1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት የእስያ ጉብኝት

ሐሙስ፣ ኅዳር 10 2002

የሐገሪቱ ገዢ የኮሚንስት ፓርቲ ልሳን ሮዶንግ ሲንሙን ዛሬ በርዕሠ-አንቀሱ «ጠብ-ጫሪ ሐይላት ያላቸዉ ዩናይትድ ስቴትስና ደቡብ ኮሪያ አሁንም ዲሞክራቲክ ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ኮሪያን ለመዉረር እየተዘጋጁ ነዉ።»

https://p.dw.com/p/KbBu
ኦባማን ሊ ሲቀበሉምስል AP

19 11 09

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ለአንድ ሳምንት ያሕል በእስያ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀዉ ዛሬ ወደ ሐገራቸዉ ተመልሱ።ኦባማ በአራት የእስያ ሐገራት ያደረጉትን ጉብኝት ዛሬ ያጠናቃቀቁት ሶል-ደቡብ ኮሪያ ላይ ነዉ።የአሜሪካ ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ፕሬዝዳንቱ ከየአስተናጋጆቻቸዉ ጋር ያደረጉት ዉይይትና ስምምነት የሐገራቸዉንና የየተጎብኚዎቹን ሐገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚረዳ ነበር።ይሁንና ጉብኝቱ፥ተቃዉሞና ቅሬታ አላጣዉምም።ነጋሽ መሐመድ የዜና መልዕክቶችን ተከታትሏል።


ባለፈዉ ሚዚያ የደቡብ ኮሪያዉ ፕሬዝዳት ሊ ምዩንግ ባክን ዋሽንግተን ላይ ሲቀበሏችዉ ከፈገግታ ጋር በኮሪያኛ ብለዉት ነበር።-ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ።
«እንኳን ደሕና መጡ» እንደማለት።

ደቡብ ኮሪያዊ እንግዳ-አቻቸዉ በምስጋና-አልተገቱም።
ሳቅ---«አመሰግናለሁ»
አባማ ዋይት ሐዉስ አስተናጋጅ በነበሩበት ጊዜ ደማቅ-ፈገግታ ሳቅ፥ ያጀበዉ ወዳጅነት ብሉ ሐዉስ (የደ.ኮሪያ ቤተ መንግሥት)-ሶል ላይ ትልቅ-እንግዳ ተስተናጋጅ ሲሆኑ ትናንት እጥፍ-ደምቆ አድጎ ነዉ-የጠበቃቸዉ።በደም-አጥንት የተማገረ-፥ በጠመንጃ ቃል የተለሰነዉ የደቡብ ኮሪያ-እና የዩናይትድ ስቴትስ ግንኙነቱ ለሁለቱ ሐገራት ያሁን መሪዎች መግባባት መሠረት ብቻ አይደለም።

ለመወያያ ርዕሳቸዉ ወጥ-ቀጥተኛ-አንድነትም ምክንያት ጭምር እንጂ።ሰሜን ኮሪያ እና የኑክሌር መርሐ-ግብሯ።ኦባማ።

«ሰሜን ኮሪያን በተመለከተ መንግሥቶቻችን ልዩ የሆነ የቅርብ ትብብርን አጠናክረዋል።ፕሬዝዳንት ሊ እና እኔ ወደፊት ሥለምንጓዝበት ሥልት ሙሉ በሙሉ ተስማምተናል።ለኑክሌሩ ዉዝግብ አጠቃላይ እና ተጨባጭ መፍትሔ ለማግኘት የስድስትዮሹ የድርድር ሒደት እንዲቀጥል ያለኝን ቁርጠኝነት መግለጥ እፈልጋለሁ።»

ሁለቱ ሐገሮች ከኦባማ-ሊ በፊትም እንደነበረዉ የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር መርሐ ግብር ሥለ ሚወገድበት ሥልት ተግባብተዋል።የዋሽንግተን-ሶል የጋራ አቋም-መግባባት ግን ለፒዮንግዮግ «ቅም» የሚል አይነት አልነበረም።ፒዮንግዮግ የኑክሌር መርሐ-ግብሯ ያስከተለዉን ዉዝግብ በድርድር ለማስወገድ ከተሰየመዉ የስድስትዮሽ ቡድን ራሷን ካገለለች ቆይታለች።

የኮሚንስታዊቷ ሐገር መሪ ኪም ጆንግ ኢል ባለፈዉ ወር እንዳሉት ሐገራቸዉ ወደ ድርድሩ መመለሱን አትጠላዉም።-ግን ሁለት ነገሮች ሲሟሉ ብቻ። ዩናይትድ ስቴትስ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ብቻ-ለብቻ ለመደራደር ከፈቀደች እና በቀጥታ ድርድሩ ሰሜን ኮሪያ ከረካች።ኦባማ-እንደ ቡሽ ሳይሆን እንደ ክሊንተን የብቻ-ለብቻ ድርድሩን ፈቀዱ-ትናንት።
«የዚሕ ጥረት አካል እንዲሆን ከሰሜን ኮሪያ ጋር ቀጥታ ድርድር ለማድረግ አምባሳደር ባዝዎርዝን ታሕሳስ ስምንት ወደ ሰሜን ኮሪያ እንልካቸዋለን።»

ይሕም ቃል-ተልዕኮ ሰሜን ኮሪያን የሚያረካ አልሆነም።የሐገሪቱ ገዢ የኮሚንስት ፓርቲ ልሳን ሮዶንግ ሲንሙን ዛሬ በርዕሠ-አንቀሱ «ጠብ-ጫሪ ሐይላት ያላቸዉ ዩናይትድ ስቴትስና ደቡብ ኮሪያ አሁንም ዲሞክራቲክ ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ኮሪያን ለመዉረር እየተዘጋጁ ነዉ።» በማለት ሁለቱን ሐገሮች አዉግዟል።

ኦባማ ከጎበኟችዉ ሐገራት ሁሉ ብዙ የቆዩ-መረር፥ ጠንከር ያለ ዉይይት-ድርድር ያደረጉትም ቻና እና ከቻይና መሪዎች ጋር ነበር።የመጨረሻ ዉጤቱ ብዙዎች እንዳሉት ቤጂንግ-ዋሽግተኖችን ያስደሰተ፥ የተቀረዉንም አብዛኛ አለም ያረካ ነበር።ታይዋንን ግን ቅር አሰኝቷል።ኦባማ ከእሁድ እስከ ሮብ-ከቻይና መሪዎች ጋር ሲወያዩ የታይዋንን ጉዳይ ብዙ አላነሱም።ለምን-ነዉ የታይፔዎች ቅሬታ።ቅሬታዉ የኦባማ መስተዳድርን «ጆሮ»ን አላጣም።እና ኦባማ ወደ ዋሽንግተን ሲያቀኑ የታይፔዎችን ቅሬታ ለማቀዝቀዝ የታይዋንና የዩናይትድ ስቴትስ የጋራ ትብብር የተሰኘዉ ድርጅት የበላይ ራይሞንድ ኤፍ በርግሐርድ እሁድ ወደ ታይፔ ለመሄድ ሻንጣቸዉን እየሽከፉ ነዉ።-ዛሬ።

US-Präsident Barack Obama mit chinesischem Präsident Hu Jintao
ኦባማ ከ ሁ ጋርምስል AP

dw, Agenturen
ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ