1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአምንስቲ ማሳሰቢያ

ሐሙስ፣ ጥር 30 2011

ከዩናይትድ ስቴትስ፣ከብሪታንያና ከሌሎች ምዕራባዉያን መንግስታት በገፍ የሚሸመተዉ ቦምብ-ሚሳዬል፣ የአዳፍኔ አረር-ጥይት ብዙ ሺዎችን አርግፏል፣ሚሊዮኖችን በረሐብና በሽታ እየጠበሰ ነዉ፣ ሚሊዮኖችን አድም አሰድዷል ወይም አፈናቅሏል።

https://p.dw.com/p/3CwJo
Jemen | Bewaffnete Sympathisanten der Huthi-Rebellen
ምስል Getty Images/AFP/M. Huwais

Amnesty call for a halt to arms sale to Saudi-led coalition - MP3-Stereo

ምዕራባዉያን መንግሥታት የመን ዉስጥ ለሚዋጉት የአረብ ሐገራት የሚሸጡት ጦር መሳሪያ በጦር ወንጀለኝነት ከሚጠረጠሩ ሚሊሻዎች እጅ መግባቱን አምንስቲ ኢንተርናሽናል አጋለጠ።ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ትናንት ይፋ ባደረገዉ ጥናቱ እንዳለዉ በተለይ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከብሪታንያና ከዩናይትድ ስቴትስ የምትገዛዉን ጦር መሳሪያ ሊጠየቁ ለማይችሉ ቡድናት አሳልፋ እያስታጠቀች ነዉ።የዩናይትድ ስቴትስ መገናኛ ዘዴዎችም ዩናይትድ ስቴትስ ለሳዑዲ አረቢያና ለተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሚሸጡት ጦር መሳሪያ «አደገኛ» ለሚባሉ ሚሊሻዎች መተላለፉን ዘግበዋል።ነጋሽ መሐመድ ዝርዝር ዘገባ አለዉ።

የሪያድ፣የአቡዳቢ፣ የካይሮ ገዢዎችና ተከታዮቻቸዉ በቴሕራን ይደገፋል የሚባለዉን የየመን አማፂ ቡድን አንሳሩላሕ ወይም ሁቲን ለማጥፋት የመንን መቀጥቀጥ ከጀመሩ መጋቢት ላይ አራት ዓመት ይደፍናሉ።ከዩናይትድ ስቴትስ፣ከብሪታንያና ከሌሎች ምዕራባዉያን መንግስታት በገፍ የሚሸመተዉ ቦምብ-ሚሳዬል፣ የአዳፍኔ አረር-ጥይት ብዙ ሺዎችን አርግፏል፣ሚሊዮኖችን በረሐብና በሽታ እየጠበሰ ነዉ፣ ሚሊዮኖችን አድም አሰድዷል ወይም አፈናቅሏል።

እስካሁን ግን አሸናፊም-ተሸናፊም የለም።የሪያድ-አቡዳቢ-ካይሮ ገዢዎች ጦርነቱን ማሸነፍ ሲያቅታቸዉ፣በቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር ከምዕራብ መንግስታት የሚሸምቱትን ጦር መሳሪያ  ላደራጇቸዉ ሚሊሻዎች ያስታጥቁ ያዙ-አምንስቲ እንደሚለዉ።ይሕ በጥናት የተረጋገጠ ሐቅ ነዉ-ይላሉ የአምንስቲ ኢንተርናሽናል አጥኚ ፔትሪክ ዊልከን።የድርጅቱ የመገናኛ ዘዴ ከፍተኛ አማካሪ ኮነር ፎርቹን እንደሚሉት ደግሞ ሚሊሻዎቹ በጦር ወንጀልኝነት መጠርጠራቸዉ ጥፋቱን አስከፊ፣አስጊም ያደርገዋል።
                                           
«እነዚሕ ሚሊሻዎች የጦር ወንጀል መፈፀማቸዉን አምንስቲ ኢንተርናሽናልም ሌሎች ተቋማትም ያጠናከሩት ሰነድ ያረጋግጣል።ሥለዚሕ በጣም፣በጣም አሳሳቢ ነገር ነዉ።በዚሕም ምክንያት ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ለተባበሩት አረብ ኤምሬትም ሆነ ለሌሎቹ በሁለቱም ወገን ላሉ ተፋላሚ ኃይላት ማስታጠቃቸዉን እንዲያቆሙ በድጋሚ እንጠይቃለን።»
የአሜሪካ መገናኛ ዘዴዎች አሶስየትድ ፕሬስና CNN በየፊናቸዉ እንደዘገቡት የሪያድና የአቡዳቢ የጦር አዛዦች በርካታ የጦር መሳሪያና ገንዘብ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት ላለዉ ቡድን ለመስጠት ከቡድኑ መሪዎች ጋር ተስማምተዋል።
ምዕራባዉያን መንግስታት ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ሊቢያ፣ሶማሊ፣ አፍቃኒስታንና እዚያዉ የመን ዉስጥ አልቃኢዳና እስላማዊ መንግስትን ይወጋሉ።የአረብ መንግስታት የወዳጆቻቸዉን ጠላቶች የመን ዉስጥ ያስታጥቃሉ።የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ጥናት አልቃኢዳና እስላማዊ መንግስትን በስም አይጠቀሰም።ሌሎቹን ሚሊሻዎች ግን ይዘረዝራሉ-ኮነር ፎርቹን
                                                  
«የጃንት ብርጌድን፣የሸዋኒ ኃይላት፣ሌሎች የየመንን መንግስት የሚደግፉ ኃይላት ናቸዉ።እነዚሕ ኃይላት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚደገፉና የሚታጠቁ ናቸዉ።ይሁንና ቀደም ሲል እንዳልኩት ለየትኛዉም መንግስት ተጠሪ አይደሉም።በጣም የሚያሳሳስበን ለዚሕ ነዉ።እነዚሕ ኃይላት የመን ዉስጥ የጦር ወንጀልን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰት ያደረሱ መሆናቸዉን በመረጃ አረጋግጠናል።»
የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ጆሴፍ ቮቴል የአሜሪካ ጦር መሳሪያ ለየመን ሚሊሺያዎች ተሰጥቷል የሚለዉ ዘገባ እንዳሳሰባቸዉ አስታዉቀዋል።ጉዳዩን በቅርብ እንደሚከታተሉም ቃል ገብተዋል።ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር ሰላማዊ ሰዎችን መግደሉንና ተቋማትን ማጥፋቱን በመቃወም  ጀርመን፣ ኖርዌና ኔዘርላንድስ ለተባባሪዎቹ ሐገራት የሚሸጡትን ጦር መሳሪያ ለመገደብ ወስነዋል።ኮነር ፎርቹን ሌሎቹም መንግሥታት ተመሳይ እርምጃ መዉሰድ አለባቸዉ ይላሉ።
                                        

Jemen Meerenge Bab al-Mandab
ምስል Getty Images/AFP/S. Al-Obeidi
Iran Kampfflugzeug und Airbus A310
ምስል mehrnews
Jemen, Adan: Explosion eines Öltanks
ምስል Reuters/F. Salman

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ