1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ኤኮኖሚ በተፈፀመው ጎርጎራዊ ዓመት ፪ሺ፬ እንዴት ነበር? (፪)

ሐሙስ፣ ጥር 12 1997

በተፈፀመው ዓመት ፪ሺ፬ የአውሮጳው የጋራ ሸርፍ ኦይሮ በምንዛሪ ደረጃው ረገድ ጋላቢ እየሆነ፣ እየመጠቀ ነበር የሄደው። በዚያው ዓመት መጨረሻ ላይ አንዱ ኦይሮ ከአንድ ዶላር ከ፴ በልጦ ነበር የተገኘው። አውሮጳውያኑ ይኸው የኦይሮ ተመን አለቅጥ የበዛ ሆኖ ነበር ያዩት፤ በተለይም አውሮጳውያኑ ላኪዎች ውዱ ኦይሮ በዩኤስ አሜሪካው ገበያ ላይ አለቅጥ ውድ ያደረገባቸውን ሸቀጥ መሸጥ አዳጋች ነበር የሆነባቸው። በዚህ አንፃር ደግሞ፥ ደካማው ዶላር ለአሜሪካውያኑ ሸ

https://p.dw.com/p/E0f2

�ጥ-ላኪዎች ጥሩ የገበያ ዕድል ነበር የሰጠው።

በአውሮጳውያኑ አመለካከት መሠረ፥ አለቅጥ ተዛናፊው የኦይሮና የዶላር ግንኙነት በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው የሆነው። ችግሩ የሚመነጨው ከዩኤስ-አሜሪካው ድርብ ጉድለት ነው---ማለት ከበጀት ጉድለትና ከንግድ ሚዛን ጉድለት። አሜሪካውያኑ ወደ ውጭ ከሚልኩት ይልቅ ከውጭ የሚያስመጡት ነው የሚያመዝነው፤ በያመቱም ከገቢያቸው የሚልቀውን ገንዘብ ነው ወጭ የሚያደርጉት(በጀታቸውን በማጓደል ማለት ነው)። በኢራቅ የተወሰደው ወታደራዊው ርምጃ ይህንኑ የበጀት ጉድለት በጣም ነው ያባባሰው። የእስያ ሀገሮች ዩኤስ-አሜሪካ ውስጥ የሚያውሉት በሚሊያርድ የሚታሰበው ወረት የበጀቱን ጉድለት ይሸፍነዋል፣ ከዚህም የተነሳ አሜሪካውያኑ ለበጀት ማስተካከያው ርምጃ ብዙ ደንታ የሚያደርጉ አይመስልም። እንዲያውም ግዙፊቱ ቻይና ዛሬ አሜሪካ ውስጥ ዋና የውኢሎተንዋይ ኃይል የሆነችበት ሚናም ነው የሚታየው። የቻይና ሸርፍ ዩዋን በዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ግንኙነት ከዘጠኝ ዓመታት ወዲህ ሳይለወጥ ነው የቆየው።

በአሜሪካውያኑ አመለካከት ግን፥ ለፊናንሱ ጉድለታቸው፥ ያው የቻይናው ሸርፍ ዩዋን ነው ተጠያቂ ሆኖ የሚታየው። ይኸውም፥ ዩዋን የሚመነዘርበት ተመን አለቅጥ ያነሰ ከመሆኑ የተነሳ፣ ዱሮውንም ርካሽ የሆኑት የቻይና ሸቀጦች አሜሪካ ውስጥ በርካሽ ዋጋ የሚቸበቸቡ መሆኑ ነው። የዩዋን ምንዛሪ ተመን ለነፃው ገበያ አደላዳይነት በነፃ እንዲተው አሜሪካውያኑ በየጊዜው የሚያቀርቡትን ማሳሰቢያ ሲቃረን የቆየው የቻይናው አመራር ደግሞ፥ ዩኤስ-አሜሪካውያኑ በሸርፉ መርሕ ረገድ ሌሎችን በመንቀፍ ፈንታ ራሳቸው የራሳቸውን ሸርፍ ውድቀት መግታት እንዳለባቸው ያስገነዝባል።

የሆነ ሆኖ፥ የአሜሪካው ድርብ የሚዛን ጉድለት በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚለወጥበት ምልክት አይታይም። የዋጋውን ግሽበት ለመግታትና ዶላርን እንደገና ኣማላይ ለማድረግ ያሜሪካው ማዕከላይ ባንክ የባንክ ወለዱን ተመን ወደ አውሮጳው ደረጃ ከፍ አድርጎት ነበር፤ ግን ከፍተኛው የወለድ ደረጃ ያሜሪካውን የኤኮኖሚ ዕድገት የሚገታና ጠቅላላውንም የዓለም ኤኮኖሚ የሚነካ እንደሚሆን ነው ታዛቢዎች የሚያስገነዝቡት። የዶላር ውድቀት ካልተገታ በስተቀር፥ የዓለም መሪ ገንዘብ ሆኖ የቆየበትን ሚና ለኦይሮ የሚለቅ እንደሚሆን ነው ብዙዎች የሚያስገነዝቡት።


በ፪ሺ፬ ሂደት የምድር ዘይት ዋጋ አለቅጥ እየመጠቀ፣ በየበርሜሉ ከ፶ ዶላር በልጦ የተገኘበትም ጊዜ ነበር። የዓለም ኤኮኖሚ በምድር ዘይት ላይ ያለበት ጥገኝነት እጅግ የከበደ ነው፤ አቶም-ኃይል እና የነፋስ ኃይል ተቋማትም ይህንኑ ሁኔታ ሊቀይሩት አልበቁም፤ አማራጭ አልሆኑም። የምድር ዘይት ዋጋ ንረት ለወደፊቱ የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት ከባድ አደጋ ሆኖ ነው የሚያዩት የኤኮኖሚ ተመራማሪዎቹ ሊቃውንት።

እንደሚታወቀው፥ በሩሲያ፣ በማዕከላይ ምሥራቅ፣ በሳኡዲት ዓረብያ፣ በኢራቅ፣ በቬኔዙኤላ፣ ወይም በሌላይቱ የምድርዘይት ሀገር ናይጀሪያ አንድ ቀውስ በተፈጠረ ቁጥር ግፊቱ በዘይቱ ዋጋም ላይ ነው የሚያንፀባርቀው፣ ገበያውን ተወጣሪ ነው የሚያደርገው።

አንዳንዶች፥ የምድር ዘይቱ ገበያ በአረጠኞች አድራጎት እንደሚቃወስ ሲጠቁሙ፣ ሌሎች ደግሞ ከአዲሶቹ የኤኮኖሚ ዕድገት ግስጋሴ ሀገሮች ቻይናና ሕንድ እየገነነ የሚፈነጠቀው የግብይቱ ፍላጎት ለዋጋው ምጥቀት ተጠያቂ ነው ይላሉ። በእነዚያው የግስጋሴ ሀገሮች ውስጥ በየጊዜው፥ በይበልጥ ብዙ ይመረታል፣ ብዙ ይገነባል፣ ብዙ ይፈጃል፣ ብዙ ተሽከርካሪ ይርመሰመሳል። ለዚህ ሁሉ የምድር ዘይት እጅግ ይፈለጋል፤ ይህም በበኩሉ ዋጋውን ያመጥቀዋል። የዋጋው ምጥቀት ለእንዱስትሪ-ሀገራት ኤኮኖሚ ብቻ አይደለም ጭነት የሚሆነው፤ በቻይና የሚገነው የምድርዘይቱ ጥም አደጋን የሚደቅን ሆኖም ነው የሚያዩት አንዳንድ ታዛቢዎች። በዚህም መሠረት፥ ቻይናውያኑ ልክ ዩኤስ-አሜሪካውያኑ የሚያደርጉትን ያህል የምድር ዘይት ፍጆታቸውን የሚያገዝፉትና በነፍስወከፍ ከአሜሪካው እኩል የሚያደርጉት ከሆነ፣ እነርሱ በየቀኑ የሚፈጁት ነዳጅዘይት ፺ ሚሊዮን በርሜል ሊደርስ እንደሚችል፣ የዋሽንግተኑ ተመራማሪ ተቋም “ዎርልድዎች ኢንስቲቱት” ይገምታል። እጎአ በ፪ሺ፩ ዓ.ም. ጠቅላላው የዓለም ነዳጅዘይት ምርት ፸፱ ሚሊዮን በርሜል ደርሶ ነበር የተገኘው። በዚህ አኳኋን ታዲያ፥ ቻይናውያኑም ያሜሪካውያኑን አኗናር ቀድተው ልክ እንደነርሱ ለመኖር ቢፈልጉ፣ ያችው ግዙፍ ሀገር፣ ቻይና፣ መላው የዓለም ነዳጅዘይት ምርት ለፍጆታዋ የሚያስፈልጋት ይሆናል--በተቋሙ ስሌት።

እንዲያውም ቻይና ዛሬ ከዩኤስ-አሜሪካ ቀጥላ እጅግ ብዙውን አየር-በካይ ተን ወደ ሰማይ የምትረጭ ሀገር ሆናለች(ፍፁሙ አሃዝ ሲታይ)። በነፍስወከፍ ሲታይ፥ ጀርመን ውስጥ የተቃጠለው ጋዝ ርጭት ከቻይናው በ፫ እጅ፣ ያሜሪካው ደግሞ ከቻይናው በ፮ እጅ የላቀ ነው።

የአየር ብክለት እንዲቀነስ በኪዮቶ/ጃፓን የተደረሰውን ስምምነት አሜሪካውያኑ አይቀበሉትም፤ ቻይና እና ሌሎቹም ወደእንዱስትሪያዊው ዕድገት የተቃረቡት ሀገሮች አይደግፉትም። ሆኖም፣ በዚያው ዓመት፥ ፪ሺ፬፥ ሩሲያ ያንኑ ኪዮቶ-ሠነድ ለማጽደቅ በመብቃቷ፣ ስምምነቱ ጽናት ሊያገኝ ይችላል። ግን በታህሣሥ ቡኤኖስ አይረስ ላይ የተካሄደው ያየር ንብረት ጥበቃ ጉባኤ አንድ እመርታ በመጨመር ያየር ብክለት የሚቀነስበት አዲስ መንገድ እንዲፈለግ በማሳሰብ ነበር ያበቃው።

አለቅጥ ከፍተኛው የምድርዘይት ዋጋ በተለይ ከባድ የውጭ እዳ ያለባቸውን ድሆቹን አዳጊ ሀገሮች ነው የሚጎዳው። የዓለምአቀፉ ገንዘብመርሕ ድርጅት/ኣይኤምኤፍ ጥናት እንደሚጠቁመው፥ የነዳጅዘይቱ ዋጋ በየበርሜሉ በአምስት ዶላር ቢጨምር፥ የአንዳንድ አዳጊ ሀገሮች ኤኮኖሚ በሁለት በመቶ የሚሟሽሽ ይሆናል። እጅግ ከባዱ የውጭ እዳ የተጫናጨው ድሆቹ ሀገሮች ከባድ ችግር ላይ ወድቀው ሳለ፥ ሐብታሞቹ አበዳሪ ሀገራት ያንኑ ከባድ እዳ ሙሉ በሙሉ ለመሰረዝ ሳይበቁ ነበር ዓመቱ የተፈፀመው።

ሁሉ ነገር መቸም የቀዳሚው ትኩረት እና የፖለቲካ ግፊቱ ጥያቄ ነው። ኢራቅ ካለባት የውጭ እዳ ባለፈው ኅዳር ፹ በመቶው ነበር የተሰረዘላት፤ ይህ የተደረገው፥ ያችው ሀገር ከጦርነቱ ፍፃሜ በኋላ የመልሶ ግንባታውን ርምጃ እንድታጠናክር ለማስቻል እንደነበር ነው የተገለፀው።


የአፍሪቃው አህጉር በተፈፀመው ዓመት ፪ሺ፬ የድርቁ አደጋ ያደረሰበትን የመባልእት እጥረት የአንበጣ መንጋው ወረራ አባብሶት ነበር የተገኘው። የተባ መ የምግብና የእርሻ ድርጅት/ፋኦ ባለፈው ታህሣሥ ለ፪ሺ፬ ዓ,ም. ያቀረበው ዓመታዊ ዘገባ እንዳመለከተው፥ በዓለም እጅግ ከባዱ ድህነት በተጫነው በአፍሪቃው አህጉር ፳፫ ሀገራት የምግብ እጥረት የደረሰባቸው ከመሆናቸው የተነሳ፥ ሕዝባቸውን ለመመገብ ቢያንስ ፫ ሚሊዮን ቶን የእህል ርዳታ እንዳስፈለጋቸውና ለጋሾቹ መንግሥታት ከዚሁ ፪-ነጥብ-፰ ሚሊዮን ቶን የሚደርሰውን ከፊል ዝግጁ አድርገው ነበር። በድርቁ አደጋና የውዝግቦች ፍርርቅ ባስከተለው የስደተኞች ትርምስ ምክንያት የተፈጠረውን የምግብ እጥረት ያንበጣው ወረራ ካባባሰባቸው ሀገሮች መካከል በተለይ ሞሪታንያ ነበረች በቅድሚያ ስትጠቀስ የቆየችው። ግዙፉ ያንበጣ ማዕበል ሞሪታንያ ውስጥ ሣሩና ቅጠላቅጠሉ ሁሉ ሳይቀር ነበር ግጦ የጨረሰው። በተለይ ሰሜንና ምዕራብ አፍሪቃን ሲያዋክብ የቆየው ያው ያንበጣ ወረራ ወደፊትም ይብሱን እንደሚስፋፋ ስለሚያሠጋ፣ ያንኑ አደገኛ ተባይ ለመደምሰስ የሚደረገው ትግል በይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ነበር ፋኦ ያስገነዘበው።


በአሕጽሮት “ኮሜሳ” የሚሰኘው፣ ፳ የምሥራቅና የደቡባዊት አፍሪቃ ሀገሮችን የሚያጣምረው የጋራው ገበያ፥ በአህጉሩ ለሚፈለገው የክፍት ገበያ ግብ ንቃት የሰጠ መስሎ ነበር የተገኘው። “ኮሜሳ” በአህጉሩ የክፍት ገበያ ሥርዓት እንዲኖር፣ ነፃው የገበያ ውድድር እንዲነቃቃና ገበያን ዝግ የሚያደርገው የሞኖፖል ኃይል እንዲሰበር የሚያደርገውን መንገድ እንደሚከታተል፣ የዚሁ ቡድን ንግድ-ሚኒስትሮች ጉባኤ ግልጽ ነበር ያደረገው። ይኸው የጋራ ገበያ ማኅበር በጠቅላላው ፫፻፹፭ ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚያካብበው፣ ተደምሮ ሲታይ ከ፫፻፹፰ ሚሊያርድ ዶላር የሚበልጥ ጠቅላላ ብሔራዊ ውጤት እንደሚኖረውና ዓመታዊ የንግድ ልውውጡም ስድሳ ሚሊያርድ ዶላር እንደሚደርስ በመጠቆም ነበር መጻኢው ለአፍሪቃ ብሩህ እንደሚሆን የገለፀው።

በ፪ሺ፬ ለአፍሪቃ መጻኢ ተሥፋ የፈነጠቀው ሌላው አንቀሳቃሽ ኃይል በአህጽሮት “ ኔፓድ”/ማለት “አዲስ አጋርነት ለአፍሪቃ ልማት” የተሰኘው የአፍሪቃውያኑ መርሐግብር ነበር። አፍሪቃውያኑ መሪዎች ባፈራረቋቸው ጉባኤዎች ላይ እንደተገለፀው፥ አህጉሩ በኔፓድ የልማት መርሐግብር ሥር ለዕድገትና ለብልጽግና በሚያደርገው ጥረት ረገድ የዴሞክራሲውንና የመልካም አስተዳደሩን ደረጃ ለማሻሻል ጉልህ ፍላጎት ነበር የታየው። በዚሁ መርሐግብር ሥር ብዙ አፍሪቃውያን መንግሥታት ፈጣን ልማትን ዓይነተኛ ግብ በሚያደርገው በዴሞክራሲውና በመልካም አስተዳደሩ እመርታ ረገድ ፍተሻ እንዲደረግባቸው፣ ጉድለትም ከተገኘባቸው ለተግሳጽና ለእርማት ሊጋለጥባቸው እንዲችል ያሳዩት በጎፈቃድና ዝግጁነት እውነትም ተሥፋን ነበር የፈነጠቀው፤ ግና የዚሁ በጎፈቃድ ትግበራ ገና ወደፊት ነው የሚታየው።