1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም የአየር ንብረት ዐቢይ ጉባዔና ተስፋው

ረቡዕ፣ ኅዳር 24 2007

ላቲን አሜሪካዊቷ ሀገር ፔሩ ፣ ከትናንት በስቲያ አንስቶ ለ 12 ቀናት የዓለምን የአየር ንብረት ጉባዔ ስታስተናግድ ትሰነብታለች። የ 195 አገሮች ተወካዮች ናቸው በዚህ ዐቢይ ጉባዔ የሚመክሩት። ለተፈጥሮ አካባቢ ፤ ለየብስ ባህርና ከባቢ አየር

https://p.dw.com/p/1Dym9

መጠበቅ ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞም ፣ ለሰዎች ቀጣይ ሕልውና የሚቆረቆሩ ጠበብት ብዙ ሲወተውቱ ከቆዩ በኋላ ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት የበላይ ተቆጣጣሪነት ፤

Kohlekraftwerk Mehrum
ምስል picture-alliance/dpa/Julian Stratenschulte

ሪዮ ደ ጃኔሮ፤ ብራዚል ውስጥ፣ የ«ፕላኔትክን አድን » ዓይነት ዐቢይ ጉባዔ፤ እ ጎ አ ከ ሰኔ 3-14 1992 ዓ ም ተካሄደ። ከዚያም እ ጎ አ ፣ በታኅሳስ ወር 1997 ዓ ም፤ ኪዮቶ ፤ ጃፓን ውስጥ፤ ለከባቢ አየር ግለት አስተዋጽዖ ያለውን የተቃጠለ አየር CO2 ልቀትና ተመሳሳይነት ያላቸውን ጋዞች ፣ በኢንዱስትሪ በበለጸጉት ሀገራት በተወሰነ ደረጃ ለመቆጣጠር ስምምነት ላይ መደረሱና እ ጎ አ ከየካቲት 16,2005 አንስቶ ተግባራዊ መደረጉ የሚታወስ ነው፤ እርግጥ አየር በመበከል ግንባር ቀደም መሆናቸው ከሚነገርላቸው መካከል ዩናይትድ ስቴትስ የኪዮቶውን ውል አልፈረመችም። ካናዳም እ ጎ አ ታኅሳስ 13,2011 ከውሉ ራሷን አግልላለች።

የኪዮቶው ውል፤ የቀንድና ጋማ ከብቶች ብዛት፤ የደን መመንጠርና የመሳሰለው ለከባቢ አየር ጠነቅ ያለው መሆኑን ይጠቅሳል። ወደ ከባቢ አየር በመትነን እየተቀላቀሉ ጉዳት ያደርሳሉ የተባሉት ጋዞች፤ ነዳጅ ዘይት፤ የተቃጠለ አየር(CO2)፣ ሜቴን ጋዝ (CH4) ለሣቅ ኮርኳሪ መሆኑ የሚነገርለት ናይትሮጂን ዳይኦክሳይድ(N2O) የድኝና ፍሎሪን 6 እጥፍ ቅልቅል መሆኑ የሚነገርለት ጋዝ (SF6)ና የመሳሰሉ ናቸው። ከኪዮቶው ጉባዔና ስምምነት በኋላ ፣ በ 2009 በደንማርክ መዲና በኮፐንሄገን ከዚያም በደርበን ፤ ደቡብ አፍሪቃ ቀጥሎም በቐጠር በ 2012 ፤ ዘንድሮ ደግሞ ፤ ማለት ከሰሞኑ በፔሩ መዲና በ ሊማ በመካሄድ ላይ ነው። ፕላኔታችንን ለመታደግ የሚያስችል መላ ለመሻት እ ጎ አ በ 2009 በኮፐንሔገን የተከሄደው ጉባዔ ፣ ዐቢይ ተስፋ አሳድሮ ከከሸፈ ከ 5 ዓመታት ወዲህ የአሁኑ የፔሩው ስብሰባ የያኔው የኮፐንሄገኑ ተስፋ እንደገና እንዲያንንሠራራ ማብቃቱ በመነገር ላይ ነው። አሁን በፔሩ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የዓለም የአየር ንብረት ተመላካች ጉባዔ ለውጤት መደላድል ይሆን ዘንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን፣ ባለፈው መስከረም ኒው ዮርክ ላይ ልዩ የአየር ንብረት ነክ የመሪዎች ጉባዔ እንዲካሄድ አብቅተው እንደነበረ አይዘነጋም።

Dürre in Brasilien
ምስል AFP/Getty Images/N. Almeida

ቻይናና ዩናይትድ ስቴትስ ፤ ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር መግቢያ ላይ ፣ በአየር ንብረት ጥበቃ ረገድ ለመተባበር ፈቀድኝነታቸውን ማሳየታቸው የሚያነቃቃ ክሥተት መሆኑ ነበረ ያኔ የተገለጠው። መንግሥታት አቀፍ የሆነው ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ነክ ምክክርም (IPCC) አስቸኳይ ርምጃ መውሰድ የግድ እንደሚል ነው ያስገነዘበው።በፖትስዳም ፤ ጀርመን የአየር ንብረት ለውጥ ስለሚያስከትለው ሳንክ ምርምር የሚያካሂደው ተቋም ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር እሽቴፋን ራምስቶርፍ፣ እንዲህ ይላሉ----

«ባለፉት 100 ዓመታት በዓለም ዙሪያ የምድራችን የሙቀት መጠን በአንድ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ከፍ ማለቱን ተገንዘብናል። የዓለም ውቅያኖሶች የባህር ልክም፤ በመቶ ዓመት ውስጥ በ 20 ሴንቲሜትርከፍ ማለቱን ዐይተናል። ከተራሮች የተቆለለ በረዶ እየቀለጠ በመሟu።ሽ ላይ ነው። የአርክቲክ የበረዶክምር እንዲሁም የግሪንላንድና የአንታርክቲካ የበረዶ ሽፋን መጠን እየተቀነሰ ነው። ይህ በበኩሉ የባህርልክ መጠን ክፍ እንዲል አስተዋጽዖ ያደርጋል። በየዘርፉ፣ ያልተለመዱ መጠን ያለፉ ሁኔታዎች መከሠታቸውን በመታዘብ ላይ ነን። ከተለመደው የወቅቶች የአየር ንብረት ይዞታ ባፈነገጠ ሁኔታ አንዳንድ ወራት የሙቀታቸው መጠን አይሎ ክብረ ወሰን የተመዘገበበት ሁኔታ አለ።»

የምድርችንን አየር ንብረት መዛባት ለማስተካከል የተገባው ቃልና የሚወሰደው ርምጃ የቱን ያህል ግቡን ለመምታት ያስችላል?የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ እ ጎ አ እስከ 2025 ከፋብሪካዎችና ከመሳሰለው የሚወጣውን የተቃጠለ አየር ልቀት መጠን እ ጎ አ በ 2005 ከነበረው፤ በ 26 ፤ 28 ከመቶ እንዲቀነስ የሚደረግ መሆኑን አስታውቀዋል። ቻይና ከፋብሪካ የሚወጣ የተቃጠለ አየር (CO2) ቅነሣ ርምጃ ለመውሰድ የምትፈልገው እ ጎ አ ከ 2030 ጀምሮ መሆኑን ነው ያስታወቀች። አሳሳቢ የአየር ብክለትን በመቃወም ቻይናውያን ያለተፈቀደ ሰልፍ እስከማካሄድ የደረሱበት ሁኔታ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ሳያስደነግጥ እንዳልቀረም የአየር ጥና ት ጠበብትና የጀርመን መንግሥት ዜና ምንጮች መታዘባቸውን ጠቁመዋል።

Symbolbild Somalia Wüste Entführung
ምስል picture-alliance/Yannick Tylle

የምድራችን ግለት እየናረ በመኼድ የ 2 ዲግሪ ጭማሪ እንዳያሳይ ለመግታት ታዲያ መላው ዓለም እ ጎ አ እስከ 2050 ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ የተቃጠሉ ጋዞችን መጠን ከ 40 እስከ 70 ከመቶ እንዲቀነስ፤ እስከ ምዕተ ዓመቱ ፍጻሜ ደግሞ የሚለቀቀው የተቃጠለ አየር መጠን፤ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጠበቃ ነክ ም/ቤት እንዳስገነዘበው ፣ ከሞላ ጎደል ደረጃው ወደ ዜሮ እንዲጠጋ ማብቃት ግድ ይላል። በተባበሩት መንግሥታት ተቆጣጣሪነት የሚመራው ጉባዔ አንዱ ዐቢይ ተግዳሮት፣ የበለጸጉ ምዕራባውያን መንግሥታትንና አሁን የዕድገት ምጥቀት በማሳየት ላይ የሚገኙትን ቻይናንና ሕንድን ኀላፊነት የማሸከሙ ጉዳይ ነው። እጅግ የደኸዩት መንግሥታትም ፤ የምድራችንን ግለት ይበልጥ በማያባብስ መልኩ ኤኮኖሚአቸውን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ እንደሚኖርባቸው የሚታመንበት ጉዳይ ነው። በዚህ በ3ኛ ደረጃ ከሚጠቀሱት ሃገራት መካከል ራሷ አስተናጋጂዋ ሃገር ፣ ፔሩ ትገኝበታለች። ፔሩ ፤ በኤንደስ ተራሮች የተቆለለ በረዶ በፈጣን ሁኔታ መቅለጥ፣ 70 ከመቶ ዜጎቿ ለሚኖሩበት ለምድረበዳማው ጠረፏ በቂ ንፁህ የሚጠጣ ውሃ ማቅረብ እንዳይሳናት ሠግታለች። በውሃ ኃይል ለሚሠራው የኤልክትሪክ ኃይል ማመንጫ አውታርና ምግብን አስተማማኝ ማድረግ ለሚኖርበት ግብርናም ሥጋትን ነው የደቀነው። የፔሩ ተደራዳሪዎች የሆነው ሆኖ፤ በመጪው ዓመት በፓሪስ ፈረንሳይ እንደሚካሄድ በሚጠበቀውና ውጤት የሚያስገኙ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ለሚጠበቀው የሊማ ቀጣይ ዐቢይ ጉባዔ፣ የሚቀርቡ ሆኖም በመሃሉ የሚስተካከሉ ሰነዶችን ማቅረባቸው ነው የተገለጠው። ላቲን አሜሪካና የካሪቢያ ደሴቶች፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ፣ ከእነርሱ በኩል ወደከባቢ አየር የሚለቀቀው የተቃጠለ አየር ከ 10 ከመቶ በታች ነው። በኤንደስ ተራሮች በረዶ መመናመን የሚደርሰው የኤኮኖሚ ኪሣራ፤ ባለንበት ምዕተ ዓመት አጋማሽ ገደማ በያመቱ ከ 100 ቢሊዮን ዶላር እንደማያንስ ነው የሚገመተው። አሁንም ፕሮፌሰር ሽቴፋን ራምስቶርፍ---

Isaland Snaefellsjökull Vulkan und Gletscher
ምስል Fotolia/frenk58

«የአየር ንብረት ለውጥ ፣ እዚህ በሰዎች ላይ ጫና በማስከተል ላይ ነው። ይህም ፣ በመጠኑ የዓለም የሙቀት መጠን በአንድ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ከፍ እንዳለ ነው። የዚህን ሂደት ካልገታን፤ የምድረ ግለት ከ2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይም ሊያሻቅብ ይችላል። እናም ባለፉት 11,700 ዓመታት ገደማ ፤ የሰው ቁጥር እጅግ እየጨመረ በመጣበት በሰነድ ተይዘው በሚገኙ የሰው ልጆች ታሪኮች የተፈጸሙ ፣ የጥፋት ውሃ መሰል አስከፊ ሁኔታዎች እንዳያጋጥሙ ነው የሚያሠጋው።»

የዓለም የህዝብ ቁጥር አሁን 7,2 ቢሊዮን ገደማ የደረሰ ሲሆን እስከያዝነው ምዕተ ዓመት ፍጻሜ 10,85 ከሞላ ጎደል 11 ቢሊዮን ይደርሳል። የዓለምን ሕዝብ የየደቂቃና ሴኮንድ ጭማሪ የሚያሰላው መለኪያ (Worldometers) እንደሚጠቁመው ከሆነ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የህዝቧ መጠን ከ 97 ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ በላይ ነው። በሕዝብ ብዛት ።በዓለም ውስጥ ያላት ደረጃም 13ኛ ነው። ናይጀሪያ ከዓለም 7ኛ ስትሆን የህዝቧም ቁጥር ከ 180 ሚሊዮን በላይ መሆኑ ነው የሚነገረው። 15ኛ ፤ ግብፅ ፤ የህዝቧ ብዛት ወደ 84 ሚሊዮን እንደሚጠጋ ተመልክቷል። አንደኛ ቻይና 1,39 ቢሊዮን ሁለተኛ ሕንድ 1,27 ቢሊዮን ሦስተኛ ዩናይትድ ስቴትስ 323 ሚሊዮን 659,298 ።

Nationalpark Los Glaciares in Patagonien, Argentinien
ምስል Fotolia/alfotokunst

ታዲያ ሰሞኑን በሊማ ፔሩ በመካሄድ ላይ ያለው ጉባዔ በመጪው ዓመት እ ጎ አ ከኅዳር 30 እስከ ታኅሳስ 11 ፈረንሳይ ውስጥ ለሚካሄደው ዐቢይ ጉባዔ ለስምምነት የሚያበቃውን ሰነድ ሳያቀርብ እንደማይቀር ነው የተነገረው። የፓሪሱ ዓበይ ጉባዔ ዓላማ በአየር ንብረት አያያዝ ረገድ ፤ በሁሉም መንግሥታት ስምምነት የሚደረግበት አሣሪ ህግ እንዲጸድቅ ማብቃት ይሆናል።

የሳይንስ ጠበብት እንደሚተነብዩት ከሆነ ፤ ከሞላ ጎደል አሁን ባለው የአየር ሙቀት መጠን ምድራችን ለሰዎችና እንስሳት መኖሪያ ተስማሚ ሆና የምትቀጥለው ለሚመጡት 500 ሚሊዮን ዓመታት ገደማ ነው። የፀሐይ የግለት መጠን በሚመጡት 1,1 ቢሊዮን ዓመታት በ 10 ከመቶ ከ 3,5 ቢሊዮን ዓመታት በኋላም በ 40 ከመቶ ከፍ ስለሚል ሐይወት ያለው ፍጡር ሁሉ ያከትምለታል ማለት ነው። በ 4,5 ቢሊዮን ዓመታት ውስጥ ደግሞ በምድራችን ላይ የተቋረው ከ 70 ከመቶ በላይ የሆነው ውሃ ውቅያኖሶች ከአነአካቴው ይነጥፋሉ።

Symbolbild Klimawandel
ምስል Reuters

ከፀሐይ በ 3ኛ ረድፍ ላይ 150 ሚሊዮን ኪሎሜትር ያክል ራቅ ብላ የምትገኘው ምድራችን አማካይ የሙቀት መጠንም 70 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊደርስ እንደሚችል ነው ሟርት ይሁን ትንቢት ወይም ሊከሠት የሚችል እውነታ ፣ ጠበብቱ የሚነግሩን! እንዲያውም በ 7 ቢሊዮን ዓመታት የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት እጅግ በማየል ፣ ለርሷ ይበልጥ ቀረብ ያሉት ሁለት ፕላኔቶች፣ ሜርኩሪና ቬኑስ ክቦቹ ፕላኔቶች ፀሐይን ይመስል ወደ ፍምነት ይሆናል የሚለወጡት። የሚያይለው የፀሐይ ግለትም የምድርን ምሕዋር ያዳርሳል። በሕዋ የፀሐይ ነፋስ በሚሰኘው የአቶም ፍንጣቂ ማየል ሳቢያ የፀሐይ ቁሳዊ አካል 30 ከመቶው ይቀነሳል ወይም ይጨማተራል ማለት ነው። ይህ ሁሉ ለዛሬው ዘመን ሰዎች ተረት እንጂ እውን የሚፈጸም የተፈጥሮ ሂደት ሆኖ መታሰቡ ያጠራጥራል።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ