1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና

ሰኞ፣ ነሐሴ 13 2005

ሞስኮ ላይ ሲካሄድ የሰነበተው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት ከሞላ ጎደል በስኬት ተጠናቋል።

https://p.dw.com/p/19SLn
ምስል Getty Images

ሻምፒዮናው በተለይም ለጃሜይካው የአጭር ርቀት መንኮራኩር ለዩሤይን ቦልት፣ ለአገሩ ልጅ ለሼሊይ-አን-ፍሬዘር-ፕራይስና ለብሪታኒያው ሯጭ ለሞ ፋራህ እጅጉን የተዋጣ ነበር ለማለት ይቻላል። ዩሤይን ቦልት በ 100፤ በ 200 እና በ 4x100 ሜትር የዱላ ቅብብል ተፎካካሪዎቹን በቀላሉ ሲያሸንፍ ያለፉ ሁለት ኦሎምፒክ ውድድሮች ድሎቹን እንደገና ለመድገም በቅቷል።

ጃሜይካዊው አትሌት በተፎካካሪዎቹ ላይ ፍጹም የበላይነቱን እንደያዘ ለቀጣዩ የ 2016 የሪዮ ኦሎምፒክ እንደሚደርስ የራሱና የብዙዎችም ዕምነት ነው። በሞስኮው ሉዥኒኪ ስታዲዮም ዩሤይን ቦልት በወንዶች የማይበገር ልዕልና እንዳሳየው ሁሉ በሴቶችም ጃሜይካዊቱ ፍሬዘር ፕራይስ በተመሳሳይ ርቀቶች የማትበገር ሆና ታይታለች።

ሻምፒዮናው በአጭር ርቀት ሩጫ የአሜሪካ የበላይነት ጨርሶ ያከተመለት መሆኑ እንደገና የተረጋገጠበት ነበር። ዩ ኤስ አሜሪካ በዚሁ የተነሣም በአጠቃላይ ድል ቀደምቱን ቦታ ለሩሢያ መተዉ ግድ ነው የሆነባት።

በመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጫ ልዕልናው ምንም እንኳ በኢትዮጵያና በኬንያ ዕጅ እንዳለ መቀጠሉ ባይቀርም ከሶማሊያ የመነጨው የብሪታኒያ ተወዳዳሪ ሞ ፋራህ በአምሥትና አሥር ሺህ ሜትር እንደገና የለንደን ኦሎምፒክ ድሉን መድገሙ ጥቂትም ቢሆን አፍሪቃውያኑን አትሌቶች ግርማ ሞገስ ማሳጣቱ አልቀረም።

Olympiasiegerin Tirunesh Dibaba
ምስል Haimanot Tiruneh

ከዚህ አንጻር በሴቶች ጥሩነሽ ዲባባና መሠረት ደፋር በነዚህ ርቀቶች የኢትዮጵያን ብቻ ሣይሆን የመላውን አፍሪቃ ክብር ማስጠበቃቸው ሊወደስ ይገባዋል። የሞስኮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እርግጥ ብዙዎች አትሌቶች የተከለከሉ አጎልባች መድሃኒቶችን በመውሰድ በመታገዳቸውና በሌሎች ምክንያቶችም እንደቀድሞው አዳዲስ ክብረ-ወሰኖች የተመዘገቡበት አልሆነም።

ቢሆንም በዝግጅቱ አኳያ ብዙ ጉድለት መታየቱ አይቅር እንጂ የከፋ አልነበረም ለማለት ይቻላል። የኢትዮጵያን አትሌቶችን ውጤት በተመለከተ በስፍራው የምትገኘውን ወኪላችንን ሃይማኖት ጥሩነህን ዛሬ በስልክ አነጋግሬያለሁ፤ያድምጡ!

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ