1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም የመፀዳጃ ቤት ቀንና ኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ ኅዳር 9 2008

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ መሰረት ከዓለም ሕዝብ መካከል 2.4 ቢሊዮኑ ደረጃውን የጠበቀ የግል ንጽህና መጠበቂያ (sanitation) የላቸውም። ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሰው ልጆች ደግሞ ጨርሶ የመጸዳጃ አገልግሎት የላቸውም። የአፍሪቃ ሕብረት መዲና አዲስ አበባም ሆነ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የዚሁ ችግር ተጠቂ ናት።

https://p.dw.com/p/1H98w
Toilette in der Wüste
ምስል Fotolia

[No title]

በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባና የክልል ከተሞች አደባባዮች ‹‹መሽናት ክልክል ነው›› ፤‹‹መሽናት በሕግ ያስቀጣል›› እንዲሁም ‹‹አጥር ሥር የሚሸና ውሻ ብቻ ነው›› የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች ማንበብ የተለመደ ነው። ማስጠንቀቂያዎቹ ግን አንድ ነገር ይጠቁማሉ። በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ የመፀዳጃ ቤት እጥረትና የአጠቃቀም ጉድለት መኖሩን። እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ውስጥ ናቸው። ያሉትም ቢሆኑ የንጽህናና የአጠቃቀም ጉድለት ይታይባቸዋል።

በምዕተ-አመቱ የልማት ግቦች ኢትዮጵያ መሻሻሎች አሳይታበለች ከተባሉት ዘርፎች አንዱ የግል ንጽህና መጠበቂያ መንገዶች ማግኘት /Access to sanitation/ ነበር። ዶ/ር አበበ በየነ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ጤናና ሜዲካል ሳይንት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው።

Symbolbild - Slum in Afrika
ምስል Getty Images/T. Karumba

ዶ/ር አበበ በየነ ከሌሎች ሦስት የዘርፉ ምሁራን ጋር ያጠኑትና ባለፈው ግንቦት ወር ለህትመት የበቃ ጥናት በጎስቋላ የአዲስ አበባ መንደሮች ከሚኖሩ ዜጎች 11.4% ያህሉ ብቻ የተሻሻለ የግል ንጽህና መጠበቂያ መንገዶች ያገኛሉ ሲል ያትታል። ከአጠቃላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ደግሞ 41.2% የመጸዳጃ ቤቶችን የሚጨምረው የዚህ ግልጋሎት ተጠቃሚ ናቸው። በከተማዋ የጎስቋላ መንደሮች ከሚኖሩት 80.4% ዜጎች የሚያገኙት የመጸዳጃ ቤትና የውሃ አገልግሎት እጅግ ኋላ ቀር ነው። ዶ/ር አበበ በየነ የአገሪቱን የግል ንጽህና መጠበቂያ መንገዶች (access to sanitation) መለኪያዎች ጎዶሎ በመሆናቸው ሊስተካከሉ ይገባል የሚል አስተያየት አላቸው።

የተባበሩት መንግስታት የህጻናት አድን ድርጅት (UNICEF) በበኩሉ ያወጣው ዘገባ የትምህርት ቤቶች መጸዳጃ ቤቶች የጥራትም ሆነ የንጽህና ጉድለት እንዳለባቸው ያትታል። የመጸዳጃ ቤቶች ያሏቿውም ቢሆኑ የሴቶችና የወንዶችን የመለየት ችግር አለባቸው። በጥናቱ መሰረት ሴት ተማሪዎች በትምህርት ቤቶቻቸው ያላቸው የመጻዳጃ ቤት አገልግሎት ከወንዶቹ በአስር በመቶ ዝቅ ያለ ነው። ይህም ተማሪዎችን በተለይም ህጻናትን ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ አሊያም ንጽህናው ባልተጠበቀ ሁኔታ እንዲጸዳዱ ያስገድዳቸዋል። በተባበሩት መንግስታት የህጻናት አድን ድርጅት ጥናት ለናሙና ከተካተቱ 1,800 ትምህርት ቤቶች መካከል በአጠገባቸው የእጅ መታጠቢያ ውሃ ያላቸው 4.4 በመቶው ብቻ ናቸው።

የውሃ ወለድ በሽታዎች በዓመት እስከ 500,000 የሚደርሱ ህጻናትን ለሞት ይዳርጋል። በኢትዮጵያ ከሚከሰቱት በሽታዎች ከ60-80 በመቶው በውኃና የንጽህና ጉድለት የሚመጡ ናቸው።

Sewage, Haiti
ምስል Letting Go of Control/CC BY-NC-ND 2.0

ዶ/ር አበበ በየነ በመከላከል ላይ ላተኮረው የኢትዮጵያ መንግስት የጤና ፖሊስ አድናቆት አላቸው። ቀስ በቀስ በመለወጥ ላይ የሚገኘው የከተሜ ኑሮ በመጸዳጃ ቤቶች አያያዝና አጠቃቀም ላይ የግንዛቤና ተግባራዊ ለውጥ በማምጣት ላይ መሆኑንም ይስማማሉ። ይሁንና በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች ለመቅረፍ በንድፈ-ኃሳብ ደረጃ የተቀመጡት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው ይመክራሉ።


እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ