1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የፀጥታ ስጋት በኢትዮጵያ

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ ጥቅምት 27 2010

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ከሁለት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እንዲማሩ የተመደቡ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች «ለደህንነታቸዉ» ሲባል በሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመደቡ ከፌዴራሉ የትምህርት ሚንስቴር ጋር በመሥራት ላይ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

https://p.dw.com/p/2n82q
20.06.2013 DW Online Karten Basis Aethiopien spanisch

mmt Insecured University Students in Ethio- Somalia and Oromia Reg. State - MP3-Stereo

በኦሮሚያ ክልልና በኢትዮጵያ-ስማሊ አዋሳኝ ድንበሮች  ለብዙ ሰዎች ሞትና ለሺህዎች መፈናቀል ምክንያት የሆነው ግጭት መዘዝ በተለያየ መልኩ እየታየ ነው ። የሁለቱም ክልሎች መስተዳደሮችና የአገር ሽማግሌዎች ለግጭቱ መፍትሄ ለመስጠት ከአንዴም ሁለቴ ቢገናኙም እስካሁን ግጭቱንና የፀጥታ ስጋቱን መግታት እንዳልቻለ የፖለትካ ተንታኞች ያስረዳሉ።

ጥቅምት 18 ቀን 2010 ዓ/ም የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚገኘዉ በጅግጅጋ ዩኒቨርስት የሚማሩ የኦሮሞ ተወላጆች ደህንነታቸዉ «አሳሳብ ሁኔታ» ላይ ስለሚገኝ «ለደህንነታቸዉ» ሲባል ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመደቡ መወሰኑን የክልሉ የኮሙዩኒኬሼን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በፌስቡክ ገጻቸዉ ላይ አስፍረዉ ነበር። ምደባቸዉንም ትምህርት ሚንስቴር ኢያጠናቀቀ እንደሚገኝም አቶ አዲሱ አሳዉቀዋል። ምድባቸዉ እስከሚታወቅ ድረስ ተማሪዎቹ ከዩኒቨርሲቲዉ ግቢ እንዳይወጡና በትዕግስት እንዲጠባበቁም አቶ አዲሱ አሳስበዋል።

ባለፈዉ አርብም ትምህርት ሚኒስቴር በጅግጅጋ ዩኒቨርስት ሲማሩ የነበሩ ወይም አዲስ የተመደቡ የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ወይም አዲስ ተመዳቢ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች በሌሎች ክልሎች ዩኒቨርስቲዎች እንዲመደቡ መወሰኑን በፌስቡክ ደረ ገፁ ላይ አስፍረዋል። እዚህ ዉሳኔ ላይ የተደረሰዉም «ተከስቶ በነበረው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት» ጊዜያዊ መፍትሄ ለማበጀት መሆኑ ተገልጿል።። 
ጊዜያዊ መፍትሄ የተባለውን ይህን ርምጃ በበጎ የተመለከቱ ሲኖሩ ሌሎች ደግሞ እንዲህ አይነት እርምጃ አገሪቱን «ይበጣጥሳል» ስሉ አስተያየተቸዉን ለዶቼ ቬሌ አጋርተዋል። ከጅንካ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አስተያየት ደግሞ ሰጭ ይህን ብለዋል።

Äthiopien Stadt Jijiga
ምስል DW/T. Waldyes

መፍትሄው ጊዜያዊ ይባል እንጅ ወደ ፊት እንድ አይነት ግጭት ሲከሰት አንዱ ክልል ከሌላዉ ዩንቨርሲቲ የክልሉን ተወላጆች የማያስወጣበት ምክንያት የለም ሲሉ እኝሁ አስተያየት ሰጭ ጨምረው ገልፀዋል። በዋትስአፕ በድምጽ አስተያየት የላኩልን ሌላ ሰው ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ርምጃ «ሌላ ስጋት» ዉስጥ የሚያስገባ ነዉ ይላሉ።

ናስር አባሚልክ የሚል የፌስቡክ ስም የያዙም ግለሰብም ሚኒስትር መሥርያ ቤቱ ጊዜያዊ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈልግ አሳስበዋል።

ላታ ባል የተባሉ ሌላ የፌስቡክ አስተያየት ሰጭ ደግሞ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወሰደዉ ርምጃ ትክክለኛ ነዉ ይላል። ምክንያቱም ተማሪዎች «ለመማር የተረጋጋ መንፈስ እና አካባቢ ያስፈልጋቸዋል፣ ይህ በሌለበትና አሁንም ግጭቶች ብዙ ቦታዎች እየተከሰቱና ሰዎች እየሞቱ ባለበት ሁኔታ እነዚህን ተማሪዎች መላክ ሆን ተብሎ ለአደጋ እንዲጋለጡ ከማዲረግ ዉጪ ሌላ ትርጉም የለውም» ይላሉ፡፡ ሌል አስተያየት ሰጭም ከለታ ጋር የሚመሳሰል ሀሳብ ሰንዝረዋል።

ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ተዘዋዉሮ መማር፣ መኖር እንድሁም መስራት መከልከሉ «ጥሩ አይመስለኝም» የሚሉት የድሬዳዋ ከተማ ነዋር አቶ ታረቀኝ አለማዬሁ አሁን የተወሰደዉ ርምጃ በጊዜዉ አኳኋን ተገቢ ነዉ ይላሉ።

በኦሮሚያ ክልል በኩል ግጭቱን ለመፍታት ተነሳሽነት አለ የሚሉት አቶ ታረቀኝ በኢትዮጵያ ሶማሌ በኩል ይህ አይታይም ይላሉ። አሁንም «በልዩ ፖሊስ» የሰዎች መሞትና መዘረፍ ወሬ እንደሚሰሙ፣ የፌደራል መንግስትም ለጉዳዩ እልባት መፈለግ እንዳልቻለ አቶ ታረቀኝ ለዶይቼ ቬሌ ይናገራሉ። በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎችን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

መርጋ ዮናስ

ኂሩት መለሰ