1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየመኑ ፕሬዝዳት ጤና እና የሥልጣን ክፍተት

ረቡዕ፣ ሰኔ 1 2003

ሟቾች መንግሥትን የሚቃወመዉ የአል-አሕመር ጎሳ አባላት፥ ገዳዮች የመንግሥት ነጥሎ ገዳዮች ይሆኑ-ይሆን?ወይስ በተቃራኒዉ።የሕመር ታጣቂዎች የመንግሥትን ደጋፊዎች ገድለዉ ጥለዋቸዉ-ይሆን? ሌላም ብዙ ጥያቄ ይዥጎደጎዳል።እስካሁን የሚታወቀዉ ግን አንዱም አለመታወቁ ነዉ።

https://p.dw.com/p/RSXS
ሰነዓምስል DW / Heymach

የየመኑ ፕሬዝዳንት ዓሊ አብደላ ሳሌሕ ባለፈዉ አርብ በተጣለባቸዉ ቦምብ የደረሰባቸዉ ጉዳት በይፋ ከተባለዉ ይበልጥ ከባድ መሆኑ እየተነገረ ነዉ።ሳሌሕ አሁንም ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ ሕክምና እየተደረገላቸዉ ነዉ።አንድ ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣን እንዳስታወቁት ሳሌሕ ከአካላቸዉ አርባ በመቶ ያሕሉ ተጎድቷል።ሐኪሞቻቸዉ እስካሁን በይፋ ያሉት ነገር የለም።የየመን ባለሥልጣናት እንደሚሉት ግን ፕሬዝዳንቱ እያገገሙ ነዉ።እዚያዉ የመን የሥልጣን ክፍተቱ እየሰፋ፥ ግድያ፥ ሥርዓተ አልበኝነቱ እየበረታ ነዉ።ማሪቲን ዱርም ያዘጋጀዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

ሠነዓዎች የከተማቸዉን የምሽት ዉበት ለማጣጣም ጊዜዉም፥ አቅሙም፥ ሠላሙም አልፈቀደላቸዉም። የኮረብታ-አዘቅጥ ስብጥሪቱ ከተማ ዉበት ግን ጀርመናዊዉ ጋዜኛ እንደሚለዉ በርግጥ ድንቅ ነዉ።በኮረብታዎቹ አናት፥ በመሳጂዶቹ ሚናራዎች ላይ የሚፈሰዉ የፀሐይ ብርሐን-ከሚንተገተገዉ የኤሌክትሪክ መብራት ጋር ሲላተም ልዩ ሕብር ሕብሩ ላየዉ ልዩ ስሜት ይፈጥራል።

የወይና-ደጋማዉ አየር ንፋስ ሽዉሽዉታ፥ የዉሾች ጩኸት፥ የሙዓዚኖች አዛን ለሰነዓ የሌሊት መለያዋ፥ ጥቁም ሙዚቃ አከልም ነበሩ።ሰሞኑን ነበር-ነዉ የሚባልላት።የአንድ ሺሕ አንድ ሌሊቶቿ ምድር፥-አንድ ሌሊት።

አዛንና እና ተኩስ።

NO FLASH Jemen Freude über die Abreise von Saleh 5. Juni 2011
ሰነዓ-መሪዋ ሔዱ ሕዝቡ ፈነደቀምስል picture alliance/dpa

በማግስቱ ሐሰባ በተባለዉ ሠፈር የአስር-ሰዎች አስከሬን መንገድ ላይ ተገኘ።የሟቾቹም ሆነ የገዳዮች ማንነት በዉል አልታወቀም።ሟቾች መንግሥትን የሚቃወመዉ የአል-አሕመር ጎሳ አባላት፥ ገዳዮች የመንግሥት ነጥሎ ገዳዮች ይሆኑ-ይሆን?ወይስ በተቃራኒዉ።የሕመር ታጣቂዎች የመንግሥትን ደጋፊዎች ገድለዉ ጥለዋቸዉ-ይሆን? ሌላም ብዙ ጥያቄ ይዥጎደጎዳል።እስካሁን የሚታወቀዉ ግን አንዱም አለመታወቁ ነዉ።

ያሕያ ሳሌሕ ባለ አራት ኮኮብ ጄኔራል ናቸዉ።የፕሬዝዳት ዓሊ አብደላ ሳሌሕ የወንድም ወይም የእሕት ልጅ።የጦር ሐይሎች አዛዥ። ሳሌሕ በዘመድ-ዉልዶቻቸዉ በማገሩት መንግሥት ዉስጥ ያሕያ አራት ኮኮብ መጫን አያንሳቸዉም።አጎቴ ደሕና ናቸዉ ይላሉ ይጄኔራሉ።«ፕሬዝዳንቱ አሸባሪዎች ካደረሱባቸዉ የመቁሰል አደጋ ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ ታክመዉ በጥሩ ሁኔታ እያገገሙ ነዉ።በጣም ቢዘገይ በሁለት ሳምንት ዉስጥ ይመለሳሉ።እናት ሐገራችን እየጠበቀቻቸዉ ነዉ። ይመሯታል።»

በጄኔራሉ ሰፊ፥ ትልቅ-ወርቃማ ጠረጴዛ ላይ ከተደረደሩት ቁሳቁሶች ሁሉ አንዱ ገዘፍ-ደመቅ ብሎ ይታያል።ከመዳብ የተሰራ የሙሉ ወታደር ምሥል ነዉ።አዉቶማቲክ ጠመጃ አንግቷል።ከግርጌዉ «ከአድናቆትና መልካም ምኞት ጋር»-የሚል የእንግሊዝኛ ፅሁፎ ተለጥፎበታል።ጋዜጠኛዉ ትንሹን ሐዉልቱን ትኩር ብሎ ማየቱን ያዩት ጄራል-«የአሜሪካኖች ሥጦታ ነዉ» አሉት።«አሜሪካኖች የየመንን ጦር በፀረ-ሽብር ዉጊያ አሰልጥነዉታል።» አከሉ።ቀጠሉም ሥለ አጎታቸዉ።

«የአሕመር ጎሳ በዚያ (ፕሬዝዳንቱን ባቆሰለዉ ማለታቸዉ ነዉ) የአሸባሪዎች ጥቃት እጁ መኖር-አለመኖሩ መጣራት አለበት።ጥፋተኛዉን ለፍርድ ለማቅረብ ምርመራዉን የፍትሕ አካላት በቅጡ ማካናወን አለባቸዉ።»

Jemen Straße
ሰነዓ-ትናንት ኦና መሰለችምስል picture alliance/landov

እያሉ።የሰነዓ ነዋሪ ሥጋት-ጭንቀት ሌላ ነዉ።ሐገሪቱ ከለየለየት የርስ በርስ ዉጊያ መግባት አለመግቧቷ ያስጨንቀዋል።ኑሮ ደግሞ ፈተና ነዉ።
ድምፅ
«(ቤንዚን ለማግኘት) ከተሰለፍኩ ሁለተኛ ቀኔ፥ ትርምስ ነዉ።ከትርምስ ሌላ ምንም የለም።»ይላሉ አንዱ።ሌላዉ፥-

«እዚሕ ሠነዓ ሁሉም ነገር ተገለባብጧል።ይሕ ገሐነብ እንጂ ከተማ አይደለም።»

ሠነዓ።የሚሊዮን ነዋሪዎቿ ሰሞናዊ ኑሮ።

ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ