1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየመን ቤተመንግስት ጥቃት

ዓርብ፣ ግንቦት 26 2003

በየመን ዛሬ በቤተመንስቱ ላይ በተፈጸመ የሮኬት ጥቃት ፕሬዝዳንት አብደላ ሳሌህን ጨምሮ የተወሰኑ ባለስልጣናት ቆስለዋል።

https://p.dw.com/p/RRia
ምስል AP

በመንግስት ታማኝ ሃይሎችና በተቃዋሚው የአሼድ ጎሳ ታጣቂዎች መካከል እንደአዲስ የተጋጋለውና ሰነዓን እያራደ ያለው ውጊያ የ60 ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል። ዛሬ በአብደላ ሳሌህ ቤተምንግስት ላይ የተፈጸው ጥቃት ሀገሪቱ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ለመግባት ከጫፍ መድረሷን ያሳያል ሲሉ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ተናግረዋል። የመንግስት ቴሌቪዥን ፕሬዝዳንቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና ለህዝብ ንግግር እንደሚያደርጉ ገልጿል። መሳይ መኮንን

ያለፈው ጥር ወር የጀመረው የየመን ቀውስ መልኩን እየቀየረ ነው። ሲጀምር በእርግጥ እንደ ግብጻና ቱኒዚያ የህዝብ ብሶት የፈነቀለው የህዝብ አብዮት በሚል ነበር። ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ግን በፕሬዝዳንት አብደላ ሳሌህ ታማኞችና በሼክ ሳዲቅ አል ሀማር በሚመራው የጎሳ ታጣቂ ቡድን መሀል በሚካሄድ የጦፈ ውጊያ ተቀይሯል። ርዕሰ ከተማዋ ሰነዓ የጦር አውድማ ሆና አርፋለች። ትላንት በሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያ የተቀጣጠለው ጦርነት ሀገሪቱን ወዴት ይወስዳት ይሆን የሚል ስጋት ያጠላበት ሆኖ ነበር። ዛሬ ድንገት የአብደላ ሳሌህ ቤተመንግስት በሮኬት ተመታና ነገሮችን የበለጠ አወሳሰባቸው። በእርግጥም የዛሬው የቤተመንግስት ጥቃት የመን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ልታመራ ነው የሚለውን ስጋት አጠናክሯል። እንደ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ድንገት በአብደላ ሳሌህ ቤተመንግስት በተፈጸመው የሮኬት ጥቃት ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ ከፍተኛ ሹሞችን አቁስሏል። በእርግጥ ለዛሬው የአርብ ጸሎት በቤተመንግስቱ ቅጥር ግቢ በሚገኝ መስጊድ ፕሬዝዳንቱና ባለስልጣናቶቻቸው የጸሎት ስነስርዓት ላይ ነበሩ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች የሳሌህ ከፍተኛ ባለስልጣናት በጥቃቱ ሲቆስሉ ፕሬዝዳንቱም መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ዝገባዎች አመላክተዋል። የየመን ቴሌቪዥን አብደላ ሳሌህ ደህና ናቸው የሚል ተከታታይ መልዕክት ቢያሰማም ስላለመቁሰላቸው ግን ማስተባበያ አልሰጠም። በዛሬው ጥቃት አራት የቤተመንግስት ሪፐብሊካን ዘብ ከፍተኛ መኮንኖች ተገድለዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የደህንነትና መከላከያ አማካሪ ጄነራል ራሻድ አል አሊሚ ክፉኛ ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል ተብሏል። ጥቃቱን የፈጸመው የአሼድ ጎሳ እንደሆነ የመንግስት ቃላአቀባይ አስታውቋል። አሼድ ሁሉንም ቀይ መስመሮች እያለፈ አሉ ቃል አቀባይ ታሬቅ አል ሻሚ ዛሬ ለጋዜጠኞች። ይህ የቤተመንግስት ጥቃት የየመንን ቀውስ ወዴት እንደሚወስደው በእርግጥ እያነጋገረ ነው። በዶሃ ብሩኪንግ የምርምር ማዕከል የፖለቲካ ተንታኝ ኢብራሂም ግራሃምሼ አብደላ ሳሌህ ሁለት ምርጫዎች ቀርቦላቸል ይላሉ።

«ፕሬዝዳንት አብደላ ሳሌህ ሁለት አማራጮች አሏቸው። አንደኛው የየመንን ቀውስ ለማብረድ እንዳልቻሉ፤ በታሂሪር አደባባይ የሚሰማውን የህዝብ ጥያቄ ወደ ጎን መግፋት እንደማያዋጣና የሚፈለገውን እርምጃ እንዲወስዱ የሚያደርጋቸው። የረገጡትን የሰላም ጥያቄ እንዲቀበሉ የሚያደርጋቸው ታሪካዊ አጋጣሚ ነው። ሌላኛው አማራጫቸው ይህን ጥቃት ሰበብ አድርገው ቀውሱን ለማባባስና ለሼክ ሳዲቅ አል አማር ቡድን አጸፋውን በመለስ ጊዜ ለመግዛት ይጠቀሙበታል። በእርግጥ ይሄ ለፕሬዝዳንት ሳሌህም ሆነ ለሀገሪቱ ምንም አይጠቅምም።»

የመን ቅውስ ለመግባት ዋዜባ ላይ ከነበረችበት ጊዜ አንስቶ አብደላ ሳሌህ ሁሌም የሚሉት እኔ ከሌለው ሀገሪቱ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ትገባለች ነው። ይህን መነሻ አድርገው ሁለት ሳምንቱን የያዘው ውጊያ እንዲቀሰቀስ ራሳቸው ፕሬዝዳንቱ ፍላጎት ሳይኖራቸው አይቀርም የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። የመካከለኛ ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኝ አብዱ ጋሃኒ አል ኢርያኒ እንደሚሉት አብደላ ሳሌህ የማያዋጣቸውን ሂሳብ አስልተዋል።

«በመሰረቱ አብደላ ሳሌህ የተሳሳተ ስሌት ይዘዋል። ጦርነትን ልትጀምረው ትችላለህ። ወዴት እንደሚያመራ ግን አታውቀውም። እና እንደሚመስለኝ ሁኔታዎች ለሳሌህ ከቁጥጥራቸው ውጪ ሆነዋል። በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የበቀል እርምጃ ይወስዳሉ ብዬ እጠብቃለሁ።»

አብዱ ጋሃኒ አል ኢርያኒ አክለው እንደሚሉት የእርስ በእርስ ግጭት በመፍጠር የተሻለ ጠንካራ ሃይል ሆኖ መውጣት የሳሌህ ዕቅድ ነው። ግጭት በመፍጠር ከዚያ በሚገኘው ግርግር ተቃዋሚዎችን መደፍጠጥና ቅስም መስበር ነው የሳሌህ ስሌት።

«ይህ በሳሌህ የታቀደ የሃይል ሚዛኑን እሳቸው ወደሚፈልጉት ለማዞር አልመው የቀሰቀሱት ግጭት ነው። ይህን ካደረጉ በኋላ የሃይል ክፍፍል የድርድር ጥሪ ያቀርቡና ከእንደገና ማንሰራራት የሚችሉበትን ቀዳዳ ይፈልጋሉ። በድርድር የተወሰኑ ነገሮችን በመተው ግን ዋናው ሃይል ሆነው ብቅ ማለት ነው ዕቅዳቸው። ይህ ፈጽሞ ከሰላማዊው የህዝብ አብዮት ሂደት ውጪ ነው።»

ዛሬ የፕሬዝዳንት ሳሌህን ቤተመንግስት ያናወጠው የሮኬት ጥቃት የተፈጸመው የፕሬዝዳንቱ ታማኝ ሃይሎች የሼክ ሳዲቅ አል አማር መኖሪያ ቤትን ለማጥቃት ዛሬ ጠዋት እንቅስቃሴ ባደረጉ ጊዜ ነበር። በሁለቱ ሃይሎች መሃል የሚካሄደውን ውጊያ ተኩስ አቁም ስምምነት ጋብ ቢያደርገውም ያለፈው ማክሰኞ ስምነቱ ተጥሶ ዳግሞ ሰነዓን ማንቀጥቀጡን ቀጥሏል። በእስከአሁንም ከ60 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ፕሬዝዳንት አብደላ ሳሌህ በተደጋጋሚ የቀረበላቸውን የስልጣን ይልቀቁ ጥያቄ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገው እስከአሁን ዘልቀዋል። በኳታር መሪነት እየተደረገ የነበረው ሽምግልና ከጫፍ እየደረሰ ሲስተጓጎል የነበረውም በእሳቸው ምክንያት ነው። በእርግጥ የዛሬ ጥቃት በአንድም ይሁን በሌላ የተጀመረውንሽምግልና ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል ተብሏል። የዛሬውን መሰል ጥቃት የመንን ወደ ከፋ ብጥብጥ ከመክተት በቀር የትኛውም ወገን የሚያተርፈው ነገር የለም ይላሉ የዶሃ ብሩኪንግ የምርምር ማዕከል የፖለቲካ ተንታኝ ኢብራሂም ግራሃምሼ

«ይህ ለማንም ጥሩ አይደለም። ለተቃዋሚዎች፤ ለአብደላ ሳሌህ፤ ለአከባቢው ሀገራት እንደ ሳዑዲ አረቢያና አሜሪካ ለመሳሰሉ በየመን ጉዳይ የተለየ ትኩረት ለሰጡ ሀገራት ብቻ ለሁሉም ጥሩ ነገር የሚያስገኝ ሊሆን አይቸልም። የመን ወደእርስ በእርስ ጦርነት እንድታመራ የማንም ፍላጎት አይደለም። በእርግጥ ሁኔታዎች ወደዛ እያመሩ ይመስላሉ። የመንን በዚህ ውስጥ እያለች ብቻዋን ትወጣው ማለት አይቻልም። »

የመን ቀውስ ውስጥ ከገባች አምስተኛ ወሯን ይዛለች። በእስከአሁን ከ350 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከእነዚህም 135 የሚሆኑት ባለፉት 10 ቀናት ውጊያ የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው።

መሳይ መኮንን

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሰ