1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ «ሴቢት» በሐኖፈር

ረቡዕ፣ የካቲት 27 2005

በየጊዜው የሚቀርቡ አዳዲስ የረቂቅ ሥነ ቴክኒክ ውጤቶች፣ የሳይንሱንና የሥነ ቴክኑኩን ዓለም ፣ በእጅጉ እየለውጡት ነው። ባለፈው ጥር ወር መግቢያ ላይ ለ 4 ቀናት ያህል በላስ ቬጋስ ፣ ካሊፎርኒያ፤ ዩናይትድ እስቴትስ ፣ Consumer Electronics

https://p.dw.com/p/17sHc
ምስል Reuters

Show (CES)ከዚያም በባርትሴሎና ፤ እስፓኝ ፣ ከየካቲት 18 እስከ  25,2005 ዓ  ም፣  World Mobile Congress(MWC) በመባል የታወቀው  ዓለም አቀፍ የኮምፒዩተር ትርዒት ከተካሄደ ወዲህ፤ አሁን የመላው ዓለም ዐይን በሰሜን ጀርመናዊቷ ከተማ በሐኖፈር ላይ ሆኗል ያረፈው።

CeBIT 3013
ምስል DW/Rosalia Romaniec

አምና  በሐኖፈር፣  የዲጂታል መሣሪያዎች ዓለም አቀፍ ትርዒት፣የተለያዩ አገልግሎቶች የሚያበረክቱ የእጅ ስልኮች፣ እጅግ ፈጣን የኮምፒዩተር ሞተሮች፤ከዚህም በተጨማሪ፤ Cloud Computer Technology(የመረጃ ቴክኖሎጂ ሰነዶች ማከማቻ ሥርዓት የተዘረጋበት ማለት ነው፤)በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያዝበትና የሚጠበቅበት አሠራር ዘዴ ፤  ዐቢይ ትኩረት  አግኝቶ እንደነበረ የሚታወስ ነው።  ዘንድሮም በዚሁ ዘርፍ የተሻሻሉ የሥነ ቴክኒክ ውጤቶች መቅረባቸው አልቀረም።

ባለፈው እሁድ ማታ ፣ በጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክልና በፖላንዱ-አቻቸው ዶናልድ  ቱስክ ተመርቆ በተከፈተውና ከትናንት ጀምሮ እስከ ፊታችን ቅዳሜ ለህዝብ ክፍት ሆኖ በሚቆየው፣ ዓለም አቀፍ ትርዒት፣ ከ 70 ሃገራት የተውጣጡ  4,100 ያህል ኩባንያዎች አዳዲስ የሥነ ቴክኒክ ውጤቶችን በማሳየት ላይ ይገኛሉ። በጥርና የካቲት ፤ በላስ ቬጋስና በባርሴሎና በተካሄዱት ዓለም አቀፍ ትርዒቶች ፣ዐቢይ ግምት የተሰጣቸው «ስማርትፎንስ» እና «ታብሌትስ» ሲሆኑ፣ «ሴቢት»(CEntrum der Büro und InformationsTechnik, Center for Office and Information Technology)  በአጠቃላዩ የዲጂታል ውጤቶች የፈጠራ ውጤትና ፣ እነዚህን ዘመናዊ የሥነ ቴክኒክ ውጤቶች፤ የተለመደው ኢንዱስትሪ፤ በተለይ ደግሞ ህዝቡ እንዴት እንደሚጠቀምባቸው  ማሰላሰሉን ሆኗል ይበልጥ የመረጠው።

Cebit 2013 Smartphone Blackberry 10
ምስል Secusmart

የሐኖፈሩ «ሴቢት» ዋና ሥራ አስኪያጅ፤  Frank Pörschmann---

«ሴቢት፤ በቅርጹና በአደረጃጀቱ ፍጹም የተለየ ነው። ይበልጥ ትኩረት የሚሰጠውም፤ ለአጠቃላዩ የሥነ ቴክኒክ ዘርፍ ነው። የመረጃ ቴክኖሎጂ፤ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ ኤሌክትሮኒክ፤ እና ይዘት--- ከእነዚህ ጋር የሚያስተሣሥረው  የሥነ ቴክኒክ ድርም ሆነ ገመድ ፣--ሁሉም ቦታ አለው። ስለሆነም መወያያዎቹ አርእስት እጅግ በዛ ያሉ ናቸው። ቀደም ባሉት ጊዜያት እንደታየው ሁሉ፤ አሁንም «ሴቢት» በዓለም ውስጥ በዓይነቱና በስፋቱ ወደር የሌለው ነው። ለእኛ ደግሞ እጅግ ሰፊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ ግምት የሚሰጠው ነው። እዚህ ፤ አዳዲስ የፈጠራ ሥራ ውጤቶች መቅረባቸውና የኢንዱስትሪው የንግድ ክፍል ትኩረት ማሳየቱ፤ አበረታች ነው።  በዐውደ ርእዩ የሚታዩትና ውይይት የሚደረግባቸው አርእስት፤ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች ለሚቆጠር ህዝብ እንደሚደርሱ   ተስፋ እናደርጋለን። ለዚህም ነው፤ በ«ኦንላይን» ና በማኅበራዊ የመገናኛ መሥመሮች መረጃ በማቅረብ ላይ የምንገኘው። ሴቢት በዚህ ረገድም አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው።»

በዘንድሮው የሐኖፈር ዓለም አቀፍ የኮምፒዩተርም ሆነ በአጠቃላይ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪዎች  ትርዒት፣ የፈጠራ ውጤቶችን  መካፈልና በጋራ መጠቀም በሚል ዓላማ (SHARECONOMY) የተሰኘው ቃል መፈክር ሆኖ ቀርቧል። ይህ ደግሞ፣ በተለይ በአሁኑ ዘመን  በወጣቶች ዘንድ፣ በተለይ በኢንተርኔት አማካኝነት፤ የተለያዩ ጉዳዮችን መካፈል የተለመደ ተግባር ነው። ለምሳሌ ያህል፤ ዕውቀት፣ ተመክሮ ፣ ሙዚቃ ---አውቶሞቢል ፣ በዘመናዊ የእጅ ስልክ የመረጃ ልውውጥ፣  በሰዓቶች ለውጥ መከራየት ይቻላል --ብስክሌቶችንም እንዲሁ! ይህ እንዴት እንደሚከናወን « ሰቢት» በግቢው አሳይቷል።

CeBIT 2013
ምስል Getty Images

«ሲካፈሉት የሚባዛ ፤ የሚዛመት ብቸኛው ሀብት ዕውቀት ነው። ይህ ደግሞ ፤ በአሁኑ ጊዜ ፤ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በትዊተርና ፌስቡክ የምናየው ነው። ግንኙነት መፍጠራችን፤ ዕውቀትና ተመክሮአችንን ማካፈላችን የኅብረተሰቡን የዕድገት ጎዳና ይበልጥ ይቀይሳል። «ፌስቡኪንግ» ሊባል የሚችል ነው።በኤኮኖምም ረገድ ዕድገትን የሚያመጣ ነው። ዕውቀት ፤ በሰፊው መረጃ ማግኘት የሚቻልበት  ሲስፋፋ፣ ኤኮኖሚውም በፍጥነት በማደግ የፈጠራ ውጤቶችን ያቀርባል።»

በሐኖፈሩ ትርዓት ፣ ዘንድሮ ምንድን ነው ልዩ ም ሆነ አዲስ የሥነ ቴክኒክ ግሥጋሴ ውጤት ተብሎ የቀረበው?

አዎ፤ አንዱ ፣ እጅግ ጥንታውያን የሆኑ መጻህፍት፣ በልዩ ጥንቃቄ በመስትውት ውስጥ የተቀመጡም ቢሆኑ  ፣ በጓንት እንጂ በአጅ ጣቶች እንኳ የማይነኩትንም  በ 3 ማዕዘናዊ ቴክኒክ ይዘታቸው በመላ በግልጽ  ቁልጭ ብሎ እንዲታይና ለኅትመት በቅቶ ለአንባብያን እንዲዳረስ ማድረግ የሚቻለበት ቴክኒክ ነው። ይህን ለማድረግ ያበቃው፤ እውቁ የጀርመን የምርምር ተቋም «ፍራውንሆፈር» ነው። ጥንታውያን መጽሐፍት ብቻ ሳይሆኑ ከህትመት ውጪ የሆኑ መጽሐፍትንም መልሶ በሰፊው ለማተም  ይቻላል።

ምቹ የሆነ ፤ የሚያዝናና የቤት ወንበር ፤ የክንድ ማረፊያዎቹ በከፊል የተለያዩ የነርስነት ተግባራት  እንዲያከናውኑ ፤ በተጨማሪም የአካል ማጠንከሪያ እንቅሥቃሴ ለማድረግ የሚያመች ሆኖ ፤ በተለይ ለሽምግሌዎችና ባልቴቶች እንዲስማማ ሆኖ መሠራቱን በሐኖፈሩ ትርዒት ለማየት ተችሏል። መጠን ያለፈ ክብደት ላላቸው ሰዎች ወንበሩ እንደተቃዛፊ ጀልባ ሆኖ የአካል ማጠንከሪያ ጅምናስቲክ እንደሚያሠራቸውም ታውቋል።  ለገበያ ሊውል የሚችለው  ከአንድ ወይም ከ 2 ዓመት በኋላ መሆኑን የልዩው ሶፋ ወንበር ሠሪዎች ገልጸዋል። ወንበሩ ብቻ ዋጋው ፣ ከ 2ሺ እስከ 3 ሺ ዩውሮ የሚገመት ሲሆን ፣በክንዶች ማረፊያ ላይ የሚገጣጠሙት  ቴክኒካዊ መሳሪያዎቹ ሲታከሉበት ከእጥፍ  በላይ ያወጣ ይሆናል።

CeBIT 3013
ምስል DW/Rosalia Romaniec

ሌላው በገበያ አዳራሾች ልዩ እገዛ የሚያደርግ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ፈልጎ በመሰብሰብ የሚረዳ፤ ለግብይት የሚስማማ ጋሪ ነው። 

በሐኖፈሩ የዲጂታል መሣሪያዎች ትርዒት፣ «ሼርኤኮኖሚ» የሚለው መፈክር ብቻ አይደለም የተተኮረበት። የዘመናዊ የእጅ ስልኮች ልዩ -ልዩ አገልግሎቶችና መረጃዎችን ወደሌላ ቦታ አዛውሮ ማስቀመጥም ሆና ማከማቸት የሚቻልበት ሥነ ቴክኒክ (ክላውድ ኮምፒዩቲንግ)ጭምር አሁንም ላቅ ያለ ግምት ነው የተሰጣቸው። እዚህም ላይ አስተማማኝ ጥበቃ ፣ እንዳምናው ሁሉ ዘንድሮም ዐቢይ ግምት ነው የተሰጠው። አዳዲስ መፍትኄዎችን ያቀረቡ አዳዲስ ኩብንያዎች ሆነው ተገኝተዋል። ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ  ከ200 በላይ የሚሆኑ ኩባንያዎች ዘንድሮ በሐኖፈሩ ትርዒት በመሳተፍ ላይ ናቸው። የመረጃ ቴክኖሎጂው እመርታም ሆነ ግሥጋሴ የተፈለገውን ያህል ባለመሆኑ ይበልጥ ሥራ ማከናወን እንደሚገባ መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል፣ በሳምንታዊ የቪዲዮ ቃልምልልሳቸው እንዲህ ሲሉ ነቀፌታ አሰምተዋል።

Roboter ARMAR von KIT auf der CeBIT am 07.03.2012
ምስል DW/Alexandre Schossler

« እንደሚመስለኝ፤ ከሁለም አስቀድመን፤ የኢንተርኔት ኩባንያዎች የሚጠይቁትን አዘምኖ ለማቅረብ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። የጀርመን የጋራ የምርምር ወረት የማሳደግ ባህል አመርቂ  እንዳልሆነ ታይቷል። ከጸደይ ጀምሮ የጋራ የምርምር (የአሰሳ )የወረት ገንዘብ ለተጠቀሱ አዳዲስ ኩባንያዎች እንመድባለን። የከፍተኛ የሥነ ቴክኒክ ማደራጃ ወረት በመመደብ እንታወቃለን ፤ በዚህም  መጠቀም ይቻላል። ከአውሮፓው ኅብረት ባለወረቶች ጋር በመተባበር ገንዘብ ሥራ ላይ እንዲውል ለማድረግ እንሞክራለን።»

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ