1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዚምባብዌዉ ገዥ ፓርቲ ጉባኤ

ሰኞ፣ ኅዳር 29 2007

የዘጠና አመቱ የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ የዛኑ ፒ.ኤፍ. መሪ ሆነው በድጋሚ ተመርጠዋል። የፕሬዝዳንቱ ባለቤት ግሬስ ሙጋቤም በፓርቲው የሴቶች ክንፍ መሪ በመሆን ወደ ፖለቲካው መቀላቀላቸው ይፋ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/1E0zO
Straßenszene in Harare, Simbabwe
ምስል AFP/Getty Images/A. Joe


በዛኑ ፒ.ኤፍ. ጠቅላላ ጉባኤ የታደሙት የፓርቲው አባላት መሪያቸው ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ለረጅም ዘመናት አብረዋቸው እንደሚቆዩ እምነታቸው ነው። በዚህ እምነታቸው የዘጠና አመቱ ሮበርት ሙጋቤ ለቀጣዮቹ አምስት አመታት እንዲመሯቸው ያለምንም ተቃውሞ መርጠዋቸዋል።እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2018 ዓ.ም. በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም ይወዳደራሉ። ያኔ እድሜያቸው 94 ይሆናል። በጉባኤው ንግግር ያደረጉት ሮበርት ሙጋቤ የፓርቲያቸውን አመራር በመጪው ሐሙስ እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።
«ብዙ ስንብቶች ይኖራሉ። አንዳንዶቹ በህገወጥ ድርጊቶቻቸው አስቀድመው መsሰናበቱን መርጠዋል። ዛሬ እዚህ የሌሉት ተሰናብተውናል። ካሁን በኋላ ወደ ፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አይመለሱም። ተራ አባል ሆነው ይቀጥላሉ። በቆሎና ድንች የሚያመርቱበት ጊዜም ይኖራቸዋል።»
ይህ ዚምባብዌ ከእንግሊዝ ቅኝ ነጻ ከወጣችበት ከጎርጎሮሳውያኑ 1980 ዓም ጀምሮ ብቸኛው መሪ ከሆኑት ሮበርት ሙጋቤ ጋር መቃቃር ውስጥ የገቡትን ምክትል ፕሬዝዳንት ጆይስ ሙጁሩ የሚመለከት ነው። ሙጁሩ ከሶስት ወራት በፊት የሮበርት ሙጋቤ አልጋ ወራሽ እንደሚሆኑ ይታሰብ ነበር። ሙጋቤ ሊያስገድሉኝ አስበዋል በሚል ከወቀሱዋቸው በኋላ ግን በብዙዎች ዘንድ የተጠበቀው የጆይስ ሙጁሩ ቀጣይ ፕሬዝዳንትነት ውሃ በላው።
በዛኑ ፒ.ኤፍ. ፓርቲ ውስጥ የተፈጠሩ ከፍተኛ የስልጣን ክፍተቶችን ለመተካት የታየው ዳተኝነት ሮበርት ሙጋቤ ዛሬም በርግጠኝነት የሚተካቸውን ሰው አያውቁም የሚል ጥርጣሬ አጭሯል። የፖለቲካ ተንታኙ ታኩራ ዛንጋዛ የቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ የሴቶች ክንፍ ዋና ጸሃፊነት ስልጣን ብቻ ተተኪ ፕሬዝዳን እንደማያደርጋቸው ይናገራሉ።
«ግሬስ ሙጋቤ በፓርቲው የሴቶች ሊግ ከተመረጡ በኋላ ለዚህ ሥልጣን እንደሚበቁ የታወቀ ነው። ነገር ግን በፓርቲው ከፍ ወዳለ አመራርነት ለመምጣት የካቤኔ አባል መሆን ይጠበቅባቸዋል። የሴቶች ክንፍ ዋና ጸሃፊ ለወትሮው በመንግስታዊ መዋቅሩ ውስጥ የሚኒስቴርነት ስልጣን ይኖረዋል።»
ምክትል ፕሬዝዳንት ጆይስ ሙጁሩ በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ስማቸው በተደጋጋሚ ቢወገዝም በይፋ ከመንግስት እና የዛኑ ፒ.ኤፍ. ስልጣናቸው አልተነሱም። እንደ ታንኩራ ዛንጋዛ ከሆነ ፓርቲው ሁለት ምክትል ፕሬዝዳንት እና አንድ ዋና ጸሃፊ ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም አሁን ለተፈጠረው ውስብስብ ሁኔታ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ሐሙስ ይፋ የሚያደርጉት የፓርቲ አመራር መፍትሄ ሊሰጠው ይችላል።
እንደ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ግምት፣ ምክትል ፕሬዝዳንት ጆይስ ሙጁሩ አሁን ከፓርቲው አመራር ውጪ ከሆኑ የፍትህ ሚኒስትሩ ኤመርሰን ማንጋግዋ የሮበርት ሙጋቤ ተተኪ ሊሆኑ ይችላሉ። ሌሎች ግን ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ከአዲሱ ሹመታቸው በኋላ ሮበርት ሙጋቤን ለመተካት ፉክክሩን እንደተቀላቀሉ ይገምታሉ። የቀድሞዋ የሮበርት ሙጋቤ ጸሃፊ የዛሬዋ ቀዳማዊት እመቤት አንድ ቀን የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት የመሆን ምኞት እንዳላቸው ከጥቂት ሳምንታት በፊት ተናግረው ነበር።
ኮሉምበስ ማቩንጋ / እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

Grace Mugabe
ቀዳማዊት እመቤት ግሪስ ሙጋቤምስል J. Njikizana/AFP/Getty Images
Joyce Mujuru
ጆሲ ሙጁሩምስል picture-alliance/AP Photo
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ