1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ደረጃቸው፣

ረቡዕ፣ መስከረም 10 2004

በ 20 አገሮች የተመሠረተውና አሁን 34 አገሮችን ያቀፈው ወደፊትም 5 መንግሥታትን ፤( ብራዚል፤ ቻይና ህንድ ኢንዶኔሺያንና ደቡብ አፍሪቃን ) ለመጨመር የተነሣሣው ዋና ጽ/ቤቱ በፈረንሳይ የሚገኘው፣ የኤኮኖሚና የልማት ትብብር ድርጅት(OECD)

https://p.dw.com/p/Rn2O
በዓለም ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ የተሰጠው፤ በእንግሊዝ ሀገር የሚገኘው፣ የ ኬምብሪጅ «ዩንቨርስቲ»፣ምስል picture-alliance / dpa

ከወዲያኛው ሰሞን ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት መሠረት፣ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት በብዙ ሺዎች ከሚቆጠሩት ዩኒቨርስቲዎች መካከል በተለይ ከ አንድ እስከ 20 ከተዘረዘሩት ታዋቂ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል፤ 13 ቱ የዩናይትድ እስቴትስ ሲሆኑ፤ ሳይራራቅ የብሪታንያ ዩኒቨርስቲዎች ይከተላሉ። ከብሪታንያ ቀጥሎ ሌሎቹ የአውሮፓ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደ ደረጃቸው ስማቸው ሠፍሯል። በቅርቡ በወጣው የጥናት ውጤት መሠረት፤ በያዝነው 2011 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ፤ በዓለም ውስጥ የብሪታንያው ኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የአንደኛነቱን ደረጃ ሲይዝ የአሜሪካው ሃርቫርድ ይከተለዋል። ይህን ጥናት ይፋ ያደረገው፤ «ኳኳሬሊ ሳይመንድስ » የብሪታንያ የተባለው ድርጅት ነው ። በዘንድሮው ጥናቱ፤ በዓለም ዙሪያ የ 600 ያህል ዩኒቨርስቲዎችን 26 የትምህርትና ምርምር ዓይነቶች መርምሯል።

ለ2 ኛ ጊዜ በተከታታይ የእንግሊዙ፤ የብሪታንያው የኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የመሪነቱን ቦታ ሲይዝ ፤ ከዚያም እስከ 10 የሚከተሉት ፤ ሃርቫርድ የማሳቹሰትስ የሥነ-ቴክኒክ ተቋም፣ ዩኒቨርስቲ፤የል ዩኒቨርስቲ፤ የብሪታንያው አክስፈርድ ዩኒቨርስቲ፤«ኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን»፣ «ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ለንደን» ፤ የቺካጎ ዩኒቨርስቲ የፔንስልቬንያ ዩኒቨርስቲ፤ የኒውዮርኩ ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ፤ ባጠቃላይ ከ መጀመሪያዎቹ 20 ዩኒቨርስቲዎች፤ ዩናይትድ እስቴትስ 13 ቱን ለማስቀደም በቅታለች። የካናዳው ማክጂል ዩኒቨርስቲ፣ 20ኛ ነው። በ 18ኛነት ደረጃ፣ ከብሪታንያ ውጭ፤ከሌላው የአውሮፓ ክፍል ዩኒቨርስቲዎች የዙሪኹ የሥነ-ቴክኒክ ተቋም ማለፊያ ስም አትርፏል። በአጠቃላይ ሲታይ የጀርመን ዩኒቨርስቲዎች ደረጃ መጥፎ አይደለም ። በዓለም ዙሪያ ምርጥ ከሚባሉት 300 ያህል ዩኒቨርስቲዎች፤ 24ቱ የጀርመን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ናቸው። ከእነዚህም መካከል፤ 4 ቱ፤ ደረጃቸው ከ1-100 ባሉት ውስጥ ነው። ለምሳሌ ያህል፤ የሃይድልበርጉ፤ Ruprecht-Karl ዩኒቨርስቲ፣ የሙዩኒኩ የሥነ ቴክኒክ ዩኒቨርስቲ፣ እንዲሁም የበርሊኖቹ፤ የሉድቪኽ ማክሲሚላን ዩኒቨርስቲና «ፍራዬ ዑኒቨርስቴት በርሊን » ማለፊያ ስም ያላቸው መሆናቸው የታወቀ ነው።

በ OECD በኩል የቀረበው፤ ዓለም አቀፍ የተማሪዎች የትምህርት ጥራትና ደረጃ ግምገማ፤ PISA(Programme for International Student Assesssment) እንደሚያስረዳው፤ ደቡብ ኮሪያ፤ ቻይና በተለይ የሆንግ ኮንግና ሻንጋይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤ በፍጥነት ደረጃቸው እጅግ ነው ከፍ ያለው።

ከ 34ቱ የ OECD አባል ሀገራት መካከል፤ የዩናይትድ እስቴትስን ያክል ለዩንቨርስቲ ተማሪ እጅግ በዛ ያለ ገንዘብ የሚያስከፍል የለም። ወጪው በየአይነቱ ተደምሮም ተቀንሶም ከ 100 ሺ ዶላር ቢበልጥ እንጂ አያንስም። በሌሎቹ የOECD አገሮች ግን ክፍያው በአማካይ ከ 50 ሺ ዶላር አይበልጥም። በትምህርትና ሙያ ብቃት ፤ ጀርመን በተለይ ጠና ባሉት ዜጎቿ ላቅ ያለ ደረጃ ነው ያላት። ከ OECD አንድርያስ ሽላይሸር የተባሉት ስለዚህ ጉዳይ ሲያስረዱ---

«በዓለም ዙሪያ፤ ከፍተኛ የትምህርትና የሙያ ሥልጠና ደረጃን ስንመለከት፤ ሰዎችን ስናነጻጽር፤ በሙያ ወይም በቀለም ትምህርት ረገድ፤ በ 55 እና 65 ዓመት መካከል የሚገኙት አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ ናቸው። ጀርመን በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ በዛ ያሉ በሙያ የሠለጠኑ ሰዎች ያፈራችና ያሠማራች ናት። በወጣቶች ረገድ ግን ፤ መጠኑ፣ ግማሽ በግማሽ ቀንሷል።»

የአፍሪቃ ዩኒቨርስቲዎች ደረጃስ እንዴት ነው?

በቅርቡ ከጠናቀርነው በመጥቀስ እናስታውሳችሁ።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ