምንም እንኳ ባለፉት ጥቂት አሠረተ-ዓመታት በዚህ መስክ ዕርምጃ መደረጉ ባይቀርም ሥነ-ምግባርን ለማራመድና ሙስናን ለመታገል ይበልጥ የተሻለ ዘዴ የማስፈኑ ተግባር ገና ግዙፍ ነው። በወቅቱ የአስተዳደር ውይይት ላይ ዓቢይ ነጥብ ሆኖ የሚገኘው የአመራርና ሥነ-ምግባር ትስስር አለመኖር ነው።

የዓለም ባንክ የታሰበው የሥነ-ምግባር ማራማጃ ሕብረት ለጋሾችንና ራሱን ሳይጨምር በመልማት ላይ ባሉ አገሮች ሲቪል ሕብረተሰብ፣ መንግሥታትና ሌሎች ወገኖች ጭብጥ ተሳትፎ ሊመራ ይገባዋል ባይ ነው። ሆኖም በዚህ በኩል በታዳጊዎቹ አገሮች፤ አንዳንዴም በለጋሽ አገሮች ድጋፍ እስካሁን የተደረጉት ጥረቶች ሁሉ የሚጠበቀውን ውጤት ሳያስከትሉ መቅረታቸው ነው ችግሩ።

አፍሪቃን በተጨባጭ ከተመለከትን ምንም እንኳ የበጎ አስተዳደር መስፈን ጉዳይ፤ ይህም የሲቪክ ማሕበረሰብ ክፍላትን መብትና ነጻነት ይጠቀልላል፤ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በለጋሽ መንግሥታት ዘንድ ሣይቀር መሪ መፈክር ቢሆንም ሃቁ ከዚህ የራቀ ሆኖ ነው የሚገኘው። ራሱ በአሕጽሮት ኔፓድ በመባል የሚታወቀው ክፍለ-ዓለሚቱን ከኋላ ቀርነት ለማላቀቅ የተነሣሣ የአፍሪቃ የልማት ሽርክና የመንግሥታት መሪዎች ስብስብ ከመሆን አልፎ የለውጡን ባለቤትና ሞተር ሕብረተሰብን ሲያሳትፍ አይታይም።

ከውጭ አበዳሪዎች የሚገኝ ዕርዳታና የሕዝብ ንብረት በሰፊው የሚመዘበርበት የባለሥልጣናት ሙስና በፍጥነት መወገድ ያለበት የሕብረተሰብ ዕድገት መቅሰፍት ነው። በጎ አስተዳደር ደግሞ ዴሞክራሲን፤ የዴሞክራሲ ሥርዓትን መሠረተ-ዓላማዎች መከበር ወሣኝ ቅድመ-ግዴታ ያደርጋል። በአፍሪቃ ባለፉት ዓመታት ለይስሙላ በተካሄዱት ምርጫዎች በዚህ ረገድ ተሥፋ የሚሰጥ ዕርምጃ አልታየም። በጎ የአስተዳደር ዘይቤ ለምናቀርበው የልማት ዕርዳታ ዓቢይ ቅድመ-ግዴታ ነው ይሉ የነበሩት ምዕራባውያን መንግሥታት ድርብ የዴሞክራሲ መሥፈርትም የሲቪሉን ማሕበረሰብ ዕድል ከማዳበሩ ይልቅ መቅጨቱ ነው እዚህም እዚያም የታየው።

ታዲያ በዚህ ሁኔታ በታዳጊ አገሮች ሲቪክ ማሕበራትን ያቀፈና እኩል የመናገር መብት የሚሰጥ ፍቱን የሥነ-ምግባር አራማጅ ሕብረትን እንዴት ነው ዕውን ማድረግ የሚቻለው? ሲበዛ የሚያጠያይቅ ጉዳይ ነው።