1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ግጭት እና ስጋት

ዓርብ፣ ሰኔ 7 2011

በቅርብ ጊዜያት ብቻ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዮንቨርስቲዎች በርካታ ግጭቶች ተካሂደዋል። በዚህም ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርታቸው ተፈናቅለዋል፣ ይባስ ብሎም የተጎዱ እና ህይወታቸዉን ያጡም አሉ። በዩንቨርስቲዎች የተከሰቱት ግጭቶች መንስኤ ብሔር ተኮር እንደሆኑ ይነገራል።

https://p.dw.com/p/3KS0F
Studenten Demo in Axum Universität
ምስል Daniel Taye

የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ግጭት እና ስጋት

   በኢትዮጵያ የአክሱም፣ የድሬደዋ እና  የደብረ ብርሃን ዮንቨርስቲዎች በቅርቡ ግጭት እና ተቃውሞዎች ተካሂደዋል። በአክሱም እና ደብረ ማርቆስ ዮንቨርስቲዎች እንደውም የሁለት ተማሪዎች  ህይወት ጠፍቷል። ተማሪዎቹ አሁንም ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ነው ሲሉ የትምህርት ቤቱ ተጠሪዎች ደግሞ ችግሮች በቁጥጥር ስር እንደሆኑ ይናገራሉ። አንዳንዶች እንደሚናገሩት ግጭቶቹ  ብሔር ተኮር ናቸዉ። ይህ አይነቱ ግጭት በተከሰተበት የድሬደዋ ዩንቨርስቲ ነገሮች በረድ ያሉ ይመስላል፤ ያለን አንድ ተማሪ ለግጭቱ መነሳት ምክንያት ነው ያለዉ « የአንድ ብሔር የበላይነት ነው።» የተፈነከቱ እና ሀብት ንብረታቸውን የተዘረፉም አሉ።  ምንም እንኳን በአሁን ሰዓት በድሬደዋ ዮንቨርስቲ መረጋጋት ቢታይም አሁንም ስጋት እንዳለ እና በርካታ ተማሪዎች ከግቢ ወጥተው ቤት ተከራይተዉ እንደሚኖሩ ወጣቱ ይናገራል። 

ሌላው ወጣት በደብረ ብርሃን የ4ኛ ዓመት ተማሪ ነበር። ትምህርቱን ለማጠናቀቅ የ 30 እና 40 ቀን እድሜ ሲቀረው ከሁለት ቀን በፊት ወደ መቀሌ እንደተመለሰ ይናገራል። በደብረ ብርሃን ዮንቨርስቲ ውስጥ ቀደም ብሎም በማንነት ላይ ያተኮሩ ግጭቶች የነበሩ ቢሆንም በአክሱም ዩንቨርስቲ ዉስጥ በታየዉ ግጭት የአንድ ተማሪ  ሕይወት ማለፉ ሁኔታዉን እንዳባባሰ ገልፆልናል።

በአንፃሩ ከአክሱም ዩንቨርስቲ ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ትውልድ ቦታው የተመለሰ ሌላው ተማሪ እንዲሁ ለህይወት አስጊ የሆነ ሁኔታ ስለገጠመኝ ወደ ትውልድ ሀገሬ ባህር ዳር ተመልሻለሁ ይላል። « ሰው በህይወት እስካለ ትምህርት የሚማርበት አጋጣሚ ይኖራል ሌላው እዛ መምማርበት ጊዜ ብሔርነት እና ዘረኝነትን ነው የተማርኩት»ወጣቱ  እንደሚለው ተማሪዎች በዋናው በር መውጣት አቅቷቸው ተደብቀው በአጥር ሾልከው ከግቢ ለመውጣት ተገደዋል። የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ኪሮስ ጉዑሽ በበኩላቸው ነገሮች መልሰው እንደተረጋጉ፣ ፈተና ያላቸውም ተማሪዎች በአግባቡ ፈተናቸውን እየወሰዱ እንደሆነ ነው የገለፁልን። « ውይይትቶች አካሂደናል።ተማሪዎችንም ለማረጋጋት ስራ ተሰርቷል። ተጠርጥረው እስር ላይ ያሉ ተማሪዎች ወይም ደግሞ በነበረው አለመረጋጋት ህክምና ሲከታተሉ ከነበሩ ተማሪዎች በቀር መደበኛ በሚባል መልኩ ተማሪዎች ፈተናቸውን እየተከታተሉ ነው»

Äthiopien Axum-Universität in der Region Tigray
ምስል DW/M. Hailesilassie


ይሁን እንጂ በተለያዩ ዮንቨርስቲዎች ያለው ግጭት በርካታ ልጆቻቸውን እንዲማሩ የላኩ ወላጆችን ወይም የቤተሰብ አባሎችን ስጋት ላይ ጥሏል። « ዋስትና የሌለው ነገር ነው። ፌደራል እና መከላክያ ለተወሰነ ቀን አብሮ ሊገኝ ይችላል። ከዛ በኋላ ላለው ነገር ግን ምንም ዋስትና የለም።» ሌላው የ12ኛ ክፍል ተማሪ  ልጅ ያላቸው ወላጅ ናቸው። ስጋታቸው ካልፈለጉት ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ ገፋፍቷቸዋል። « ልጄ ወደ ሌላ ክልሎች እንዲሄድ ፍቃደኛ አይደለሁም።»

ዶክተር የራስ ወርቅ አድማሴ በአሁን ሰዓት ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ በሚባል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ስራ አስፈፃሚ ዳሬክተር ናቸው። ለረዥም ዓመታት በአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ የሶይሶሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆነው አገልግለዋል።  በተለያዩ ዮንቨርስቲዎች በሚገኙ ተማሪዎች መካከል የሚስተዋለዉ በማንነት ላይ ያተኮረ ግጭት የተማሪዎቹ ችግር ብቻ ሳይሆን በኅብረተሰቡም ችግር ነዉ ይላሉ። «መሰዳደብ ፣መጋጨት ፣ መጋደል ባለበት ሀገር ዩንቨርስቲ አካባቢ ያሉ ወጣቶች በዚህ አይነት ስሜት ተነሳስተው ለመጋጨት ከማንም የበለጠ ዝግጁ ናቸው። ሌላው ደግሞ ዮንቨርስቲ በአንድ ጠባብ ስፍራ በሺዎች የሚቆጠሩ ከልዩ ልዩ ብሔረሰቦች የሚገኙበት ቦታ ነው። ስለዚህ በብዙ ጉዳዮች ርዕስ በዕርስ ይገናኛሉ። » የማህበራዊ ኑሮ ባለሙያው ዶክተር የራስ ወርቅ፤ ለረዥም ዓመታት በቅርበት ከዮንቨርስቲ ተማሪዎች ጋር መስራታቸው ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም የነበሩ የተለያዩ የተማሪዎች ተቃውሞዎችንም ለመታዘብ ችለዋል። 
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዩንቨርስቲ ተማሪዎች መካከል የታየዉን ግጭትና ይህም የፈጠረውን ስጋት የቃኘው የወጣቶች ዓለም ዝግጅትን በድምፅ  መከታተል ይችላሉ።

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ