1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዝውውርና አጫጭር ስፖርት ነክ ዜናዎች

ሰኞ፣ ሐምሌ 14 2006

የአውሮጳ ታላላቅ የእግር ኳስ ቡድኖች ጨዋታ በአዲስ መልክ ከመጀመሩ አስቀድሞ ቡድኖቹ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እየተዘዋወሩ የአቋም መለኪያ ግጥሚያዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ ከጋቦን አቻው ጋር እኩል ለእኩል ወጥቷል። ሌሎች ዜናዎችንም አካተናል

https://p.dw.com/p/1CgHY
ምስል Reuters

የአውሮጳ ታላላቅ የእግር ኳስ ቡድኖች የበጋ ወራት የዙር ጨዋታ በአዲስ መልክ ከመጀመሩ አስቀድሞ ቡድኖቹ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እየተዘዋወሩ የአቋም መለኪያ ግጥሚያዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ። ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ ከጋቦን አቻው ጋር እኩል ለእኩል ወጥቷል። ሌሎች ዜናዎችንም አካተናል፤ ቆይታችሁ ከእኛ ጋር ይሁን!

በመጀመሪያም አዳዲስ የዝውውር ዜናዎች። ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን በመሰለፍ የዓለም ዋንጫን ለመጨበጥ የታደለው የሪያል ማድሪዱ አማካይ የ27 ዓመቱ ሳሚ ከዲራ ወደ አርሰናል የመዛወሩ ነገር ላይሳካ ይችላል ተባለ። በአንፃሩ የሀገሩ ልጅ የ24 ዓመቱ ቶኒ ክሮስ ከጀርመን ቡንደስ ሊጋ ባለድሉ ባየርን ሙንሽን ወደ ስፔን ላሊጋ ኃያሉ ሪያል ማድሪድ ሊያቀና እንደሆነ ከሰሞኑ ተዘግቧል። ክሮስ ወደ ሪያል ማድሪድ እንዲመጣ ወደ 6 ሺህ ያህል የሪያል ማድሪድ ቡድን ደጋፊዎች እንደሚፈልጉ ለማወቅ ተችሏል። ክሮስ ማድሪድ ከገባ በዓመት የሚከፈለው ስድስት ሚሊዮን ዩሮ እንደሚሆንም ተጠቅሷል። በነገራችን ላይ እጎአ በ2009 ፖርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ወደ ሪያል ማድሪድ እንዲመጣላቸው ይፈልጉ የነበሩ የሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች ቁጥር 80 ሺህ እንደነበር ይታወሳል።

ክሮስ ወደ ሪያል ማድሪድ ሊያቀና እንደሆነ ሲነገር፤ ጀርመናዊው የብሔራዊ ቡድን ባልደረባው ሳሚ ከዲራ ሰሞኑን ወደ እንግሊዙ አርሰናል ቡድን በስድስት ሚሊዮን ዩሮ የተጣራ ክፍያ ሊዛወር እንደነበር ተዘግቦ ነበር። ይሁንና ግን ዛሬ የወጣ ዘገባ እንደሚያመለክተው የፈረንሣዩ ሞናኮ ቡድን ሳሚ ከዲራ ላይ አይኑን ጥሏል። በጀርመን ሰፊ ተነባቢነት ያለው ቢልድ የተሰኘው ዕለታዊ ጋዜጣ እንዳተተው ከሆነ ሪያል ማድሪድ አማካዩ ሳሚ ከዲራን ወደ ሞናኮ በመላክ 75 ሚሊዮን ዩሮ ተጨማሪ ክፍያ ለመፈፀም ጫፍ ደርሷል። በምትኩም ማድሪድ የሞናኮው አጥቂ፣ የ23 ዓመቱ አማካይ ጄምስ ሮድሪጌዝን በእጁ ለማስገባት እንደቋመጠ ተዘግቧል። ኮሎምቢያዊው ሮድሪጌዝ በሞናኮ ዓመታዊ ክፍያው 1,2 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ነው።

ሳሚ ከዲራ ወደ ሞናኮ ቡድን ተዛውሮ የመጫወት ፍላጎት እንደሌለው የመጥቀሱ ዜና አርሰናሎችን ሳያፅናና አይቀርም። ሞናኮ ሪያል ማድሪድ ያቀረበለት 75 ሚሊዮን ዩሮ ላይ አስር ካልተጨመረ ሮድሪጌዝን አለቅም ብሏል። የኃያላን ተጨዋቾች ስብስብ የሆነው ሪያል ማድሪድ በበኩሉ አስር ሚሊዮን ዩሮ አያጣላንም፤ ከፈለጋችሁ ከከዲራ ሌላ ዲ ማሪያን፣ ፔፔን ወይንም ዲዬጎ ሎፔዝን መውሰድ ትችላላችሁ ሲል ሞናኮን ለማባበል ሞክሯል።

ፕሬሚየር ሊጉ በጋ ላይ ከመጀመሩ አስቀድሞ ቡድኖች አቋማቸውን ለመፈተሽ ወደተለያዩ ሃገራት በሚያደርጉት ጉዞ ሊቨርፑል ለአሜሪካ ቆይታው ሠርቢያዊው ላዛር ማርኮቪችን ማካተቱ ተጠቅሷል። ሽቴቫን ዤራርድም ከዓለም ዋንጫ ግጥሚያ በኋላ ከተራዘመው ረፍቱ በመመለስ ቡድኑን ተቀላቅሎ ወደ አሜሪካ ማቅናቱ ታውቋል። ሊቨርፑል ላዛርን ከፖርቹጋል ቤኔፊካ ቡድን ለመውሰድ 20 ሚሊዮን ፓውንድ እንዳወጣ ተጠቅሷል። ሊቨርፑሎች በዩናይትድ ስቴትስ ቆይታቸው ከ6 ቀናት በኋላ፤ ሐምሌ 20 የግሪኩ ኦሎምፒያኮስን ቺካጎ ውስጥ ይገጥማሉ። በዛው አቋማቸውን ለክተው ከ9 ቀናት በኋላ፣ ሐምሌ 23 ቀን ደግሞ ኒውዮርክ ውስጥ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ይፋለማሉ። ቅዳሜ፣ ሐምሌ 26 ቀን ቻርሎቴ ውስጥ ከኤስ ሚላን ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዋል። የአሜሪካው ጉዞ 20 ሚሊዮን ፓውንድ የወጣበት ላርዛን ጨምሮ የሊቨርፑል ተጨዋቾች ብቃታቸውን የሚያስለኩበት ይሆናል። አድማጮች ተጨማሪ የዝውውር ዜናዎችን ይዘናል። እንመለስበታለን።

ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ግጥሚያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የጋቦን አቻውን ገጥሞ ያለምንም ግብ አቻ መለያየቱ ተዘግቧል። የመልስ ጨዋታው የሚካሄደው ቅዳሜ፣ ሐምሌ 26 ቀን ነው። በትናንትናው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአስተዳደራዊ ጉድለት በርካታ ተጨዋቾችን ማሰለፍ እንዳልቻለ የተዘገበ ሲሆን፤ በተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበረው ተጨዋችም አንድ ብቻ እንደነበር ተጠቅሷል።

ሌሎች አገሮች ላይ በተደረገው መሰል ግጥሚያ ዛምቢያ ቦትስዋናን እንዲሁም ጊኒ ሞሮኮን 1 ለ ዜሮ አሸንፈዋል። ቶጎ ከሴኔጋል ያለምንም ግብ ተለያይቷል። ከትናንት በስትያ ኡጋንዳ ሩዋንዳን 4 ለዜሮ ረትታለች። ሞዛምቢክ አንጎላን 2 ለ1 ስታሸንፍ፣ ካሜሩን ቡርኪናፋሶን 2 ለ ባዶ ሸንታለች። ቤኒን ማሊን 1 ለምንም አሸንፋለች። ታንዛኒያ ከደቡብ አፍሪቃ ያለምንም ግብ አቻ ተለያይታለች።

እጎአ በ2015 ኒጀር ውስጥ በሚካሄደው ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ግጥሚያ ለመሳተፍ 24 የተለያዩ አፍሪቃዊ ሀገራት ፉክክር በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ዘንድሮ በተደረጉ ግጥሚያዎች የኡጋንዳ እና የግብፅ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድኖች ለሦስት ጊዜያት አሸናፊ ሆነዋል። ሞዛምቢክ ሁለት ጊዜ አሸንፋለች። አይቮሪኮስት፣ ካሜሩን፣ ጊኒ፣ ዛምቢያ እና ቤኒን አንድ አንድ ጊዜ አሸናፊ ሆነዋል። ዘንድሮ የመጀመሪያ ግጥሚያውን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ ሌሎቹ 16 ሃገራት እስካሁን ምንም አላሸነፉም።

ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት መካከለኛው አፍሪቃን ገጥሞ በደርሶ መልስ ሁለቱንም ግጥሚያዎች 3 ለ ባዶ ማሸነፉ ይታወሳል። በተመሳሳይ ዓመት ከቱኒዚያ ጋር ተገናኝቶ 3 ለ ዜሮ ያሸነፈ ሲሆን፤ በመልስ ጨዋታው 5 ለአንድ ተሸንፎ ነበር። ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተጨዋቾች ያሳዩት የእግር ኳስ ብቃት የሚበረታታ ነው። ሆኖም ከእዚህ ቀደም በእድሜ የተነሳ ዘንድሮ ደግሞ በፓስፖርት እና መሰል አስተዳደራዊ ድክመቶች ቡድኑ መሰናክሎች እንደገጠሙት ተጠቅሷል።

የሚኪና ሽቅድምድም፤
በአውሮጳ ተወዳጅ በሆነው፣ ፎርሙላ አንድ በተሰኘው የመኪና ሽቅድምድም ጀርመናዊው ኒኮ ሮዘንበርግ ጀርመን ውስጥ በተከናወነው ሽቅድምድም አሸናፊ ሆነ። በመርሴዲስ መኪናው ሲከንፍ የነበረው ኒኮ ሮዘንበርግ አንደኛ የሆነው የቡድኑ ባልደረባ ሌዊስ ሐሚልተንን እና ቫልተሪ ቦታስን በመቅደም ነው። በእዚሁ ውድድር የብሪታንያው ተወላጅ ሌዊስ ሐሚልተን በመርሴዲስ መኪናው ሦስተኛ የወጣበት ጥረት በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አትርፎለታል።

ሌዊስ መጀመሪያ ላይ ከነበረበት 20ኛ ደረጃ ተንደርድሮ ነበር በስተመጨረሻ ሦስተኛ በመሆን ፉክክሩን ያጠናቀቀው። የፎርሙላ አንድ የአራት ጊዜያት ባለድሉ ሌላኛው ጀርመናዊ ሠባስቲያን ፌትል በሬድ ቡል ተሽከርካሪው ትናንት በአራተኛነት ለማጠናቀቅ ተገዷል።

ኒኮ ሮዘንበርግ
ኒኮ ሮዘንበርግምስል Reuters
እግር ኳስ አፍቃሪ የጎዳና ተዳዳሪዎች በአፍሪኣ
እግር ኳስ አፍቃሪ የጎዳና ተዳዳሪዎች በአፍሪኣምስል picture-alliance/Ton Koene
የሊቨርፑል ቡድን እጎአ በ1977 ጀርመን ውስጥ
የሊቨርፑል ቡድን እጎአ በ1977 ጀርመን ውስጥምስል picture-alliance/Sven Simon
ክርስቲያኖ ሮናልዶ
ክርስቲያኖ ሮናልዶምስል Getty Images
ሉዊስ ቫን ጋል በስተግራ
ሉዊስ ቫን ጋል በስተግራምስል AP

ስፔናዊው ፈርናንዶ አሎንሶ በፌራሪ ተሽከርካሪው አምስተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፤ አውስታራሊያዊው ዳኒኤል ሪቺያርዶ በሬድ ቡል ሬኖልት ተሽከርካሪው ስድስተኛ ሆኗል። አድሪያን ሱቲል የተሰኘው ሌላኛው ጀርመናዊ ተወዳዳሪ ውድድሩን አቋርጧል።

ብስኪሌት
ከባድ ውሽንፍር ባጀበው ዝናባማው የቱር ደ ፍሯንስ የብስኪሌት ሽቅድምድም የ32 ዓመቱ ጀርመናዊ አንድሬ ግራይፕል ትናንት አራተኛ በመውጣት ከጀርመናውያን ተሳታፊዎች ቀዳሚው ሆኗል። የ26 ዓመቱ የሀገሩ ልጅ ሌላኛው ጀርመናዊ በእዚሁ ውድድር በ11ኛነት አጠናቋል። የኖርዌይ ተወላጁ አሌክሳንደር ክሪስቶፍ ከአውስትራሊያዊው ሔንሪሽ ሐውስለር ጋር ተናንቆ በአንደኛነት አሸናፊ ሆኗል። የስሎቫኪያው ተፎካካሪ ፔተር ዛገን ሦስተኛ ወጥቷል። ሌላኛው አውስትራሊያዊው በጀርመኑ አንድሬ ተቀድሞ አምስተኛ ሲወጣ፤ ፈረንሣውያኑ ብሪያን እና ሮማይን ስድስተኛ እና ስምንተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

የቸልሲው የክንፍ ተመላላሽ ግብፃዊው ሞሐመድ ሳላህ ከግብፅ ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ግዳጅ ለጥቂት ነፃ መውጣቱ ተነገረ። የ22 ዓመቱ ግብፃዊ ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት ለሚዘልቀው የግብፅ ብሔራዊ የውትድርና አገልግሎት ወደ ግብፅ የመመለስ ግዴታ አለበት የሚለው ዜና የቸልሲ ደጋፊዎችን አስደንግጦ ነበር። ሞሐመድ ሳላህ ተመዝግቦ ከነበረበት የግብፅ የትምህርት ተቋም በማቋረጡ የብሔራዊ ውትድርና ግዳጅ ይጠብቀው ነበር። ሆኖም ስታምፎርድ ብሪጅ ውስጥ ማሳየት የጀመረው መሻሻል ስኬታማ እንዲሆን ተፈቅዶለታል። ከባዝል ቡድን በ11 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ የተዘዋወረው ሞሐመድ ሳላህ በስድስት የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ሁለት ግቦችን ለማስቆጠር ችሏል።

በተያያዘ የጋላታሳራይ ቆይታው ያበቃው የቀድሞው የቸልሲ አጥቂ የ36 ዓመቱ ዲዲየር ድሮግባ ተመልሶ ወደ ቸልሲ እንዲመጣ አንዳንድ ደጋፊዎች ፍላጎት እንዳላቸው ገለጡ። ዲዲየር ድሮግባን ከ10 ዓመት በፊት ከፈረንሳዩ ማርሲይ ቡድን ፈርመው ያስመጡት የቸልሲው አሰልጣኝ ጆሴ ሞርሂኖ ነበሩ። እናም አሁን ዴምባ ባ ቸልሲን ለቆ መውጣቱ ድሮግባ ዳግም ተመልሶ ለመፈረም ዕድል ይኖረዋል ሲሉ አንዳንድን ተንታኞች ተናግረዋል። አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪኒሆ ድሮግባን ለአንድ ዓመት ለማስፈረም እችላለሁ ሲሉ ዝተዋል። ድሮግባ ለቸልሲ ከፈረመ በተያያዥነት የአሰልጣኝነት ተደራቢ ሥራም እንደሚሰጠው ተጠቅሷል።

የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አንበል እና የሊቨርፑል አማካይ ሽቴፋን ዤራርድ ከእንግዲህ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እንደማይሳተፍ ዛሬ ይፋ አድርጓል። እ ጎ አ በ2000 ዓም ዌምብልዴይ ላይ የዩክሬይን ብሔራዊ ቡድንን 2 ለ ባዶ በማሸነፍ ከዛሬ 14 ዓመት በፊት ዓለምአቀፍ ውድድሩን ለሀገሩ ተሰልፎ ማካሄድ የጀመረው ሽቴፋን ዤራርድ እስካሁን ለ114 ጊዜያት ለእንግሊዝ በመሰለፍ 21 ግቦችን ለሀገሩ አስቆጥሯል። ዤራርድ የስንብት ንግግሩን ሲያደርግ እንዲህ ብሎ ነበር። «ሀገሬን የወከልኩበትን እያንዳንዱን ደቂቃ ተደስቼበታለሁ። እናም ዛሬ ዳግም የእንግሊዝን ማሊያ እንደማልለብስ ያወቅኩበት አሳዛኝ ቀን ነው።» የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሮይ ሆድግሰን በበኩላቸው የሽቴፋን ዤራርድን ውሳኔ መስማታቸው እንዳበሳጫቸው ሆኖም ውሳኔውን እንደሚያከብሩ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል። «በውሳኔው ብበሳጭም ሽቴፋን ያለበትን ሁኔታ እረዳለሁ፣ ለሀገሩ ያበረከተው ድንቅ አስተዋፅዖ ላይም ምንም አይነት ቅሬታ የለብኝም።»

ሊቨርፑል በእዚህ ሳምንት ሦስት ተጨማሪ ተጨዋቾችን ለማስፈረም ጫፍ እንደደረሰ ተዘግቧል። ለሊቨርፑል እንደሚፈርሙ የተነገረላቸው ተጨዋቾች፤ ሎይች ሬሚ፣ ጂቮክ ኦሪጂ እና ዴጃን ሎሬን ናቸው ሲል ዘ ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ ዛሬ አትቷል። ሚቻ ሪቻርድስን ማንቸስተር ሲቲ ለሊቨርፑል አለያም ለቶትንሐም ወይንም ለኒውካስል እንደሚያስተላልፍ ይፋ አድርጓል ሲል የዘገበው ደግሞ ዴይሊ ኤክስፕሬስ ነው። አርሰናል የስፖርቲንግ ሊዝቦን አማካይ ዊሊያም ካርቫሎህን በእጁ ለማስገባት 24 ሚሊዮን ፓውንድ መክፈል ይጠበቅበታል የሚል ፅሁፍ ለንባብ ያበቃው ዴይሊ ቴሌግራፍ ነው።


የሆላንድን ብሔራዊ ቡድን በብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ሦስተኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ ያስቻሉት አሰልጣኝ ሉዊስ ቫን ጋል ባለፈው ሳምንት ኦልትራፎርድ መግባታቸው ታውቋል። ቫን ጋል ሁሉንም የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋቾች መገምገም እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ከትናንት በስትያ የአቅም መለኪያ ጨዋታዎችን አሜሪካን ውስጥ ለማድረግ በተነሱበት ወቅት 25 ተጨዋቾቻቸውን ይፋ አድርገዋል። በቡድኑ ውስጥ ያልታቀፉት ሦስት ተጨዋቾች፤ በዓለም ዋንጫ ግጥሚያ መዳቀቁን የገለፀው ቫን ፔርሲ፣ የቁርጭምጭሚት ቀደ-ጥገና የተደረገለት ሚካኤል ካሪክ እንዲሁም በልምምድ ወቅት የተጎዳው አንደርሰን ናቸው። ማንቸስተር ዩናይትድ በአሜሪካ ቆይታው ከነገ በስተያ ኤል ኤ ጋላክሲን ይገጥማል። ሐምሌ 19 ኤኤስ ሮማን፣ ሐምሌ 22 ኢንተር ሚላንን እንዲሁም ሐምሌ 26 ሪያል ምድሪድን ይፋለማል።

የአልጄሪያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ፈረንሳዊው ክርስቲያን ጉክቺፍን አዲሱ አሠልጣኝ አድርጎ ሾመ። አዲሱ አሠልጣኝ በብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ቡድኑን ወደ ሁለተኛ ዙር እንዲገባ ያደረጉት ቫሂድ ሀሊሆጂክን ይተካሉ ተብሏል። የ59 ዓመቱ ፈረንሣዊ አሠልጣኝ መደበኛ ሥራቸውን በይፋ የሚጀምሩት ዓርብ ሐምሌ 25 ቀን ሲሆን፤ ቡድኑ የመጀመሪያ ግጥሚያ የሚያደርገው ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ይሆናል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አዲስ አሠልጣኝ ማረፊያቸውን ኢንተር ኮንቲነንታል ሆቴል ያደረጉት ፖርቹጋላዊው ማሪያኖ ባሬቶ ስለአዲሱ አሠልጣኝ እና የአልጄሪያ ቡድን ጥናት በማድረግ ውጤት ያስመዘግባሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል። አዲሱ የአልጄሪያ ቡድን አሠልጣኝ ውል የፈረሙት ቡድኑን እስከሚቀጥለው የዓለም ዋንጫ ለማሰልጠን እንደሆነም ታውቋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ሽቅድምድም
ቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ሽቅድምድምምስል Reuters

ኂሩት መለሰ