1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩክሬንና የሩሲያ መሪዎች ዉይይት

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 20 2006

የምሥራቃዊ ዩክሬን አማፂያን ከሐገሪቱ መንግሥት ጦር ጋር መዋጋት ከጀመሩበት ካለፈዉ ሚያዚያ ወዲሕ ከሁለት ሺሕ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል።ጦርነቱ አማፂያኑን ትረዳለች በምትባለዉ ሩሲያና የኪየቭን መንግሥት በሚደግፉት ምዕራባዉያን መካካል ከማዕቀብ-ቅጣትና አፀፋ ቅጣት ያደረሰ ጠብ ቀስቅሷል።

https://p.dw.com/p/1D1W9
ምስል Reuters/Sergei Bondarenko/Kazakh Presidential Office

ሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንና የዩክሬኑ አቻቸዉ ፔትሮ ፖሮሼንኮ ሁለቱን ሐገራት ዉዝግብ በሚያስወግዱበት ሐሳብ ላይ ዛሬ ሚኒስክ-ቤሎሩስ ዉስጥ ተነጋግረዋል።በሚንስኩ ጉባኤ ከሁለቱ መሪዎች ሌላ የአስተናግጅዋ የቤሎ ሩስ እና የካዛክስታን መሪዎች እንዲሁም የአዉሮጳ ሕብረት ተወካዮች ተካፍለዉ ነበር።በሩሲያ ይደገፋሉ የሚባሉት የዩክሬን አማፂያን ከሐገሪቱ መንግሥት ጦር ጋር ዉጊያ ከገጠሙ ወዲሕ የሩሲያና የዩክሬን መሪዎች ፊት ለፊት ሲገናኙ የዛሬዉ ሁለተኛቸዉ ነዉ።ከጉባኤዉ በፊት ግን ዩክሬን ከጦር ግንባር «የተማረኩ» ያለቻቸዉን የሩሲያ ወታደሮችን የሚያሳይ ቪዲዮ ማሠራጨቷ የዉይይቱን ይዘት፤ ሒደትና ተስፋ አጨፍግጎታል።ነጋሽ መሐመድ ዝርዝር ዘገባ አለዉ።

የቤሎ ሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሎካሼንኮ አስተናጋጅ ናቸዉ፤የካዛክስታኑ ፕሬዝዳንት ኑርሱልጣን ናዛርባዬቭ ተጋባዥ እንግዳ።ሁለቱ መሪዎች የሩሲያ አቻቸዉን ጨምረዉ ሐገሮቻቸዉን በ-ከቀረጥ ነፃ የንግድ ቀጠና ያስተሳሰሩ ናቸዉ።ዩክሬን እንደ ሰወስቱ ሐገራት ሁሉ የቀድሞዋ ሶቬት ሕብረት ሪፕብሊክ ብትሆንም-ሐገራቸዉን ከምሥራቁ ይልቅ ከምዕራቡ ጎራ ለመቀየጥ የሚጣጣሩት ፕሬዝዳንት ፖሮሼንኮ በጉባኤዉ «የብቸኝነት» ስሜታቸዉን ያቃለላቸዉ በአዉሮጳ ሕብረት መልዕክተኞች መታጀባቸዉ ነዉ።

የአዉሮጳ ሕብረትን የንግድ እና የሐይል ኮሚሽነሮች አስከትለዉ በጉባኤዉ የተሳተፉት የሕብረቱ የዉጪ ግንኙነት ሐላፊ ወይዘሮ ካትሪን አሽተንም በጉባኤዉ የመካፈላቸዉ ምክንያት «የዩክሬንን ሕዝብ በመደገፍ» በማለት ሕብረታቸዉ ለማን እንደወገነ በግልፅ ተናግረዋል።

ያም ሆኖ ከጉባኤተኞቹ የሐይል አሠላለፍ ይልቅ ትናንት ከወደ ኪየቭ የተሰራጨዉ ዜና ወትሮም የመነመነዉን በጎ ተስፋ-ይበልጥ አስልሎታል።የዩክሬን መንግሥት ከአማፂያን ወግነዉ ሲዋጉ የተማረኩ ያላቸዉን አስር የሩሲያ ወታደሮችን ምሥል፤የወታደሮቹን የጦር ክፍል፤ ማንነትና የቃል ማረጋገጪያ የሚያሳይ ቪዲዮ አሰራጭቷል።

Gipfeltreffen in Minsk Putin Lukaschenko und Poroschenko 26.08.2014
ምስል Kirill Kudryavtsev/AFP/Getty Images

በጀርመን የዩክሬን መንግሥት ተወካይ ኻይምዬኔትስ ቫስዬል እንደሚሉት የመንግሥታቸዉ ጦር ወታደሮቹን የማረከዉ ወታደሮቹ የነበሩባቸዉን የሩሲያ ታንኮች አዉድሞ ነዉ።ይሕ ደግሞ ሩሲያ ከጠብ ጫሪነትም አልፋ በጦርነቱ በቀጥታ መሳተፏን የሚያረጋግጥ ነዉ-ቫስዬል እንደሚያምኑት።

«የሩሲያ ጦር ባልደረቦች የሆኑ ወታደሮች ታሥረዋል።ምሥሉ ተሠራችቷል።ድርጊቱ በርግጥ በጣም ያሳሰበን።ይሕ ጠብ አጫሪነት ብቻ ሳይሆን (ሩሲያ) ጦርነት መክፍቷን፤ በጦርነቱ መቀጠሏንም የሚያረጋግጥ ነዉ።»

የሩሲያ ዉንጀላዉን አጣጥላ ነቅፋዋለች።የሐገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር እንደሚለዉ ወታደሮቹ የተያዙት ዩክሬን ድንበር አካባቢ ወደሚገኝ የሩሲያ ግዛት ለሌላ ተልዕኮ ሲጓዙ አቅጣጫ ስተዉ ዩክሬን ግዛት በመግባታቸዉ ነዉ።ለዉጊያ የዘመቱ ቢሆኑ ኖሮ፤ ሚኒስቴሩ መግለጫ እንደሚለዉ፤ በዩክሩን ጦር ላይ ሳይተኩሱ እጃቸዉን ባልሰጡ ነበር።

ፑቲንና ፖሮሼንኮ ለመነጋገር ሰዓታት ሲቀራቸዉ ዛሬ ደግሞ የኪየቭ መንግሥት ዩክሬንን የአየር ክልል ጥሶ የገባ ያለዉ አንድ የሩሲያ የጦር ሔሊኮብተር በከፈተዉ ተኩስ ቢያንስ አራት የዩክሬን ጠረፍ ጠባቂ ወታደሮችን ገድሏል።

የሁለቱ መሪዎች ዉይይትና መገለጫ ግን የወቀሳ፤ ዉንጀላ፤ እሰጥ አገባዉን ያክል መራር አልነበረም።እንደ ወዳጅ ተጨባብጠዋል።ፕሬዝዳንት ፑቲን ለምሥራቃዊ ዩክሬን ቀዉስ አብነቱ በኪየቭና በአማፂያኑ መካከል የሚደረግ ድርድር እንጂ የጦር ጥቃትና አፀፋ ጥቃት መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንት ፖሮሼንኮም ምሥራቃዊ ዩክሬንን የሚያብጠዉን ጦርነት በሰላማዊ መንግድ ለማስቆም መንግሥታቸዉ አብክሮ እንደሚጥር አስታዉቀዋል።በጀርመን የዩክሬን ተወካይም ቀዉሱን ለማስወገድ በተለይ ከሩሲያ ጋር ከድርድር የተሻለ አማራጭ የለም ባይ ናቸዉ።

Gipfeltreffen in Minsk Putin Ashton Lukaschenko und Poroschenko 26.08.2014
ምስል Reuters

«በምንም መንገድ ቢሆን ድርድሩን መቀጠሉ ያዋጣል።በኛ በኩል፤ፕሬዝዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ ያሳዩት የተለያዩ ችግሮችን ለማስወገድ ከሩሲያ ጋር በሚደረገዉ ድርድር ለመቀጠል ዝግጁ መሆናችንን ነዉ።ድርድሩን በመቀጠል ሩሲያ ወደ ግጭቱ አካባቢ ወታደራዊ ቁሳቁስ፤የጦር መሳሪያ እና ተዋጊ ሐይል ማዝመቷን እንድታቆም ማድረግ ነዉ።ለኛ ዋናዉ ነጥብ ይሕ ነዉ።»ፕሬዝዳንት ፖሮሼንኮም የመንግሥታቸዉን አቋም ወደ ሚኒስክ ከመጓዟቸዉ በፊት ምክር ቤቱን ሲበቱ አስታዉቀዉ ነበር።

«እኔ እንደሚታየኝ ዶንባስ (ምሥራቅ ዩክሬን) እና ፓርላማ ዉስጥ የሚገኙ የዴሞክራሲያዊዉን ሐይላት የተሐድሶ ድል ብጥብቅ የተገናኙ ናቸዉ።አቸኳይ ምርጫዉም የሠላም እቅዴ አካል ነዉ።ቁልፍ ነጥቡ ከዶንባስክ ጋር የሚደረግ ድርድር ነዉ።»

የምሥራቃዊ ዩክሬን አማፂያን ከሐገሪቱ መንግሥት ጦር ጋር መዋጋት ከጀመሩበት ካለፈዉ ሚያዚያ ወዲሕ ከሁለት ሺሕ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል።ጦርነቱ አማፂያኑን ትረዳለች በምትባለዉ ሩሲያና የኪየቭን መንግሥት በሚደግፉት ምዕራባዉያን መካካል ከማዕቀብ-ቅጣትና አፀፋ ቅጣት ያደረሰ ጠብ ቀስቅሷል።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለስ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ