1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንታዊ እጩዎች የቲቪ ክርክር

ማክሰኞ፣ መስከረም 17 2009

በዩኤስ አሜሪካ የፊታችን እጎአ ኅዳር ስምንት ለሚደረገው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የሚወዳደሩት የዴሞክራት እና የሬፓብሊካን ፓርቲዎች እጩዎች ሂለሪ ክሊንተን እና ዶናልድ ትራምፕ ትናንት የመጀመሪያውን የቴሌቪዥን ክርክራቸውን አካሄዱ።

https://p.dw.com/p/2Qf7y
USA Wahlkampf TV Duell
ምስል Getty Images/DW Montage

ለ45ኛ የዩኤስ ፕሬዚደንትነት ስልጣን የሚፎካከሩት እጩዎች በኒው ዮርክ የሆፍስትራት ዩኒቨርሲቲ ባካሄዱት የፊት ለፊት ውይይት ስለ ቀረጥ፣ የሀገር ውስጥ ፀጥታ፣ ስለ ፀረ ሽብርተኝነቱ ትግል፣ ስለውጭ ፖለቲካ ፖሊሲዎቻቸው ተራክረዋል። ክሊንተን ለመካከለኛው መደብ ለሚገኘው የኅብረተሰቡ ክፍል ቀረጥ የመቀነስ እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል።
« እኔ የማምነው የመካከለኛውን መደብ ለማጠናከር እስከሰራን ድረስ፣ ከዚሁ ጥረት የሚገኘውን ገንዘብ ለናንተ ሊጠቅም በሚችል ፣ ብሎም፣ ለትምህርታችሁ፣ ለሙያ ስልጠናችሁ እና ለወደፊት እድላችሁ  ልናውለው እንችላለን። ይህን ስናደርግ ልንሻሻል እና ልናድግ እንችላለን። ይህ ዓይነት ኤኮኖሚ ነው ልገነባ የምፈልገው።። »
በአንጻራቸው ሬፓብሊካኑ ተፎካካሪያቸው ዶናልድ ትራምፕ ለትልልቆቹ ባለተቋማት ቀረጥ በመቀነሱ፣ የሚሰራባቸውን የንግድ ስምምነቶችን እንደገና በመከለሱ ላይ ማተኮራቸውን በማጉላት የክሊንተንን ሀሳብ ተቃውመዋል። 
« በኔ እቅድ፣ ለኩባንያዎች፣  ለአነስተኞቹ እና ለከፍተኛ የንግድ ተቋማት ግዙፍ የቀረጥ ቅናሽ አደርጋለሁ። ከ35 ከመቶ ወደ 15 ከመቶ፤ ይህ  ከሮናልድ ሬገን ዘመነ ስልጣን ወዲህ አይተነው የማናውቅ ብዙ የስራ ቦታ የሚፈጥር ይሆናል። ይህ ለማየት የሚያስደስት ነገር ነው የሚሆነው። ኩባንያዎች ይመጣሉ፣ ይስፋፋሉ፣ አዳዲስ ኩባንያዎች ይፈጠራሉ። »
ይህንኑ የእጩዎች ክርክር ወደ 100 ሚልዮን የሚጠጉ አሜሪካውያን ተከታትለውታል። ከክርክሩ በኋላ የ«ሲ ኤን ኤን » ቲቪ ባወጣው የአስተያየት መመዘኛ መዘርዝር መሠረት፣ በክርክሩ ማን አሸናፊ ነበር ተብለው ከተጠየቁት መካከል 67% ክሊንተን ሲሉ፣ 27% ትራምፕ ሲሉ መልሰዋል። በተፎካካሪዎቹ መካከል ቀጣዩ የቲቪ ክርክር እጎአ የፊታችን ጥቅምት ዘጠኝ፣ 2016 ዓም ይደረጋል። የዋሽንግተን ዲሲውን ዘጋቢያችንን መክብበ ሸዋን ስለ ትናንቱ ክርክሩ ይዘት እና በክርክሩ ላይ ስለተሰጡ አስተያየቶች በስልክ አነጋግረነዋል ።

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ