1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዕዳ ምሕረት ትናንትና ዛሬ

ረቡዕ፣ የካቲት 20 2005

በገንዘብ ችግር ላይ ለወደቀ አገር የዕዳ ምሕረት ማድረጉ ከ80ኛዎቹ ዓመታት ወይም ከቅርቡ ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ ወዲህ የተለመደ ነገር አይደለም። ዛሬ ከቀደምቱ በኢንዱስትሪ ልማት ከበለጸጉ መንግሥታት መካከል አንዷ የሆነችው ጀርመን፤ በተጨባጭ

https://p.dw.com/p/17mVD
ምስል picture-alliance/dpa

ምዕራብ ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት የዕዳ ምሕረት ባታገኝ ኖሮ የኤኮኖሚ ተዓምር የሚል ስያሜ ያተረፈ የቀለጠፈ የምጣኔ ሃብት ዕርምጃ ለማድረግ ባልቻለች። አገሪቱ በከፊል ከጦርነቱ በፊትና በከፊልም ከዚያ በኋላ 30 ሚሊያርድ ዶቼ ማርክ የሚጠጋ የጊዜው ጠላቶቿን ጨምሮ የሰባ አገራት ዕዳ ተሸካሚ ነበረች።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጥፋት በኋላ የተወለደችው አዲሲቷ ፌደራል ሬፑብሊክ ጀርመን እንግዲህ በመጀመሪያዎቹ ቀውጢ ዓመታት ከመጠን በላይ ከባድ ዕዳ የተጫናት አገር ነበረች። እናም ለዕድገቷ አስፈላጊ የሆነውን አዲስ ካፒታል ለማግኘት ከማትችልበት ከባድ ሁኔታ ላይ ትደርሳለች። ታዲያ አገሪቱ ከዚህ ቀውስ ልትላቀቅ የቻለችው በጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 27 ቀን 1953 ዓ-ም ለንደን ላይ በተካሄደ የአበዳሪዎች ጉባዔ የዕዳ ምሕረት ከተደረገላት በኋላ ነበር።

ምዕራብ ጀርመን በጊዜው 15 ሚሊያርድ ማርክ ዕዳ ይሰረዝላታል። ታሪካዊው ዕለት ዛሬ 60ኛ ዓመቱን ሲደፍን የጀርመን የኤኮኖሚ ዕድገት ተዓመር በር ከፋች ሆኖ ነው የሚታየው። ዕውነትም የኤኮኖሚ ዕድገት ተዓምር!

በዚህ በጀርመን ለታዳጊ ሃገራት የዕዳ ምሕረት የሚሟገት erlassjahr.de በመባል የሚታወቅ ስብስብ ተግባር የፖለቲካ አቀናባሪ ዩርገን ካይዘር መለስ ብለው ሲያስታውሱ የዕድገቱ ተዓምር ምሥጢር የሕዝቡ ታታሪነትና የአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ መሆኑን መማራቸውን ነው የሚናገሩት። እርግጥ የጦርነቱን ታሪክ የማድበስበሱን ዝንባሌ አይቀበሉትም። ለማንኛውም ቢቀር ታታሪነቱ ከጊዜው ትውልድ አንጻር ዕውነት የማያጣው ነው።

ጀርመን በዚህም በዚያም የዕዳ ምሕረቱን ተጠቅማ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለብልጽግና በቅታለች። ታዲያ በጀርመን የዕዳውን መቀነስ አስከትሎ የታየው የዕድገት ተዓምር ዛሬ ለምን በታዳጊ ሃገራት አይሳካም? በንጽጽር ሲታይ የ 50ኛዎቹን ዓመታትና የዛሬውን አንድ የሚያደርገውና የሚለየው ለመሆኑ ምንድነው? እነዚህንና አፍሪቃ ውስጥ ሙስና ወይም የበጎ አስተዳደር ጉድለት በሚያስከትለው ችግር ዩርገን ካይዘርን ዛሬ አነጋግሬ ነበር። እንደርሳቸው አባባል የዛሬ 60 ዓመት በጀርመንና ዛሬ በታዳጊው ዓለም ያለው የዕዳ ሁኔታ በእርግጥም ተመሳሳይነት አያጣውም።

«ከመጠን በላይ ዕዳ የተጫነው አገር ሲባል የትም ቢሆን ከባድ ዕዳ የተሸከመ አገር ማለት ነው። እናም ብዙ ዕዳ ያለባቸው ሃገራት ያለ ችግር ዕዳቸውን መልሰው ሊከፍሉ አይችሉም። ይህ ደግሞ ያኔ በ 1953 ዓ-ምም ሆነ ዛሬ ሶሥተኛው ዓለም እየተባለ በሚጠራው የዓለም ክፍል የተለያየ አይደለም። ዕዳ ላይ የወደቁት ሃገራት ቁጥርና ባህርይ ግን እርግጥ ይለያያል»

ዩርገን ካይዘር ቀጠል አድርገው እንደሚያስረዱት በ 80ኛዎቹ ዓመታት ከባድ ችግር የገጠማቸው በርካታ ሃገራት ነበሩ። ሆኖም ዛሬ ያን ችግር ብዙዎቹ አልፈውታል።

«በአሁኑ ወቅት በዕዳ ችግር ከመጠን በላይ ተጠምደው የሚገኙት ዋነኞቹ አንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት ናቸው። እነዚሁ በጊዜው በዓለም ባንክና በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የዕዳ ቅነሣ ፕሮግራም ውስጥ ቢጠቃለሉም አሁን እንደገና ችግር ገጥሟቸው ነው የሚገኙት። ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ የመካከለኛና ምሥራቅ አውሮፓ ሃገራትም በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ናቸው። እነዚህ ሃገራት ደግሞ እንደ ግሪክ ሁሉ ያኔ ጀርመን ከነበረባት በበለጠ የዕዳ መስፈርት ላይ ነው የሚገኙት»

እርግጥ ጀርመን የዕዳ ምሕረቱን ስታገኝ ጊዜው ሌላ ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት በ 50ኛዎቹ ዓመታት! ወቅቱ ቀዝቃዛው ጦርነት በአፍላ ደረጃው የሚገኝበት ነበር። ታዲያ ዛሬ ጊዜው ተለውጧል። እንዲህም ሆኖ ግን አፍሪቃን ስናስተውል ለምሳሌ ቡድን-ስምንት መንግሥታት በዘጠናኛዎቹ ዓመታት በርከት ላሉ ሃገራት ሰፊ የዕዳ ቅነሣ ነበር ያደረጉት። ግን አልሰራም፤ ችግሩ እምብዛም አልተወገደም። ለምን? ዩርገን ካይዘር በጉዳዩ ቅይጥ አስተያየት ነው ያላቸው።

«የዕዳ ምሕረቱ በአንዳንድ ሃገራት ሰርቷል ባይ ነኝ። በወቅቱ በዚህ ዕዳን በማቃለል ጥረት ውስጥ የተካተቱት ሃገራት ቁጥር አርባ ገደማ ይጠጋል። ታዲያ የተወሰነ የስኬት ታሪክ መኖሩም አልቀረም። ለምሳሌ ያህል ዛምቢያ፣ ታንዛኒያ ወይም ጋና መዋቅራዊ መሻሻል ሲያደርጉ የዕዳው ምሕረት የኤኮኖሚ ዕድገት እንዲያደርጉም በጅቷቸዋል»

በሌሎች አገሮች ይሁንና ሁኔታው ከበድ ያለ ነው። ዩርገን ካይዘር እንደሚሉት ችግሩ በአንድ በኩል ከበጎ አስተዳደር እጦት ጋር በጣሙን የተሳሰረ ሲሆን የዕዳው ምሕረት የሚገባውን ያህል ሰፊ አለመሆኑም ሌላው የችግሩ መንስዔ ነው።

«ለነገሩ መንግሥታቱ ሙሉ ዕዳቸው ተሰርዞላቸዋል ማለት አይደለም። የዓለም ባንክና የምንዛሪው ተቋም ባስቀመጡት መስፈርት መጠን ነው የተቀነሰው። በዚሁ የተነሣም ብዙው ዕዳ እንዳለ ሲቀጥል አንዳንዶቹ ሃገራት ለምሳሌ የቅርቡ የፊናንስ ቀውስ ታክሎበት ሊሸከሙት አልቻሉም። እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ቡሩንዲ፣ ጋምቢያና ቡርኪና ፋሶ ይህ ችግር የገጠማቸው ሃገራት ናቸው»

የበጎ አስተዳደር ጉድለት በተለይም በአፍሪቃ ዓቢይ የዕድገት መሰናክል ሆኖ ነው የሚገኘው። መንግሥታዊው ሙስናም ሲበዛ ስር የሰደደ ነው። ታዲያ ይህ ደግሞ የዕዳ ምሕረቱን ተጠቅሞ ማሕበራዊ ዕድገትን ለማራመድ እንዳይቻል መሰናክል መሆኑ አልቀረም። ዩርገን ካይዘር እንደሚሉት ደግሞ የዕዳው ቅነሣ መጠንም የራሱ ድርሻ አለው።

«አዎን፤ ሙስና ታላቅ ድርሻ አለው። ምንም እንኳ ድርጊቱ የአፍሪቃ ሃገራትን ብቻ የሚመለከት ባይሆንም! እንግዲህ ሙስና የአፍሪቃ ፍጡር ብቻ አይደለም። ግን ለችግሩ ትልቅ ድርሻ አለው። ሌላው ጥያቄ ደግሞ የዕዳ ምሕረት ሲደረግ በዕውነት በሚገባው መጠን ተደርጓል ወይ የሚል ይሆናል»

ችግሮቹ ተደርድረዋል። ነገር ግን የዕዳ ምሕረቱን በሚገባ ለመጠቀም በአፍሪቃ ምን ቢደረግ ይበጃል? እንደ ዩርገን ካይዘር ከሆነ፤

«ብዙ ነገር ከወዲሁ ተለውጧል ለማለት ይቻላል። በ 80ኛዎቹ ዓመታት የፓሪስ ክበብ የተሰኘው የበለጸጉ መንግሥታት ስብስብ ባወጣው መርህ መሠረት የመጀመሪያው ከፊል የዕዳ ምሕረት ሲደረግ ያቀረቡት ቅድመ-ግዴታም ተረጂዎቹ ሃገራት ሃብትን ከታች ወደ ላይ እንዲያከፋፍሉ የሚጠይቅ ነበር። እርግጥ ሁኔታው አንዳንዶች እንዲካብቱ ነው ያደረገው»

ዩርገን ካይዘር ቀጠል አድርገው እንደሚያስረዱት ከሆነ በተከታዩ አሠርተ-ዓመትም ወሣኝ ዕርምጃ ተደርጓል ለማለት የሚያዳግት ነው። በተለይም የበጎ አስተዳደር ጉድለት መቀጠል ሁኔታውን እንደሚያከብደው መገመቱ አያዳግትም።

«ከ 90ኛዎቹ ዓመታት ወዲህ ድህነትን በመታገሉ ፖሊሲ ረገድ ጠቃሚ ዕርምጃ ተደርጓል ሊባል ይችላል። ግን በጎ አስተዳደር ይስመር አይስመር በሁኔታው የሚወስኑት አሁንም የዓለም ባንክና የምንዛሪው ተቋም ናቸው። እነዚህ ሁለት ታላላቅ ተቋማት ደግሞ ሙስና ውስጥ ከተዘፈቁ መንግሥታት ሲወግኑ ነው ባለፉት ዓመታት የታዩት»

እንግዲህ ለልማት ትብብር እንደ ቅድመ-ግዴታ በየጊዜው ሲነሣ የቆየው የበጎ አስተዳደር መስፈንና የሙስና መወገድ መፈክር በአብዛኛው ለይስሙላ ሆኖ ቀርቷል ማለት ነው። ይህ ሁኔታ ካልተለወጠ በያዝነው ምዕተ-ዓመት ድህነትን ያለፈ ታሪክ ለማድረግ የታለመው ህልም ቅዠት ሆኖ መቅረቱ ነው። ጀርመን የዛሬ 60 ዓመት በተደረገላት የዕዳ ምሕረት የተፈጠረውን ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅማ የኤኮኖሚ ተዓምር ሰርታለች። ተዓምሩ ለመሆኑ እንዴትና ለምን ተሣካ፣ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም ሊሰምር የቻለው አገሪቱ ያገኘችው አዲስ ካፒታል ወደ ግለሰቦች ኪስ በመግባት ፈንታ ለአገር ልማት ስራ ላይ በመዋሉ ነው። ይህ ትምሕርት ሊሆን ይገባዋል።

መሥፍን መኮንን
አርያም ተክሌ

Symbolbild Korruption Afrika
ምስል AP
Wirtschaftswunder 50er Jahre
ምስል dpa - Bildfunk
Deutschland Präsentation des Schuldenreports 2009 in Berlin von Jürgen Kaiser
ምስል erlassjahr
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ