1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩናይትድ ስቴትሱ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 30 2013

በአፍሪቃ ቀንድ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሬይ ፌልትማን የአፍሪቃ ጉዟቸውን ቀጥለው ትናንት ሱዳን ገብተዋል። ጄፍሬይ ፌልትማን የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ኾነው በተሾሙበት ወቅት ኢትዮጵያን በተመለከተ የተናገሩት አወዛጋቢ ንግግር በበርካቶች ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታዩ አድርጓል።

https://p.dw.com/p/3t7vo
Jeffrey Feltman UN-Untergeneralsekretär
ምስል Getty Images/AFP/R. Arboleda

የጄፍሬይ ፌልትማን የአፍሪቃ ጉዞ

በአፍሪቃ ቀንድ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሬይ ፌልትማን የአፍሪቃ ጉዟቸውን ቀጥለው ትናንት ሱዳን ገብተዋል። ጄፍሬይ ፌልትማን  በመጀመሪያ ግብጽን ከጎበኙ በኋላ፤ ሱዳን ውስጥ ትናንት ከባለሥልጣናቱ ጋር ተነጋግረው ነበር። ከዚያ  ቀደም ብሎ ከትናንት በስትያ ወደ ኤርትራ ማቅናታቸውም ተዘግቧል። ከኤርትራው ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋርም ዴንደን የእንግዳ ማረፊያ ውስጥ መወያየታቸውን የኤርትራ የማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።  «ለአራት ሰአታት በዘለቀው ረዥም ስብሰባ  አሜሪካ የአፍሪቃ ቀንድ ችግሮችን ለመፍታት በምታደርገው ጥረት ኤርትራ በትብብር ለመሥራት ዝግጁነቷን ፕሬዚደንት ኢሳያስ  አስምረውበታል» ብለዋል።    

ጄፍሬይ ፌልትማን በሱዳን የሁለት ቀናት ቆይታቸው ኢትዮጵያ ግብፅ እና ሱዳንን ስላወዛገበው የአባይ ግድብ እንዲሁም ለም ስለሆነው የድንበር ግዛት እንደሚነጋገሩ የሱዳን መንግሥታዊ የዜና ተቋም ሱና መዘገቡን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አትቷል። 

የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልእክተኛው በሱዳኑ የሁለት ቀናት ቆይታቸው ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ቡራኒ፣ ከጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ እንዲሁም ከሌሎች የሱዳን ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያዩ የዜና ምንጩ አክሎ ዘግቧል። 

Infografik Karte Grand Ethiopian Renaissance Dam ENG

አምባሳደር ጄፍሬይ ፌልትማን ባሳለፍነው ረቡዕ ከፕሬዝዳንት አብዱልፋታህ አል ሲሲ ጋር ካይሮ ውስጥ ተገናኝተው ተወያይተዋል። በዕለቱም የግብፁ ፕሬዚደንት «ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ግድብ ምክንያት ከናይል ወንዝ የግብጽን የውኃ ድርሻ ሊቀንስ የሚችል ማንኛውም የኢትዮጵያ ርምጃን» ካይሮ አትታገስም ሲሉ በድጋሚ ማስጠንቀቃቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።  

የ«ታላቁ የሕዳሴ ግድብ» የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌትን ባለፈው የክረምት ወራት ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያ በቀጣዩ የክረምት ወራት ሁለተኛውን ዙር ሙሌት ለመፈጸም የሚያግዳት አንዳችም ኃይል አለመኖሩን በተደጋጋሚ ዐስታውቃለች።  እንደ ዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መረጃ ከሆነ  ጄፍሬይ ፌልትማን  ግብፅ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያን በመጎብኘት ከእየ ሃገራቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ይወያያሉ።

ጄፍሬይ ፌልትማን የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ኾነው በተሾሙበት ወቅት ኢትዮጵያን በተመለከተ የተናገሩት አወዛጋቢ ንግግር በበርካቶች ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታዩ አድርጓል። ጄፍሬይ ፌልትማን የአፍሪቃ ቀንድ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልእክተኛ ኾነው ከተሾሙ በኋላ ከፎሬይን ፖሊሲ ጋር  ባደረጉት የመጀመሪያ ቃለ መጠይቅ፦ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ግጭት ወደ ቀጣናዊ ግጭት ሊሻገር የሚችል ነው በማለት እጅግ ከፍተኛ ውድመት እና ጥፋት ካስከተለው የሶሪያ ጦርነት ጋር ለማመሳሰል ሞክረዋል። ይህ ንጽጽራቸው አንድም ለቀጣናው ያላቸው ምልከታ በብዥታ የተሞላ አለያም አድሏዊ ነው የሚሉ ብርቱ ትችቶችም ተሰንዝሮባቸዋል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ