1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ኤኮኖሚ ይዞታ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 3 2004

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም IMF በተለይ በኤውሮ ምንዛሪ ሃገራት የተፈጠረውን የበጀት ቀውስ ምክንያት በማድረግ የዓለም ኤኮኖሚ በዚህ በያዝነው ዓመት ከባድ አደጋ የተደቀነበት እንደሚሆን በዘመን መለወጫው ዋዜማ ማስጠንቀቁ የሚዘነጋ አይደለም።

https://p.dw.com/p/14aZi
ምስል REUTERS

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም IMF በተለይ በኤውሮ ምንዛሪ ሃገራት የተፈጠረውን የበጀት ቀውስ ምክንያት በማድረግ የዓለም ኤኮኖሚ በዚህ በያዝነው ዓመት ከባድ አደጋ የተደቀነበት እንደሚሆን በዘመን መለወጫው ዋዜማ ማስጠንቀቁ የሚዘነጋ አይደለም። የምንዛሪው ተቋም ሃላፊ ፈረነሣዊቱ ክሪስቲን ላጋርድ አሁን ሰሞሙን እንደገለጹት ደግሞ የዓለም ኤኮኖሚ የማገገም አቅጣጫን ይዞ እየተራመደ ነው።

ሆኖም የተቃወሰው የአውሮፓ የፊናንስ ስርዓት፣ ከፍተኛ የመንግሥትና የግል ዘርፍ ዕዳ፤ እንዲሁም አልበገር ያለው ሰፊ ሥራ አጥነት ሁኔታውን ወደቀድሞው ችግር ሊመልሰውም ይችላል። የመንግሥታቱ ዕዳው ገና ከፍተኛ ሲሆን ሰፊው ሥራ አጥነትም በሕብረተሰብ ላይ ሃያል ተጽዕኖ ነው ያለው። ላጋርድ የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር ፈታኝ ሊሆን እንደሚችልም ሳያስገነዝቡ አላለፉም።

«የማገገሙ ሂደት ባለበት መቀጠሉ ገና አስተማማኝ ነገር አይደለም። የአውሮፓ የፊናንስ ስርዓት ገና ከባድ የዕዳ ግፊት አለበት። የመንግሥቱም ሆነ የግሉ! ሰፊው ሥራ አጥነትም በሕብረተሰብ ላይ ሃያል ተጽዕኖ ነው ያለው። ይህ ሁሉ ሳያንስ አሁን ደግሞ የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር ሌላው አንዣባቢ አደጋ እየሆነ ነው»

እንዲህም ሆኖ ላጋርድ የዓለምን ኤኮኖሚ ሂደት ተሥፋ ሰጭ አድርገው መመልከታቸው አልቀረም። ከኤውሮ ምንዛሪ ሃገራትና ከአሜሪካ አኳያ የሚደርሱት መረጃዎች የሚያሳዩት እርሳቸው እንደሚሉት የማገገም አዝማሚያን ብቻ ነው። አውሮፓ በቅርቡ ከከባድ የበጀት ቀውስ ላይ የወደቀችውን ግሪክን ለማገዝ ባደረገችው ጥረት ችግሩን ለመፍታት ጠቃሚ ዕርምጃ አድርጋለች።

ከአሜሪካ በኩል የሚቀርቡትም የኤኮኖሚ መረጃ ዳታዎች ሻል ያሉ ሲሆኑ ከዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በኋላ የተወሰዱት የፖለቲካ ዕርምጃዎችም ፍቱንነት እንደሚያሳዩ የክሪስቲን ላጋርድ ዕምነት ነው። ሆኖም በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት ሃገራት ሰፍኖ የሚገኘው ከፍተኛ የዕዳ ሸክምና የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር ወደፊትም አደጋ እንደሆኑ ይቀጥላሉ። ለምሳሌ ያህል የኤውሮን ምንዛሪ ሃገራት፤ የኤውሮ-ዞንን ሁኔታ በንመለከት ከአጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት 23 በመቶ የሚሆነው ድርሻ የመንግሥታዊ ዘርፎችን ዕዳ ለመሸፈን ተግባር ላይ ሲውል ነው የቆየው።

ከዚሁ ሌላ በተፋጠነ ዕድግት የሚራመዱት ሃገራት የኤኮኖሚ ዕድገት እንዳያቆለቁል በምንዛሪው ተቋም ዘንድ ስጋቱ ከፍተኛ ነው። በዚሁ የተነሣም በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት የፊናንስ ስርዓታቸውን ማጠናከራቸውና ከውጭ የሚመጣ አደጋን ለመቋቋም ብቃት መፍጠራቸው ግድ መሆኑ ይጠቀሳል። እንደ ምንዛሪው ተቋም አሁን ለፖለቲካ ስህተት አንዳች ቀዳዳ መክፈት አይቻልም። መንግሥታቱ የፊናንሱን ዘርፍ በመጠገን ሚዛን የጠበቀ የበጀት ፖሊሲን ማራመድ አለባቸው።

መዋቅራዊና የመንግሥታዊ ተቋማት ለውጥ በማካሄድ በቀውሱ የተፈጠረውን ጉዳት ማስወገድና የፉክክር ብቃትን ማጠናከር ይኖርባቸዋል። ክሪስቲን ላጋርድ እንደሚያሳስቡት በተፋጠነ ዕድገት የሚራመዱት ሃገራትም ከበለጸጉት መንግሥታት ቀውስና ይሄው ሊያስከትል ከሚችለው የኤኮኖሚ ችግር ራሳቸውን ለመጠበቅ የኤኮኖሚ ዕድገት ዕርምጃዎቻቸውን ማጣጣማቸው ግድ ነው።

በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ ያሉትን ሃገራት ካነሣን የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም አስተዳዳሪ ክሪስቲን ላጋርድ ቻይናንም የኤኮኖሚ ዕድገትን በሚያራምዱ ዕምጃዎች ለዓለም ኤኮኖሚ መረጋጋት ላደረገችው አስተዋጽኦ አወድሰዋል። እርግጥ የቻይና መንግሥት ለውስጥ ኤኮኖሚው የሚሰጠውን ድጎማ ለዘብ አድርጎ መያዙና ውስጣዊ ፍጆትን በማጠናከር አዲስ የዕድገት አንቀሳቃሽ ሃይል መሻቱ አስፈላጊ ነው።

China Wirtschaft Logo Bank of China in Peking
ምስል AP

መለስ ብሎ ለማስታወስ ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ የኤውሮን ምንዛሪ ሃገራትና የአሜሪካን የፊናንስ ችግሮች በማጤን የዓለም ኤኮኖሚ ዕርምጃ በዚያው በተገባደደው 2011 እና በያዝነው 2012 ዓመት-ምሕረት የቀዘቀዘ እንደሚሆን ነበር የተነበየው። የጊዜው ማስጠንቀቂያ የ 2008-ን የበልግ ወራት ሁኔታ የሚያታውስ ነበር። ላጋርድ ከሰላሣኛዎቹ ዓመታት የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ ሁኔታ ሊዛምዱትም ሞክረዋል።

በ 2008 ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ጣራው ላይ እንደደረሰ ብዙ ማስጠንቀቂያዎች ነበሩ ከያቅጣጫው የሚሰነዘሩት። የዕድገት ትንበያን ዝቅ አድርጎ ማረምም እንዲሁ ሲደጋገም ታይቷል። ይህ እርግጥ ዛሬም ያለ ነገር ነው። የምንዛሪው ተቋም ዋና የኤኮኖሚ ባለሙያ ኢሊቪዬር ብላንቻርድ እንደሚሉት የማገገሙ ሁኔታ በሰፊው እያቆለቆለና ሊባባስ የመቻሉም አደጋ እየጨመር ነው የመጣው።

ተቋሙ በተፋጠነ ዕድገት በሚራመዱት ሃገራት 6,4 በመቶ የኤኮኖሚ ዕድገት ሲጠብቅ ለበለጸገው ዓለም 1,6 ከመቶ ነበር የተነበየው። በሌላ አነጋገር ይሄው በዓለምአቀፍ ደረጃ በአማካይ አራት ከመቶ ዕድገት ሲሆን በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸገው ዓለም ለዕድገቱ ያደረገው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ መሆኑን ያመለክታል።

ለዚህም ነበር የዓለም ንግድ ድርጅት ለምሳሌ ቀደም ብሎ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውሱን ለማለዘብ በሚደረደው ትግል የንግድ ገደብ ውይም መሰናክል እንዳይፈጠር ያስጠነቀቀው። የድርጅቱ ጠቅላይ ጸሐፊ ፓስካል ላሚይ እንደገለጹት በዚሁ ገበያን በመከለል ዕርምጃ ሳቢያ የዓለም ንግድ 800 ሚሊያርድ ዶላር አጥቷል። እናም መሰናክሉ በአንዳንድ የዓለም አካባቢዎች እየጠነከረ ሲቀጥል ቀውሱን ለመታገል ጨርሶ የማይበጅ ለመሆኑ እርግጥ አንድና ሁለት የለውም።

ቀውሱ እያደር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ታዳጊ በተባለው ዓለም ኤኮኖሚ ላይ ብርቱ ተጽዕኖ ማሰደሩም አልቀረም። የዚሁ ሂደት አንዱ መከሰቻ ሃብታም ሃገራት የሚሰጡት የልማት ዕርዳታ መቀነስ ነው። በአሕጽሮት OECD በመባል የሚጠራው የኢንዱስትሪው መንግሥታት የኤኮኖሚና የልማት ትብብር ድርጅት 34 ዓባል ሃገራቱ ለልማት ትብብር ያወጡት ገንዝብ ባለፈው ዓመት ቀደም ካለው ዝቅ ብሎ መገኘቱን ነበር አሁን በቅርቡ ያመለከተው።

Bäuerin in Uganda
ምስል DW

ድርጅቱ በጊዜው በትክክል 133,5 ሚሊያርድ ዶላር ወጪ ሲያደርግ ይህም ቀደም ካለው ዓመት ከ 2010 ሲነጻጸር በ 2,7 ከመቶ ያነሰ መሆኑ ነው። ለበጀቱ ማቆልቆል ምክንያቱ ደግሞ በዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ በበለጸጉት ሃገራት የሰፈነው ቁጠባ እንጂ ሌላ ነገር አይደለም። የኤኮኖሚና ልማት ትብብሩ ድርጅት የልማት ተራድኦ ዘርፍ የሰንጠረዥ ክፍል ሃላፊ የሆኑት ሣይመን ስኮት እንደሚሉት የተቆረጠው በጀት ያን ያህል ብዙ አይደለም። ሆኖም ግን አጠቃላዩን ሁኔታ ይለውጠዋል።

« ከጎርጎሮሳውያኑ ዓመት 1997 አንስቶ በድርጅቱ የልማት ትብብር በጀት ላይ ይህ ነው የሚባል ቅ ነሣ ተደርጎ አያውቅም። ሆኖም የወቅቱ ቅነሣ የሚጠቁመው ይሄው የሂደቱ ዘላቂ ባሕርይ እንደሚሆን ነው»

ስኮት ከተል አድርገው እንደሚስርዱትም ይህ በበጀት ችግር በተወጠሩት በግሪክና በስፓኝ ሁኔታ ጎልቶ ይንጸባረቃል።

ሁለቱ ሃገራት የልማት ዕርዳታቸውን በአርባና በሰላሣ ከመቶ መጠን ሲቀንሱ የኤኮኖሚና ልማት ትብብሩ የበጀት ሁኔታ በፍጥነት ይሻሻላል በሎ መጠበቁም የሚያዳግት ነው። በሌላ በኩል የዓለምአቀፉ ሰብዓዊ ድርጅት የኦክስፋም ባልደረባ ቶቢያስ ሃውስሺልድ እንደሚሉት በቁጠባው ያን ያህል በዙ ገንዘብ ማትረፍ የሚቻል ሆኖ አይደለም። ለነገሩ አብዛኞቹ የድርጅቱ ሃገራት የሚሰጡት የልማት ዕርዳታ ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው አንጻር ከአንዲት በመቶ ያነሰ ነው።

«ምንም እንኳ የቁጠባ ግፊት መኖሩን መረዳት ባያዳግትም ቅነሣው የድሃ ድሃ የሆኑትን ሃገራት የሚጎዳ እንዳይሆን ማሳሰቡ አልቀረም። በነዚያ ሃገራት ትንሽ የሚባልም ገንዘብ ጠቃሚ ክብደት አለው። በዚህ ቁጠባ የተነሣ ታዲያ ብዙዎች ፕሮዤዎችን ማራመዱ የማይቻል ነገር ነው የሚሆነው»

ጀርመን ለልማት ትብብር አብዛኛውን ገንዘብ ከሚያቀርቡት ቀደምት ሃገራት መካከል አንዷ ናት። ባለፈው ዓመት 14,5 ሚሊያርድ ዶላር ስታቀርብ ከአሜሪካ ቀጥላ ሁለተኛዋ ዓቢይ የልማት ዕርዳታ አቅራቢ መሆኗ ነው። የአገሪቱ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ዲርክ ኒብል ሰሞኑን በጉዳዩ ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃል ምልልስ የጀርመን የልማት ትብብር በጀት እየጨመረ እንደመጣ ነው ያስረዱት።

Dirk Niebel
ምስል dapd

«በ 2010, 2011 እና 2012 ያለማቋረጥ የኤኮኖሚ ትብብር ፌደራል መሥሪያ ቤታችንን በጀት ከፍ አድርገናል። መዋቅራዊ ለውጦች በማካሄድ ተግባራችንን ፍቱንና ብቁ ለማድረግ፤ እንዲሁም ባለው ገንዘብ የተሻለ ውጤት ላይ ለመድረስም ጥረናል። በጥር 2011 የጀርመን የልማት ድርጅት DED፣ የጀርመን ቴክኒካዊ ተራድኦ ተቋm4 GTZ እና የሥልጠናው ድርጅት ኢንቬንት ተዋሕደው የጀርመን ዓለምአቀፍ ትብብር ድርጅት ሆነዋል»

የሆነው ሆኖ በጥቅሉ ሲታይ በሚቀጥሉት ዓመታት ሂደት ለዓለምአቀፉ የልማት ትብብር የሚቀርበው በጀት እየጨመረ መሄዱ ብዙ የሚያጠርጥር ነው። የዓለም ኤኮኖሚ በወቅቱ ገና በበጎውና በክፉው መካከል የሚዋዥቅ በመሆኑ ብሩህ ጊዜ ለጊዜው ጎልቶ አያታይም። ስለዚህም ለአዳጊዎቹ መንግሥታት በተለይም በልማት ዕርዳታ ላይ ይበልጡን ጥገኛ ሆነው ለኖሩት ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት ሁኔታቸውን ማጤኑና አማራጭ መሻቱ ግድ እየሆነ ይሄዳል።

መሥፍን መኮንን