1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩኒቨርሲቲዎቹ ተቃውሞ በኢትዮጵያ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 6 2010

በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ በኢትዮጵያ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መዘጋታቸውን በርካታ የመገናኛ አውታሮች ዘግበዋል። የዚምባብዌ አዲሱ አስተዳደር የኢትዮጵያ የቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያምን አሳልፎ እንደማይሰጥ መግለጡም ተዘግቧል። 

https://p.dw.com/p/2pSUp
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የዩኒቨርሲቲዎቹ ተቃውሞና የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መዘጋት

የኢትዮጵያ የቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ከዚምባብዌ ተላልፈው ለኢትዮጵያ እንደማይሰጡ የመገለጡ ዜና የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የመነጋገሪያ ርእስ ነበር። የቀድሞው የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በዘመነ-ሥልጣናቸው ኮሎኔል መንግሥቱ ተላልፈው እንዳይሰጡ አድርገዋል። በኬንያ ዋነኛ ተነባቢው ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ በድረ-ገጽ ባወጣው ጽሑፍ የዚምባብዌ አዲሱ አስተዳደርም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን ወደ ኢትዮጵያ አሳልፎ እንደማይሰጥ መግለጡን ዘግቧል። ምንም እንኳን የዚምባብዌ መንግሥት ተቃዋሚዎች ኮሎኔል መንግስቱ ተላልፈው እንዲሰጡ የሚፈልጉ ቢሆንም፤ የዚምባብዌ መንግሥት በሮበርት ሙጋቤ የተያዘውን አቋም በፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋም የሚጠበቅ መኾኑ ተገልጧል። የፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ቃል አቀባይ ጆርጅ ቻራምባ መንግሥቱ ተላልፈው እንደማይሰጡ የተናገሩት በዚምባብዌ ዋነኛ ዕለታዊ ጋዜጦች መካከል አንዱ በኾነው ዴይሊ ኒውስ ነው። 

ቻራምባ ለጋዜጣው በሰጡት መግለጫ፦ «ሲመስለኝ ያ ዋና ጉዳያችን አይደለም» ብለዋል። «የኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ አላቀረበም» ያሉት ቃል አቀባዩ የዚምባብዌ ተቃዋሚዎችን፦ «እናስ እነሱ ምን በማያገባቸው ጥልቅ አደረጋቸው?» ሲሉ ተችተዋል። ኮሎኔል መንግሥቱ ዚምባብዌ ስለቀሩበት ኹኔታም ለተቃዋሚዎቹ ሲያብራሩ «እንዴት እንደመጡ እንኳን ዐያውቁም። የእሳቸው ጉዳይ በዓለም አቀፍ ፕሮቶኮል የተስተናገደ ነው» ብለዋል። የኮሎኔል መንግሥቱ ተላልፎ መሰጠት ጉዳይ የዚምባቤዌ አዲሱ መንግሥት አጀንዳ አለመኾኑንም ተናግረዋል። ይኽ ዜና በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲዘዋወር የተለያዩ አስተያየቶችም ተሰንዝረውበታል። 

ሳሙኤል መታ በፌስቡክ ገጹ ባቀረበው ጽሑፍ፦ «ዚምባቡዌ መንግስቱ ኃይለማርያምን አሳልፌ አልሰጥም አለች» የሚል ጽሑፍ አያይዞ «ጥሩ» ብሏል። «እስኪ አሁን ጀግናውን ሰው ከተቀመጠበት ስለ ጀግናው መንግስቱ ተውና ስለወያኔ ግፍ ንገሩን አታዘናጉን» የሚል አስተያየት የሰጠው ደግሞ አገሬ አገሬ ነው። ራስ ዳሸ በተባለ የፌስቡክ ስም የቀረበ አስተያየት ደግሞ፦ «ሁለቱም መንግሥታት ዜጐችን የገደሉ ናቸው። አንዱ ርእዮተዓለምንና መደብን መሰረት አድርጎ ሌላው ደግሞ የብሔር ልዩነትን መሰረት አድርጎ»  በሚል አስተያየት ሰጥቷል። የደርግ እና የኢሕአዴግን  fገዛዝ በማነፃጸር። 

Äthiopien Anhänger Arbeiterpartei
ምስል Getty Images/AFP/A. Joe

የኢትዮጵያ ቀድሞው ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግሥቱን ያወደሱ በርካቶች የመኾናቸውን ያኽል፤ በዘመነ-ሥልጣናቸው ለፈጸሙት ግፍ ሊጠየቁ ይገባል ያሉትም ብዙዎች ናቸው። ዴቪድ በትዊተር ገፁ ባቀረበው ጽሑፍ «አምባገነኑ መንግሥቱ ሚሊዮኖች በተራቡበት ወቅት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድሏል። በአፋጣኝ ወደ መጣበት መመለስ አለበት» ሲል አተያየት አስፍሯል።  የመንግሥቱ ዘመንን በአኹኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ግድያ እና እስራት ጋር በማያያዝም መንግሥቱን ጀግና ሲሉ ያወደሱ በርካቶች ናቸው።

በአጭሩ፦ «መንጌ ማረን» ሲል በፌስቡክ አስተያየት የሰጠው ደጀን ፍስኃ  ነው። ዓለም ማሞ በትዊተር ያቀረበው ጽሑፍ ደግሞ እንዲህ ይነበባል። « መንግሥቱ ፍትኅ አደባባይ መቅረብ ካለበት ሄግ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኚያ ፍርድ ቤት ነው። ከእሱ ባልተናነሰ ገዳይ እና ወንጀለኛ ለኾነው ሕውሓት አሳልፎ መስጠት ተቀባይነት የሌለው መንግሥትን ሕጋዊ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ ለፍትኅ የሚሰጠውን ዋጋም መራከስ ነው» ብሏል። 

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባባቢዎች በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በተመሳሳይ ወቅት ተቃውሞ እና ግጭት የተስተዋለውም በዚሁ ሳምንት ነው። ከግጭት ተቃውሞዎቹ መካከል በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሐረርጌ፤ ጨለንቆ ውስጥ የመንግሥት ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ 15 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችም ግድያ መፈጸሙ ተገልጧል። 

በርካቶች የመንግሥት ታጣቂዎች በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ጨለንቆ ነዋሪዎች  የፈጸሙትን  ግድድያ እና ድብደባ  በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ተቃውመው ጽፈዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች እና ጨለንቆ ውስጥ ስለተከሰተው ግድያ በሰጠው መግለጫ መቸገሩን ገልጧል። ኤምባሲው በድረገጽ መግለጫው እንዳስነበበው፦ «በጨለንቆ ከተማ እና በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ግድያ እና የመቁሰል አደጋ ባስከተለው ግጭት ዘገባዎች አዝነናል ተቸግረናልም» ብሏል። መንግሥት ለአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ደኅንነት ዋስትና እንዲሰጥ በግጭቱ እጃቸው ያለበትም ተጠያቂ እንዲኾኑ አሳስቧል። «የሚደነቅ» ያለውን የኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ የመከባበር የረዥም ዘመን ባህሉንም አበረታትቷል።
ቀደም ሲል የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪቃ ጉዳዮች ተመልካች  ኃላፊ የነበሩት ሔርማን ኮህንም  «ወደ ለየለት ትርምስ » እንዳይገባ ስጋታቸውን በትዊተር ገጻቸው ገልጠዋል እንዲህ ሲሉ፦ «የኢትዮጵያ ሕወሓት መሪዎች ሕግና ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ ከመፍረሱ በፊት አዲስ ዲሞክራሲያዊ ሂደት እንዲወለድ የሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ጉባኤ እንዲያኪያሂዱ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥያቄ የምር ቢያጤኑት ይበጃቸዋል» ብለዋል። አባባሉን በሁለት ቢላ እንደመብላት የቆጠሩት በርካቶች ናቸው። 

ጋዜጠኛ አርጋው አሽኔ፦ የሄርማን ኮህን ማንነትን ሲያብራራ «ሔርማን ኮህን የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ በሽግግር ሒደት ላይ እንዲወያይ መክረዋል» ሲል በትዊተር ጽፏል። አርጋው ቀጠል አድርጎም «ጥሩ ምክር! ግን ችግሩ ያለው ኮህን በአኹኑ ወቅት የኤርትራ ተከፋይ አማካሪ መኾናቸው ላይ ነው። በዚያ ላይ በ1991ዱ ድርድር ወቅት የኢትዮጵያን ሕዝብ ክደዋል» ሲል ጽሑፍን አጠቃሏል። 

Symbolbild Social Media
ምስል DW/S. Leidel

ዳናኤል ደብልዩ ደግሞ ለሄርማን ኮህን ጽሑፍ በሰጠው ምላሽ «በ1990/91 የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ማደራደር ዛሬ ያለንበት ጋር አድርሶናል» ብሏል። አያይዞም «ከማንም በላይ ያን እርስዎ ያውቃሉ። ዩናይትድ ስቴትስ የምትጨነቀው ኢትዮጵያ ስላላት የመሬት መጠን ነው፤ ስለኢትዮጵያውያን ፈጽሞ ደንታ የላትም» ሲል ጽሑፉን ቋጭቷል።   

ግጭቶቹን ተከትሎ የማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች በዙር አዙር ካልኾነ በስተቀር አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውም በዛው በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ተጽፎ ተነቧል። ቄሮ ዴካሜ «ምንም የመንግስት ወግ የላቻው አሁንም አስተሳሰባቸው እዛ ደደቢት በረሃ እደነበረው ነው» ብሏል። ሚካኤል ወን ቦጋለ፦ «እውነት ነው መፍትሔ ተብሎ የተወሰደ እምጃ መሆኑ ነው» ሲል ርምጃውን አጠይቋል። «መዝጊያ በማጥበቅ ስልጣን ላይ መቆየት አይቻልም። ወያኔ ከኔክሽን አጥፍቶብናል» ሲል አስተያየት የሰጠው ደግሞ የኢትዮጵያ ልጅ በላይ ነው። በዛው በፌስቡክ ላይ ተዘጋ መባሉን የደገፉም አልታጡም። ዘባጭ ነይኮ በሚል የፌስቡ ስም የተሰጠ አጭር አስተያት «እሰይ» ሲል ይነበባል።  «ምንም ችግር የለም ውሸት ነው» ያለው ክንፉ ገብሬ ነው። «ኧረ፤ ይሰራል እንዴ ዋሻችሁ !!» ሲል ሠራ መባሉ ሐሰት መኾኑን ገልጧል። 

«እረ እነዚህ ሰዎች ሬዲዮኑንም እንዳይዘጉት ምን ቀረ መሰላችሁ» በዋትስአፕ ከኢትዮጵያ የደረሰን መልእክት ነው። «ፌስ ብክ እና የመሳሰሉት የሁከት መሳርያዎች በኢትዮጵያ ምድር ለዘላዓለም ይዘጉ፤ እነሱ ካልተዘጉ ሰላም የለንም ።መንግስት አሁን ነው ጥሩ ስራ የሰራ። በዚህ እንዲቀጥል ጫና ማሳደር አለብን። በፌስ ብክ ሃገራችን መፍረስ የለባትም» የሚል አስተያየትም ከዛው ከኢትዮጵያ በፌስቡክ ደርሶናል። «መንግሥት ሀገር ውሥጥ ችግር ሢኖር ኔትወርክ መዝጋት አሁን አልጀመረም» ይኽም በዋትሰፕ ከኢትዮጵያ የደረሰን መልእክት ነው።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ