የዩኤስ አብራሪ የለሽ አይሮፕላን ጥቃት
ሐሙስ፣ ግንቦት 30 2004
እአአ 2012 ዓም ከገባ ወዲህ እንኳን በፓኪስታንና አፍጋኒስታን ድንበር አካባቢ በዚሁ የጦር አይሮፕላን ቢያንስ ሀያ ጊዜ ጥቃት ተጥሎዋል። በትናንቱ ዕለትም አሜሪካውያኑ የአል ቓይዳ አመራር ሁለተኛ ቦታ ላይ የሚገኙትን አቡ ጃሃጃ ኣል ሊቢንን መግደሉ ተሳክቶላቸዋል። ዩኤስ አሜሪካ ሊቢን ይዞ ለማስረክባት አንድ ሚልዮን ዶላር ለመክፈል ዝግጁ ነበረች። ፓኪስታን ይህንኑ አሸባሪዎች የተባሉትን ብቻ ሳይሆን የሲቭል ሕዝብን ሕይወት ጭምር ያጠፋውን የአሜሪካ ርምጃ ሕገ ወጥ አድርጋ ብትመለከተውም፡ የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ዛንድራ ፔተርስማን እንደዘገበችው፡ ዩኤስ አሜሪካ ይህንን ውጤታማ የሆነውን የትግል ሥልቷን ለመለወጥ ፍላጎት የላትም።
አብራሪ በሌለው የጦር አይሮፕላን የሚሰነዘረው የዩኤስ አሜሪካ ጥቃት በፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ የሥልጣን ዘመን በጉልህ ጨምሮዋል። ከአየር የሚሰነዘረውን የግድያ ጥቃት በተመለከተ የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጡት አሜሪካዊው ፕሬዚደንት ናቸው።
« ይህ አሜሪካውያንን፡ አሜሪካውያን ተቋማትንና የጦር ሰፈሮችን፡ ወዘተ፡ ለመጉዳት የሚሞክሩ አሸባሪዎች ናቸው ተብለው ስማቸው በዝርዝራችን ውስጥ በተጠቀሱ የታወቁ ሰዎች አንጻር ሆን ተብሎ ጥቃት ለመሰንዘር የሚደረግ ጥረት ነው። ስለዚህ ብዙዎቹ እነዚህ ጥቃቶች የተጣሉት የአል ቓይዳ ተዋጊዎች ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በሚንቀሳቀሱባቸው እና በቀላሉ ሊደረስባቸው በማይችሉት በፓኪስታን እና በአፍጋኒስታን ድንበር መካከል በሚገኙት አካባቢዎች ነው። እነዚህን ግለሰቦች በሌላ መንገድ እንያዝ ካልን ግን ይህ ከኛ አሁን ከምንጠቀምበት የበለጠ ጠንካራ የጦር ርምጃ መውሰድን ይጠይቅብናል። »
የፓኪስታን መንግሥት በማይቆጣጠራቸው የሀገሩ ጎሣዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ባለፉት ሁለት ሣምንታት ብቻ በአብራሪ የለሹ የጦር አይሮፕላን ስምንት የሌሊት ጥቃቶች፡ ካለፉት አምስት ወራት ወዲህ ደግሞ ሀያ ጥቃቶጭ ተጥለዋል። ባንድ በኩል ይኸው ዘመናዊው የጦር አይሮፕላን ሮኬቶቹን የሚጥለው በቀላሉ ሊደረስበት በማይችለው በፓኪስታን እና በአፍጋኒስታን ድንበር እንደመሆኑ መጠን፡ በሌላ ወገን ደግሞ፡ አክራሪ ሙሥሊሞች፡ የስለላ ድርጅቶች እና የፓኪስታን ጦር ኃይል ጋዜጠኞች ወዳካባቢው በመሄድ ሁኔታው እንዲዳይዘግቡ ስለሚያከላክሉ የሚያደርሰው ጉዳት በትክክል ይህ ነው ብሎ ለመናገር ይከብዳል። በዚህም የተነሳ የጥቃቱን በተመለከተ መረጃ የሚገኘው ከስለላ ድርጅት ጋ ግንኙነት ካላቸው ምንጮች፡ ማንነታቸው ካልታወቁ የመንግሥት ምንጮች እና የጎሣ አባላት፣ መረጃው ሀቅ ወይም ፕሮፓጋንዳ ይሁን አይሁን መለየቱ ያዳግታል። በዚያም ሆነ በዚህ ግን የፓኪስታን ጦር ኃይል ይህንኑ የአብራሪ የለሽ የጦር አይሮፕላን ጥቃት እንዲያበቃ ከፍተኛ ግፊት አርፎበታል። ጥቃቱ ከሀገሪቱ ህብረተሰብ ተቃውሞ ተፈራረቆበታል።
ይኸው አሸባሪ የተባሉትን ብቻ ሳይሆን የሲቭል ሕዝብን ሕይወት ጭምር እያጠፋ ያለውን የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነትን ይበልጡን እያሻከረው የተገኘው የአብራሪ የለሽ የጦር አይሮፕላን ጥቃት ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጥስ መሆኑን የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሂና ራባኒ ገልጸዋል።
« በኛ አመለካከት በአብራሪ የለሽ የጦር አይሮፕላን የሚጣል ጥቃት በጠቅላላ ሕገ ወጥ ነው። ዓለም አቀፍ ሕግን ይጥሳል። ከሁሉም በላይ ግን ይህን አካባቢ ከአክራሪነትና ከሽብርተኝነት ነፃ ለማድረግ የተጀመረውን ትግል ይጎዳል። በጥቃቱ ዒላማ የሆነ አንድ ተጠርጣሪ ሽብርተኛ ቢገደልም፡ ርምጃው ሌሎች አምስት ወይም አሥር ተከታዮችን በመፍጠር አክራሪነት ይበልጥ ያባባሳል። »
ዛንድራ ፔተርስማን
አርያም ተክሌ
ሸዋዬ ለገሰ