1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የብድር ማዕቀፍ "እንዲቀጥል" ኢትዮጵያ ጠየቀች

ሐሙስ፣ መስከረም 13 2014

ኢትዮጵያ የተራዘመ የብድር አቅርቦት (Extended Credit Facility) የተባለው እና መስከረም 9 ያበቃው የዓለም የገንዘብ ድርጅት ማዕቀፍ እንዲቀጥል መጠየቋን የገንዘብ ምኒስትር ድኤታ እዮብ ተካልኝ ተናግረዋል። በማዕቀፉ ከተፈቀደላት 1.7 ቢሊዮን ዶላር ብድር ውስጥ ኢትዮጵያ የወሰደችው ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ብቻ ነው።

https://p.dw.com/p/40fkH
Video Still TV Magazin The 77 Percent
ምስል DW

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የብድር ማዕቀፍ "እንዲቀጥል" ኢትዮጵያ ጠየቀች

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ጠቀም ያለ ገንዘብ ከምትበደርባቸው አንዱ የሆነው እና የተራዘመ የብድር አቅርቦት (Extended Credit Facility) የተባለው ማዕቀፍ ጊዜው ሳይጠናቀቅ የመቋረጥ ሥጋት ተጋርጦበታል። ይኸ ማዕቀፍ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ አገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ ድጋፍ ከሚያደርግባቸው መርሐ-ግብሮች አንዱ ነው።

ለሶስት አመታት በሚዘልቀው የድጋፍ መርሐ-ግብር በሁለት ማዕቀፎች የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ለኢትዮጵያ በአጠቃላይ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት ውሳኔ ያሳለፈው በታኅሳስ 2012 ዓ.ም. ነበር።

ይኸ ገንዘብ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የተራዘመ የብድር አቅርቦት (Extended Credit Facility) እና የተራዘመ የፈንድ አቅርቦት (Extended Fund Facility) በተባሉ ሁለት ማዕቀፎች በኩል ነው። ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ የተራዘመ የብድር አቅርቦት (Extended Credit Facility) በተባለው ማዕቀፍ ከተፈቀደላት 1.7 ቢሊዮን ዶላር ብድር ውስጥ ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ብቻ እንደወሰደች የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት መረጃ ይጠቁማል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቃል አቀባይ ጄሪ ራይስ "የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሐ-ግብር በተያዘው መስከረም ወር ያበቃል። ሌላኛው የተራዘመ የፈንድ አቅርቦት በሥራ ላይ ይቀጥላል" ሲሉ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ተናግረው ነበር።

ኢትዮጵያ ባለባት የውጭ ዕዳ  ላይ ልታደርግ ባቀደችው የአከፋፈል ሽግሽግ ምክንያት ይኸው የተራዘመ የብድር አቅርቦት ከትናንት በስቲያ መስከረም 9 ቀን 2014 ዓ.ም. "ያበቃ ነበር" ሲሉ የኢትዮጵያ የገንዘብ ምኒስትር ድዔታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ዛሬ በአዲስ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

"ይኸ የዕዳ ሽግሽግ ስለዘገየ የተራዘመ የብድር አቅርቦት የምንለው መስከረም 9 ያበቃ ነበር" ያሉት ዶክተር እዮብ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከቡድን 20 አባል አገራት ጋር በተደረገ ውይይት "እንደገና እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ጥያቄ አቅርባለች። በዚህ መሠረት ያንንው የገንዘብ መጠን በአዲስ መልክ እንደገና የሚቀጥል ይሆናል" ሲሉ ተደምጠዋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቃል አቀባይ ጄሪ ራይስ ግን "አዲስ መርሐ-ግብር ለማቀድም ሆነ አሁን በሥራ ላይ ያለውን የተራዘመ የፈንድ አቅርቦት ለመገምገም በባለሙያዎች እና በባለሥልጣናቱ መካከል ግንኙነት ለመጀመር ጊዜው ገና ነው። ነገር ግን መደበኛ ግንኙነታችን እንደቀጠለ ነው። የኤኮኖሚ ትንተና እና የፖሊሲ ውይይታችን ይቀጥላል" ሲሉ እንዲህ በአጭር ጊዜ ጊዜው ያበቃውን ማዕቀፍ መተካት እንደማይቻል የሚጠቁም አስተያየት ሰጥተዋል።

ከዚህ ቀደም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ በዘረጋው ተቀራራቢ መርሐ-ግብር ተመሳሳይ ዕክል ገጥሞ እንደነበር የሚያስታውሱት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ "ይኸ ትልቅ ገንዘብ ስለሆነ እንነጋገር ቢባል እንኳን ከእንደገና ሰነድ ማዘጋጀት ዝርዝር ጉዳዮችን ማውጣት ስለሚጠይቅ ብዙ ጊዜ የሚፈጅ ነው። በትንሹ ሶስት አመት ይፈጃል" ሲሉ ያስረዳሉ።   

ይኸ ማዕቀፍ እስከ ታኅሳስ 2015 ዓ.ም. የሚዘልቅ ነበር። የማዕቀፉ ያለ ጊዜው ማብቃት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ኢትዮጵያ ያለ ወለድ ልትበደር ከተፈቀደላት 1.7 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ የቀረውን 1.5 ቢሊዮን ዶላር የማግኘት ዕድሏ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።

ኢትዮጵያ በጠየቀችው እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በተስማማበት መሠረት የአበዳሪዎች ኮሚቴ ተቋቁሞ የመጀመሪያውን ስብሰባ ባለፈው መስከረም 6 ቀን 2014 ዓ.ም ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በመግለጫው መሠረት ዋና ዋና የኢትዮጵያ አበዳሪዎችን ባካተተው እና ፈረንሳይ እና ቻይና በተባባሪ ሊቀ-መንበርነት በመሩት ስብሰባ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። 

ኢትዮጵያ ከአቅሟ 700 በመቶ የላቀ ገንዘብ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት መበደር  ሲፈቀድላት በምትኩ የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በርከት ያሉ የቤት ሥራዎች እንዲያከናውን ይጠበቅበት ነበር። የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዘላቂነት መፍታት እና በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት መዘርጋት ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የዕዳ ተጋላጭነት ለመቀነስ የአስተዳደር እና ቁጥጥር ሥርዓቱን ማጥበቅ፤ የአገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን ማጠናከር፤ የመንግሥት ወጪ ለድህነት ቅነሳ እና መሰረታዊ የመሠረተ-ልማት ግንባታ በሚያመች መንገድ ማቀላጠፍ የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ማከናወን አለበት ከተባሉ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።

የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ እና አገሪቱ የምትከተለውን የገንዘብ ፖሊሲ የግል መዋዕለ-ንዋይን በሚያግዝ መንገድ ማሻሻል፤ የፋይናንስ አገልግሎት ደኅንነት ማዕቀፍን ቁጥጥር ማጠናከር ተጨማሪ የቤት ሥራዎች ናቸው። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ እነዚህ በርከት ያሉ የቤት ሥራዎች መንግሥትን የሚፈትኑ መሆናቸውን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ