1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ኤኮኖሚ በተገባዳጁ 2008 ዓ.ም.

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 22 2001

ዛሬ ማምሻውን እኩለ-ሌሊት ላይ የሚሰናበተው የጎርጎሮሣውያኑ 2008 ዓ.ም. ኤኮኖሚን በተመለከተ ዓለምን ከአያሌ ዓመታት ወዲህ ብርቱ ነውጽና ውዥምብር ላይ ጥሎ ነው ያለፈው።

https://p.dw.com/p/GPty
የፊናንስ ገበዮች ውዥቀት
የፊናንስ ገበዮች ውዥቀት

የነዳጅና የምግብ ዋጋ ንረት፤ በተለይ ድሆች አገሮችን ክፉኛ ሲንጥ ቀደም ባለው ዓመት በአሜሪካ የቤት ባለቤቶች ዕዳ መንሰራራት የጀመረው ችግር ደግሞ በ 2008 መገባደጃ ገደማ የለየለት የፊናንስ ቀውስን ያስከትላል። የአሜሪካን ታላላቅ ባንኮች ተንኮታኩቶ መውደቅና የፊናንሱን ገበዮች ውዥቀት ዓመቱ ሃ ብሎ ሲጀምር በዚህ መጠን የጠበቀውም ሆነ ለመተንበይ የደፈረ አንድም የኤኮኖሚ ጠቢብ አልነበረም። ለማንኛውም የፊናንሱ ገበያ ቀውስ ተጽዕኖ ቀስ በቀስ በአምራቹ ኤኮኖሚ ዘርፍ ላይ ግልጽ እየሆነ ሲሄድ መዘዙንና ጓዙን ጠቅልሎ አብሮን ወደ አዲሱ ዓመት እየተሻገረ ነው። ተሰናባቹ ዘመን 2008 በበለጸገውም ሆነ በታዳጊው ዓለም በብዙዎች ዕለታዊ ኑሮ ላይ አጃቢ ሆኖ ይቀጥላል።

ላይመለስም ቢሆን መዘዙን ለተከታዩ አሸክሞ የሚያከትመው 2008 ዓ.ም. የዓለምን ኤኮኖሚ ምናልባትም ከሰላሣኛዎቹ ዓመታት ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ ወዲህ ለብርቱ ውዥቀት ዳርጎ ነው የሚያልፈው። ገና በዓመቱ መጀመሪያ በወርሃ ጥር የነዳጅ ዘይት ዋጋ በበርሚል፤ ማለትም በ 159 ሊትር ወደ መቶ ዳላር ያሻቅባል። የመጨረሻ ጣራውም አልነበረም። ይህ ሂደትና ሌሎች ምክንያቶችም ተጣምረው በዓለም አራት ማዕዘናት ገና ከጅምሩ የኤኮኖሚ ዝግመት ስጋትን ይደቅናሉ። መንግሥታት በተለይም በምዕራቡ ዓለም ምንም እንኳ የኋላ ኋላ የመጣውን ቀውስ በዚያ መጠን ባይጠብቁትም የዓመቱን የዕድገት ትንበያቸውን ዝቅ አድርገው ማረም የጀማመሩት ወዲያው ነበር። በዚህ በጀርመን ሂደቱን ለስለስ ባለ መልክም ቢሆን ከጠቆሙት ጠበብት አንዱ የበርሊኑ የምጣኔ-ሐብት ምርምር ኢንስቲቲቱት ፕሬዚደንት ክላውስ ሢመርማን ነበሩ።

“የኤኮኖሚው ዕድገት ረገብ እያለ ነው። የማቆልቆል አደጋውም ትልቅ እየሆነ መሄድ ይዟል። ፍጥነቱ ካለፈው ዓመት ሲነጻጸር እርግጥ ለዘብ እያለ መሆኑ አያጠያይቅም። ይህም ሆኖ ግን እኛ የምናምነው የጀርመን የዕድገት መንኮራኩር ነፋሻ እየሆነ በሄደው የዓለም ኤኮኖሚ ባሕር ላይ በአስተማማኝ ሁኔታ እየቀዘፈ እንደሚራመድ ነው”

የነዳጅ ዘይት ዋጋ ወደ ላይ መተኮስ፣ የአሜሪካ ኤኮኖሚ መዳከምና የዶላርም መውደቅ ምንም እንኳ አዝማሚያው አደገኛ መሆኑን ቢያሳይም ወደ ኋላ የተከሰተው የለየለት ቀውስ በዚህ ወቅት ገና የሩቅ ነገርን ያህል ነበር። ሆኖም አመቱ እየገፋ አጋማሹ ላይ ሲዳረስ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ይበልጥ በማሻቀብ በበርሚል 150 ዶላር ገደማ ይጠጋል። የዚሁ የነዳጅ ዋጋ ምጥቀት ደግሞ በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸገው ዓለም አውቶሚል ዘዋሪውን በማስቆጣትና በማንጫጫት ብቻ አልተወሰነም። የብዙ ምርቶችን ዋጋ ወደ ላይ በመስቀል ከበድ ያለ የኑሮ ውድነትን ያስከትላል። በተለይ የዕርሻ ምርቶች ዋጋ መናር በዓለምአቀፍ ደረጃ የምግብ ዋጋ እስከዚያው ወዳልታወቀ ጣራ እንዲጋልብ ነው ያደረገው።

የዓለም ኤኮኖሚ አጽናፋዊነት እርግጥ ከዚያ ቀደም በየጊዜው ይባል እንደነበረው ሁሉ ዋና ምክንያት ሆኖ በተደጋጋሚ ተነግሯል። ግን ምክንያቱ በዚህ አጠቃላይ አባባል ተወስኖ አይቀርም። ዋሺንግተን ላይ ተቀማጭ የሆነው የምግብ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲቲቱት ጠቅላይ አስተዳዳሪ ዮአኺም-ፎን-ብራውን ፍጆቱ ከምርቱ እየጨመረ መሄዱን ነበር ዓቢይ ችግር አድርገው የጠቆሙት።

“በዕርሻው ዘርፍ ዓለምአቀፉ የምርት ዕድገት ዛሬ በዓመት ከአንድ እስከ አንድ ተኩል በመቶ ቢሆን ነው። ይሁንና በዛሬይቱ ዓለማችን ውስጥ የሕዝብ ቁጥር እየናረ በመሄዱ የተነሣ ሚዛን ለመጠበቅ በዘርፉ አራት ከመቶ የሆነ ዕድገት ያስፈልጋል። እና ልዩነቱ እየሰፋ ነው የሄደው። በሌላ አነጋገር ዓለም ከሚያመርተው በላይ ነው የሚፈጀው”

ይሄው አልበቃ ብሎ የሚመረተው የዕርሻ ውጤት የተራበ ሆድን በመሙላት ፋንታ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ባዮ-ነዳጅ ለማውጣት በሥራ ላይ መዋሉ ደግሞ ያስተዛዝባል። የምግብ ዋጋ መናር በተለይ በእንቅርት ላይ ጆር ደግፍ የሆነው ለታዳጊው ዓለም ድሃ ሕዝብ ነው። በኢትዮጵያ ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ተጽዕኖ ቤት ሰራሽ ችግር ታክሎበት በዓመቱ ያስከተለው የምግብ ዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ሕብረተሰቡን ከሥር መሠረቱ አናግቷል። 2008 ዓ.ም. ለብዙሃኑ የሚላስ የሚቀመስ ማግኘት ያዳገተበት ነበር። መንግሥት ችግሩን ለማስታገስ የተወሰኑ ዕርምጃዎችን ቢወስድና ለመውሰድ ቃል-ቢገባም ሁኔታው የሚገባውን ያህል ተሻሽሏል ለማለት በጣሙን ነው የሚያዳግተው። እንዲያውም ባይባባስ!

ለማንኛውም መንግሥት ለምርቱ ዋጋ መናር ከዓለምአቀፉ ተጽዕኖ ባሻገር ዓቢይ ምክንያት አድርጎ ያቀረበው የአንዳንድ ነጋዴዎችን አግባብ የለሽ የትርፍ ማጋበስ ድርጊት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጊዜው በጉዳዩ በም/ቤት እንደተናገሩት!

ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ ዋጋ ንረትና ከሃያ በመቶ በላይ የኑሮ ውድነት ሕብረተሰብን በሰፊው ማነጋገር ይዞ እንዳለ በሌላ በኩል ደግሞ የአገሪቱ ኤኮኖሚ ከአምሥት ዓመት ያልተቁዋረጠ ዕድገት በኋላ በተከታዩም ከአሥር በመቶ በላይ ዕድገት እንደሚያሳይ መንግሥት ያስታውቃል። በኢትዮጵያ ታየ የተባለው የኤኮኖሚ ዕርምጃ ይሁንና በሕብረተሰብ ዕድገት የሕዝብ ተጠቃሚነትንም ሆነ የኑሮ ሁኔታ መሻሻልን አላስከተለም። የኦሮሞ ፌደራል ኮንግሬስ ተጠሪ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በአገሪቱ ም/ቤት በጊዜው በተካሄደው ክርክር ላይ ይህንኑ ሃቅ ያስረግጣሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ ዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ሳያንስ ረሃብም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብን ጠምዶ ነው ዓመቱ የሚገባደደው። 2008 ዛሬ ሌሊቱን ያልፋል። ረሃቡ ግን ነገ በአዲሱ ዘመንም ለብዙዎች ፈታኝ ሆኖ ነው የሚቀጥለው። ያሳዝናል ከዚህ አዙሪት መውጣት አለመቻሉ!

በዓመቱ መገባደጃ አቅራቢያ ወርሃ ጥቅምት የአሜሪካ ግዙፍ መዋዕለ-ነዋይ ባንኮች ተራ በተራ እየከሰሩ መንኮታኮት ሲጀምሩ የዓለም የፊናንስ ገበዮችም ውዥቀትና ውዥምብር ላይ ይወድቃሉ። ብዙዎች ያልጠበቁት ወይም ሊቀበሉት ያልፈለጉት ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ ገሃድ ይሆናል። የሰላሣኛዎቹ ዓመታት መሰል የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ አደጋ ሩቅ ያለመሆኑ ግንዛቤ በብዙዎች አዕምሮ የሰረጸው በዚህ ወቅት ነበር። ለነገሩ ብዙ ውዥምብርና ግራ መጋባት ይታይ እንጂ ኢትዮጵያዊው የኤኮኖሚ ምሁር ዶር/ በፈቃዱ ደገፌ በጊዜው እንደጠቀሱት ችግሩ ድንደት የመጣ ዱብ ዕዳ አልነበረም።

በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ባንኮቻቸውን ለማዳንና የዓለምአቀፉን የፊናንስ ገበዮች የገንዘብ ፍሰት መልሶ ሕያው ለማድረግ ከለንደን እስከ ቶኮዪ፤ ከበርሊን እስከ ዋሺንግተን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዚህ ቀደም ባልታወቀ መጠን ብዙ ሚሊያርድ ዶላር አፍሰዋል። ከዚህ ገንዘብ ጥቂቷ እንኳ ረሃብን ለመታገል ብትውል በአዲሱ 2009 ዓ.ም. አንድም ረሃብተኛ ባልተገኘ ነበር፤ ሰሞኑን በዚህ በጀርመን የኬር-ኢንተርናሺናል ግብረ-ሰናይ ድርጅት ቅርንጫፍ አስተዳዳሪ የተናገሩት።

ለማንኛውም ቡድን-ሃያ መንግሥታት በቅርቡ ዋሺንግተን ላይ ባካሄዱት ዓቢይ ጉባዔም ዓለምአቀፉን የፊናንስ ሥርዓት በመጠገንና በገበያው ላይ ግልጽ አሠራርን በማስፈን ቀውሱ እንዳይደገም በጋራ ለመታገል ተስማምተዋል። ዕርምጃው በቂ ነው-አይደለም ወደፊት ጠብቆ መታዘቡ ይመረጣል። ከወዲሁ አንድ ጭብጥ ሃቅ ካለ ግን የታዳጊውን ዓለም የኤኮኖሚ ተጠቃሚነትና ዕድገት የማይጠቀልል የሥርዓት ተሃድሶ ፋይዳ እንደማይኖረው ነው። በዚህም ዓመት ያልሰመረውን ፍትሃዊ የዓለም ንግድን ለማስፈን ታስቦ የተጸነሰውን የዶሃን ድርድር መልሶ ማንቀሳቀሱ ነገ በአዲሱም ዓመት እንደገና ወቅታዊ ጥያቄ ነው የሚሆነው።