1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የዓለም ኤኮኖሚ በጎርጎሮሳዊው 2017 3.5 በመቶ ያድጋል።

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 12 2009

የዓለም ኤኮኖሚ ከነበረበት መቀዛቀዝ እያንሰራራ እንደሆነ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አስታወቀ። በዚህ አመት የዓለም ኤኮኖሚ በ3.5 በመቶ እድገት ያሳያል ተብሏል። የዓለም የገንዘብ ድርጅት ይፋ ባደረገው የትንበያ ዘገባ ከሰሐራ በታች የሚገኙ አገራት ኤኮኖሚ በያዝንው የጎርጎሮሳውያኑ 2017 ዓ.ም. የ2.6 ከመቶ እድገት ያሳያል ብሏል።

https://p.dw.com/p/2bXwD
USA IWF Haupteingang
ምስል picture-alliance/dpa/J. Lo Scalzo

Wirtschaft-IWF bekräftigt optimistische Prognose-19.04.2017 - MP3-Stereo

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረገው ትንበያ በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሐራ በታች የሚገኙ አገራት የ2.6 ከመቶ ኤኮኖሚያዊ እድገት እንደሚያስመዘግቡ ገልጧል። የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በዚህ አመት በ7.5 ከመቶ እንደሚያድግ ትንበያውን ገልጧል። የታንዛኒያ፤ኬንያ፤አይቮሪ ኮስት እና የሴኔጋል ኤኮኖሚ በአንፃሩ ከ5-7 ከመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል። ዘገምተኛ የነበረው የደቡብ አፍሪቃ ናይጄሪያ እና አንጎላ ኤኮኖሚ የሚያሳየው ማገገም ከሰሐራ በታች ለሚገኙ አገራት ለተሰጠው ትንበያ ድጋፍ ያደርጋል ብሏል-ተቋሙ።  በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. በዓለም ገበያ ማሽቆልቆል የታየበት የሸቀጦች ዋጋ እና ኢትዮጵያን በመሳሰሉ አገራት የከፋ ተጽዕኖ ያሳደረው ድርቅ የቀጣናውን አጠቃላይ አመታዊ የምርት መጠን እድገት በ1.4 በመቶ ብቻ እንዲወሰን አስገድዶት ነበር።
ከጠባ አራት ወራት ባስቆጠረው የጎርጎሮሳውያኑ 2017 ዓ.ም. ኤኮኖሚያዊ እድገታቸው መነቃቃት ይታይበታል ከተባለላቸው አገራት አንዷ ናይጄሪያ ናት። ባለፈው አመት የኤኮኖሚ እድገት ዝግመት፤በዓለም ገበያ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ማሽቆልቆል እና የኃይል እጥረት የፈተናት ናይጄሪያ በዚህ አመት አመታዊ የምርት መጠኗ በ0.8% እድገት እንደሚያሳይ የዓለም የገንዘብ ድርጅት አዲስ የትንበያ ሰነድ ጠቁሟል። ደቡብ አፍሪቃ በበኩሏ ባለፈው አመት በ0.3 በመቶ የተወሰነው ኤኮኖሚያዊ እድገቷ ተነቃቅቶ  ወደ 0.8 % ከፍ ይላል። ደቡብ አፍሪቃ ከገጠማት ድርቅ ማገገሟ እና የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መሻሻሉ ለኤኮኖሚዋ እድገት መነቃቃት ቀዳሚ ምክንያቶች ተብለዋል። ከአኅጉሪቱ ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት አምራች ሀገራት አንዷ የሆነችው አንጎላ ባለፈው አመት እድገት ያላሳየው ኤኮኖሚዋ በዚህ አመት መነቃቃት ያሳያል ተብሎለታል።በናይጄሪያ፤ጋና እና አንጎላ የመገበያያ ገንዘባቸውን የመግዛት አቅም በማሳነሳቸው ምክንያት ባለ ሁለት አኃዝ የዋጋ ግሽበት ሊከሰት እንደሚችል  የዓለም የገንዘብ ድርጅት የኤኮኖሚ እድገት ትንበያ ገምቷል። 
በዓለም የገንዘብ ድርጅት ትንበያ መሰረት በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. መነቃቃት የሚታይበት ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪቃ አገራት ኤኮኖሚ ብቻ አይደለም። የድርጅቱ ዋና የኤኮኖሚ ባለሙያ ሞሪስ ኦብስትፌልድ ይኸ አመት የዓለም ኤኮኖሚ መሰረታዊ ለውጥ የሚያሳይበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ሳንሆን አንቀርም ባይ ናቸው። ድርጅታቸው ለጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. ባወጣው ትንበያ የዓለም ኤኮኖሚ በ3.5 ከመቶ ሊያድግ ይችላል ብሏል። 
"ካለፈው አመት አጋማሽ ጀምሮ የሚታየው የዓለም አቀፉ ኤኮኖሚ እድገት የቀደሙ ትንበያዎቻችንን ደግመን እንድናረጋግጥ ረድቶናል። በ2017 ዓ.ም. የዓለም ኤኮኖሚ በ3.5 ከመቶ ያድጋል ብለን እንጠብቃለን። ካለፈው ዓመት በ3.1 በመቶ የተሻለ ሲሆን በ2018 ዓ.ም. ደግሞ 3.6 ከመቶ ያድጋል።የኤኮኖሚ እድገት ፍጥነቱ በማምረቻ እና የንግዱ ዘርፍ በበለጸጉት፤ በማደግ ላይ በሚገኙት እና አነስተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ሰፊ መሰረት ይኖረዋል።"
በርካታ ደሐ አገሮች ባለፈው አመት የገጠማቸው ግጭት እና የጸጥታ መናጋት ኤኮኖሚያዊ እድገታቸውን እጅግ እንዳስተጓጎለባቸው የዓለም የገንዘብ ድርጅት የትንበያ ሰነድ ጠቁሟል። አፍጋኒስታን፤ቻድ፤ደቡብ ሱዳን፤የመን እና ናይጄሪያ በዚህ ጎራ ተዘርዝረዋል። ድርቅ ከአፍሪቃ በኢትዮጵያ እና በማላዊ እንዲሁም በሐይቲ ኤኮኖሚዎች ላይ የከፋ ተፅዕኖ አሳርፎ ነበር። እኒህ የጸጥታ መናጋቶች እና የአየር ጠባይ ለውጥ በያዝንውም አመት በበርካታ አገራት ኤኮኖሚ ላይ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችሉ ሞሪስ ኦብስትፌልድ ተናግረዋል። 

"ዓለም አቀፉ ኤኮኖሚ የእድገት ምልክት ቢታይበትም ካለፈው ትንበያ በታች የእድገት ምጣኔ የሚኖራቸው በርካታ አገሮች በዚህ አመት ይቸገራሉ። የሸቀጦች ዋጋ ከ2016 ዓ.ም. የመጀመሪያ ወራት ጀምሮ መረጋጋት ቢታይበትም በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ፤በአፍሪቃ እና በላቲን አሜሪካ በውጭ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ በገበያው ፈተና ገጥሟቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ አስከፊ የአየር ጠባይ እና ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በርካታ አነስተኛ ገቢ ያላቸው አገራትን እስከ ረሐብ የሚያደርስ ሥጋት እንዲደቀንባቸው አድርገዋል።"
በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች ኤኮኖሚ በዚህ አመት በ4.5 ከመቶ በሚቀጥለው አመት ደግሞ በ4.8 ከመቶ ሊያድግ ይችላል የሚል ትንበያ ተሰጥቶታል። የዩናይትድ ስቴትስ ኤኮኖሚ በጎርጎሮሳዊው 2017 በ2.3 ከመቶ በሚቀጥለው አመት ደግሞ በ2.5 ከመቶ ያድጋል ብሏል። 
"የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ አስተዳደር ፖሊሲ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት ወደ መሥፋፋት ሊያዘነብል ይችላል። የዩናይትድ ስቴትስ የኤኮኖሚ እድገት ቸልተኛ ሆኖ ከዘለቀ ውጤቱ የዋጋ ንረት ከሚጠበቀው በላይ በፍጥነት የሚያድግ የወለድ ምጣኔ ይሆናል። የዶላርን የበለጠ በማጠናከርም በማደግ ላይ ለሚገኙ ኤኮኖሚዎች በተለይም አብዛኛው በዶላር የሆነ እዳ ላለባቸው አገራት ፈተና ይጋርጣል። "
የዓለም ኤኮኖሚ ከተቋሙ የተሰጠው ትንበያ በጎ ቢሆንም ካለፉት አመታት ያነሰ ኤኮኖሚያዊ እድገት የሚያስመዘግቡ አገሮች መኖራቸው አልቀረም። የሸቀጦች ዋጋ መረጋጋት ቢታይበትም የጥሬ እቃ ዋጋ ማሽቆልቆል ለመካከለኛው ምሥራቅ፤አፍሪቃ እና ላቲን አሜሪካ አገራት መልካም ዜና አይደለም። የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዋና የኤኮኖሚ ባለሙያው ሞሪስ ኦብስትፌልድ የኤኮኖሚ እድገቱ አሁን ባለበት ደረጃ ለመቀጠሉ ማረጋገጫ እንደሌለ ይናገራሉ።
"አሁን የሚታየው የኤኮኖሚ እድገት መነቃቃት ባለበት ይቀጥላል ወይ የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው። የሸማቾች እና የንግዱ ዘርፍ በራስ የመተማመን መንፈስ በበለጸጉት ሀገራት ከዚህ በላይ እድገት ሊያሳዩ ይችላሉ። በሌላ በኩል የዓለም ኤኮኖሚ እድገቱን ወደ ኋላ የሚጎትቱ ፈተናዎችም ይገጥሙታል።"
የዓለም የገንዘብ ድርጅት ባቀረበው ትንታኔ የዓለም ኤኮኖሚ እድገት ማንሰራራት ያሳየው በሸቀጦች ዋጋ መረጋጋት እና የመዋዕለ-ንዋይ ላይ ፈሰስ የሚደረገው ገንዘብ በመጨመሩ መሆኑን ገልጧል። የገበያውን ፍላጎት በመምራቱ ረገድ ቻይና ቀዳሚ ስትሆን ኤኮኖሚዋ ካለፉት ሁለት አመት በተሻለ በ6.9 በመቶ እድገት እንደነበረው አስታውቃ ነበር። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የግል እና የመንግስት መዋዕለ-ንዋይ እድገት ማሳየቱ ለኤኮኖሚው አዎንታዊ ተፅዕኖ ማበርከቱን ይናገራሉ። የዓለም የገንዘብ ድርጅት የቻይና ኤኮኖሚ በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. ካለፈው አመት አነስተኛ ቅናሽ አሳይቶ በ6.6 በመቶ ያድጋል ብሏል። 

"ንግድ አማካኝ አመታዊ የገቢ መጠንን በማበረታታት እንዲሁም በመላው ዓለም በተለይም በደሐ አገሮች ድኅነትን በመቀነስ የእድገቱ ዋንኛ አንቀሳቃሽ ኅይል ሆኗል። ይሁንና ሁልጊዜም የጥቅም ክፍፍሉ በአገራት ዘንድ ሁልጊዜም እኩል አልነበረም። መንግሥታት የሰራተኞቻቸውን አቅም ካላጎለበቱ እና  ክፍፍሉን ፍትኃዊ ለማድረግ ካላገዙ ለንግዱ ዘርፍ የሚደረገው ፖለቲካዊ ድጋፍ ያሽቆለቁላል።"

ሮልፍ ቬንክል/እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ 

Venezuela | Einführung neuer Banknoten in Venezuela
ምስል Getty Images/AFP/J. Barreto
IWF Wachstumsprognose Maurice Obstfeld
ምስል Getty Images/AFP/M. Riley