1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዕዳ ጫና መፍትሄው የፋይናንስ ዘርፉ ወደ ግል መዛወር

ማክሰኞ፣ የካቲት 5 2011

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብድር ጫና ካለባቸዉ ጥቂት የአፍሪቃ ሐገራት አንዷ መሆንዋ ይነገራል። ኢትዮጵያ ያለባትን የውጭና የሀገር ውስጥ እዳ ለመክፈል ያላት አማራጭና የመክፈል አቅሟ ታዛቢዎችን እያነጋገረ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3DE7W
Nil Dammbau in Äthiopien Archiv 28.05.2013
ምስል William Lloyd-George/AFP/Getty Images

የብድር ዕዳ ጫና ለማቃለል ዘርፉን ወደ ግል ማዛወር

የኢትዮጵያ የብድር እዳ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱ  የብዙዎች ስጋት ሆኗል።አሁን ያለባት ዕዳ 1.4 ትሪሊዮን ብር ደርሷል። በየዓመቱ የምትበደረው የብድር መጠን እየቀነሰ ቢመጣም ከዚሕ ቀደም የተበደረችዉን ባለመክፈሏ  ዕዳዉ ዛሬም እንደተቆለለ ነው። መንግስት፣ ብድሩ ለመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ለንግድ እንቅስቃሴ እና ግዙፍ ለሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች ማከናወኛ ውሏል ባይ ነዉ። በተባበሩት መንግስታት የአፍሪቃ ጉዳይ ከፍተኛ አማካሪ የነበሩት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሃተስፋ ለ DW እንደነገሩት፣ ዕዳዉ የተከመረዉ መንግስት  የተለያዩ ከፍተኛ ፕሮጀክቶችን በተመሳሳይ ወቅት በአንድ ጊዜ ግንባታ በመጀመሩ ነዉ። «አብዛኛው ብድሮች የዋሉበት ከፍተኛ መንግሥት የሚያሰራቸው ፕሮጀክቶች ላይ ነው። የሀይል ማመንጫ ግድቦች በሙሉ በአንድ ጊዜ መሰራት ነበረባቸው ወይ የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል። አንድ መንግሥት ብድር በሚበደርበት ጊዜ ያለውን ፖሊሲ ተከትሎ ነው መሄድ ያለበት።» ሀገሪቷ ያለባትን ዕዳ በአጭር ጊዜ ለማቃለል መንግስት የፋይናንስ ዘርፉን በማሻሻልና ነጻ በማድረግ ወደ ግሉ ዘርፍ መዛወር እንዳለበት ዶ/ር ቆንጠንጢኖስ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። መንግሥት የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ማድረግ ይኖርባታል ይላሉም። «ሀገሪቱ ስትበደራቸው የነበረው በአጭር ጊዜ የሚደርሱና ወለድ የሚከፈልባቸው ናቸው። ይሄ ነገር መታሰብ ነበረበት። በተለይ ከቻይና የሚመጡ ብድሮች በአብዛኛዎቹ አሁን መከፈያ ጊዜያቸው ስለደረሰ የቻይናም ኢኮኖሚ መንገዳገዱ ሊሰጥ የሚችለው ተጨማሪ መዋለ ነዋይ ለኢትዮጵያ ሆነ ሌሎች አፍሪካ ሀገሮች እየቀነሰ መቷል።» አቶ አቢስ ጌታቸው በልማት ምርምር ኢንስቲትዮት በኢኮኖሚ ረዳት ተመራማሪ ናቸው። እሳቸውም ዕዳዉን ለማቃለል የፋይናንስ ተቋማት ወደ ግሉ ዘርፍ ይዛወር የሚለዉን ሐሳብ ይደግፋሉ። «በአፋጣኝ ያሉብንን ዕዳዎቻችን ለመክፈል ትልቁ አማራጭ ዘርፉን ወደ ግል በማዛወር ከመንግሥት እጅ ማውጣት አማራጭ ሊሆን ይችላል።» ይሄው የብድር እዳ መዘዝ በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ የእቃዎች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አድርጓል፤ በዚህም በህዝቡ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳመጣ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎቹ ይስማማሉ። 

 

ነጃት ኢብራሂም

ነጋሽ መሐመድ