1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓርብ ዕለቱ የቦምብ ፍንዳታ በአንዋር መስጊድ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 2 2008

ትናንት በአዲስ አበባ ታላቁ አንዋር መስጊድ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ በትንሹ 17 ሰዎች መጎዳታቸው ተገለጸ። የመንግስት ኮምዩንኬሽን ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ከተጎዱት 17 ሰዎች መካከል ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው መኖራቸውን ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/1HMQl
Addis Abeba
ምስል picture alliance / landov

አቶ ጌታቸው ረዳ «እስካሁን ጥቃቱን ማን እንደፈጸመው የምናውቀው ነገር የለም።» ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል። በመርካቶ በሚገኘው ታላቁ አንዋር መስጊድ የደረሰው የቦምብ ፍንዳታው ከዓርብ የጁምዓ ጸሎት በኋላ ነበር። ለመንግስት ቅርበት ያለው ሬዲዮ ፋና በበኩሉ በፍንዳታው የተጎዱ ሰዎች ቁጥር 24 መሆኑን ዘግቧል። በፍንዳታው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በቅዱስ ጳውሎስና ተክለሃይማኖት ሆስፒታሎች ህክምና እንደተደረገላቸው ዘግቧል። እስካሁን ለፍንዳታው ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም። በአደጋው በአምስት ሰዎች ላይ ከባድ በ19 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የመቁሰል አደጋ መድረሱን የዘገበው የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቭዥን የፍንዳታው መንስዔ «ማንነቱ ባልታወቀ ግለሰብ የተወረወረ ቦምብ» መሆኑን የፌደራል የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል መግለጫን በመጥቀስ ዘግቧል።

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ