1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየመን የረሐብ ሥጋት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 2 2006

ከግማሽ የሚበልጠዉ የየመን ሕዝብ ሠብአዊ ርዳታ እንደሚያሥፈልገዉ የተባበሩት መንግሥታት የሠብአዊ ርዳታ ማስተባባሪያ ቢሮ (OCHA በምሕፃሩ) እስታወቀ።OCHA እንደሚለዉ ለችግር ለተጋለጠዉ የመናዊ እስቸኳይ ርዳታ ካልደረሰ ለመገመት የሚከብድ ሠብአዊ ድቀት መከሰቱ አይቀርም።

https://p.dw.com/p/1CYMg
Jemen Checkpoint einer schiitischen Miliz in der Provinz Omran 03.06.2014
ምስል Reuters

ሠብአዊ ርዳታ ከሚያስፈልገዉ የመናዊ መሐል 3,5 ሚሊዮኑ ችግሩ ጠንቶባቸዉ ለረሐብ ተጋልጠዋል።ድርጅቱ እንደሚለዉ ለየመን ሕዝብ እርዳታ እንዲያደረግ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ከለጋሽ መንግሥታት እስካሁን ያገኘዉ ምላሽ አነስተኛ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ የኦቻ ቃል አቀባይን አነጋግሮ ነበር። የጀነት-ገነት ተምሳሌቲቱ ምድር፦ በሥልጣን ሽኩቻ፤በርዕዮተ-ዓለም ፍትጊያ፤በሐብት ሽሚያ፤ በጎሳ- ጠብ ያልታወከች፤ያልተመሰቃቀለችበት ቅርብ ዘመን በርግጥ አልነበረም። የለምም።ዛሬም በፈረጀ-ብዙ ትርምስ-ምስቅልቅሏ መሐል-ያን ጥንታዊ ኩሩ ሕዝብ ቁል-ቁል የሚደፍቀዉ መከራ ታከለበት።ረሐብ።


«እኛ እንዳሰላነዉ ሐምሳ ስምንት ከመቶዉ ሕዝብ ማለትም ከየአስሩ የመናዊ ስድስቱ ሠብአዊ ርዳታ ያስፈልገዋል።ብዙዎቹ በጣም የሚያስፈጋቸዉ ለመኖር በጣም መሠረታዊ ነገሮች ናቸዉ።ምግብ፤ንፅሕ ዉሐ፤ጤና ና መጠለያ።»
ይላሉ የኦቻ ቃል አቀባይ የንስ ሌርከ።ከየአስሩ-ስድስቱ፤ ከ24 ሚሊዮኑ የየመን ሕዝብ 14,7 ሚሊዮኑ ርዳታ ጠባቂ ነዉ።ከዚሕ መሐል ደግሞ 4,5 ሚሊዮኑ ችግሩ እጅግ ጠንቶበት-የሚላስ የሚቀመንስ እንኳ የለዉም።

«የመን ዉስጥ ወላጆች እንበል ዛሬ ጠዋት ከመኝታቸዉ ሲነሱ ለልጆቻቸዉ የሚሰጡት ምግብ ያግኙ-አያግኙ እርግጠኛ አይደሉም።ይሕ በጣም አስከፊ ነዉ።ምክንያቱም በቃ-ይራባሉና።»
ዓለም አቀፉ ድርጅት፤ ባለሥልጣናቱ እንደሚሉት፤ ለችግረኛዉ ሕዝብ መርጃ ለጋሾች 529 ሚሊዮን ዶላር እንዲረዱ በተደጋጋሚ ጠይቆ ነበር።የተሰጠዉ ከጠየቀዉ 33 በመቶ ብቻ ነዉ።

በዚሕም ምክንያት ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች ከችግረኛዉ መሐል-ረሐብተኛዉን፤ከረሐብትኛዉም በጣም የባሰበትን መርጠዉ ለአንድ ሚሊዮኑ ያክል ምግብ ሲያድሉ ነበር።አሁን ቃል አቀባይ ሌርከ እንደሚሉት ለእነሱም የሚስጠዉ እየተሟጠጠ፤ ሥጋቱ ባንፃሩ እየገዘፈ ነዉ።

«ይሕ ባለፉት ጥቂት ቀናት ወይም ሳምንታት ዉስጥ የተከሰተ ሠብአዊ ድቀት አይደለም።ለብዙ ዓመታት የተከማቸ ችግር ነዉ ነዉ።አሁን ግን በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነን።በጣም እየጠና ነዉ።የርዳታ ድርጅቶች ችግረኛዉን ለመርዳት ባስቸኳይ ገንዘብ ካላገኙ፤ለችግረኛዉ ሕዝብ ርዳታዉን ማቀበል ካልቻሉ---ነገሮች በርግጥ ይበላሻሉ።»
የተከማቸዉ ችግር የመን ላይ ፀረ-ሽብር ዘመቻ ከተከፈተ ወዲሕ ይከመር ያዘ።ዘመቻዉ ለአማፂያን ዉጊያ፤ ለሽፍቶች ዘረፋና እገታ በር ከፍቶ ወትሮም-ሥርዓት የማታዉቀዉን ሐገር-ቅጥ አሳጥቷታል።በነዚሕ ላይ ሙስና ሕዝባዊ አመፅ፤የመገንጠል ንቅናቄ-ያካልባት ገባ።

ድርብርቡ ችግር ያሥራበዉ የመኖችን ብቻ አይደለም።እዚያ የተጠለሉ የኢትዮጵያ፤የሶማሊያ፤ የኤርትራ ስደተኞችንም ጭምር-እንጂ።

«እዚያ የሚገኙ ሥደተኞችም በጣም አስከፊ ሁኔታ ላይ ናቸዉ።እንዳልከዉ ሥደተኛ ናቸዉ። ወደ ሌላ ሐገር ለመሻገር የሚሹ ፈላሾችም ናቸዉ።ግን የመን ዉስጥ ተቃርጠዉ፤ ወደፊትም መሔድ ወደ ኋላም መመለስ በማይችሉበት ሁኔታ መላወሻ አጥተዋል።»
የመን ከሁለት መቶ ሐምሳ ሺሕ የሚበልጡ የአፍሪቃ ቀንድ ስደተኞች ሠፍረዉባትል።ደቡብና ሰሜን ግዛቶችዋን የሚያብጠዉ ግጭትና ጦርነት ደግሞ 320 ሺሕ ዜጎችዋን አፈናቅሏል።

Hunger im Jemen
ምስል picture-alliance/dpa
Hunger im Jemen
ምስል AP
Hunger im Jemen
ምስል AP

ነጋሽ መሃመድ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ