1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩክሬይን ጠ/ሚ የዋሽንግተን ጉብኝት

ሐሙስ፣ መጋቢት 4 2006

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ የዩክሬይንን የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር አርሴኒ ያዜንዩክ ትናንት በዋይት ሀውስ ቤተ መንግሥት ተቀብለው አነጋገሩ። ግዛቷ ክሪሚያ በሩስያ የተያዘባትን ዩክሬይን ዩኤስ አሜሪካ እንደምትደግፍ ኦባማ ለያዜንዩክ አረጋገጠዋል።

https://p.dw.com/p/1BPJs
Obama trifft Jazenjuk in Washington
ምስል picture-alliance/dpa

ሩስያ ዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ በክሪሚያ አስፍራዋለች ያሉትን ጦር እንደታስወጣ ማስጠንቀቂያ አቅርበዋል። ይህን ካላደረገች ግን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአንፃሯ ጠንካራ ርምጃ እንደሚወስድ ዝተዋል። ክሪሚያ ከሩስያ ጋ ለመቀላቀል በማሰብ የፊታችን እሁድ የምታካሂደውን ውሳኔ ሕዝብም ኦባማ በተጨማሪ አውግዘዋል።

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ የዩክሬይንን የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር አርሴኒይ ያዜንዩክ በተቀበሉበት ድርጊት ሀገራቸው ከአዲሱ የዩክሬይን አመራር ጎን መቆሟን ማሳየታቸውን በዋሽንግተን የሚገኘው «አትላንቲክ ካውንስል» የተባለው የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ያን ብሬዤዚንኪ አስረድተዋል።

« እንደሚመስለኝ፣ ጉብኝቱ ዓቢይ ትርጉም የሚሰጠው ነው። ምክንያቱም፣ ዩኤስ አሜሪካ የዩክሬይንን፣ የክሬሚያን ግዛት ጭምር ነፃነት እና የግዛት ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባት መልዕክት ያስተላለፈችበት ነውና። »

Ukraine Militär Belbek
ምስል AFP/Getty Images

ዩኤስ አሜሪካ ለዩክሬይን ጦር ማጠናከሪያ የሚበጁ የፀጥታ ማስጠበቂያ ቴክኒካዊ ቁሳቁሶች ጭምር የተካተቱበት፣ እንዲሁም፣ ግዙፍ የኤኮኖሚ ርዳታ ልትሰጥ እንደምትችል ለአውሮጳ እና ለሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ኪዳን፣ ኔቶ ተጠያቂ የነበሩት የቀድሞው የዩኤስ ተጠባባቂ ምክትል መከላከያ ሚንስትር ያን ብሬዤዚንኪ አመልክቶዋል።

« ርዳታው የዩክሬይንን ጦር ማጠናከር፣ ማደስ ል እና ዘመናይ ማድረግ የሚያስችል ሊሆን ይችላል። ይህም ዩክሬይን ከዩኤስ እና ከምዕራቡ ጋ ግንኙነቷን ለማጠናከር ያስቀመጠችውን የረጅም ጊዜ ራዕይዋን ዕውን ሊያደርግላት ያስችላል። ከዚህ ሌላም ርዳታው የዩክሬይንን መከላከያ አቅም በሩስያ ጦር ኃይላት አንፃር ብቁ እና ጠንካራ ሊያደርገው የሚያስችለው፣ ለምሳሌ፣ ጦር መሳሪያም ሊሆን ይችላል። »

ዩክሬይን ከዩኤስ አሜሪካ ጠንካራ ድጋፍ ማግኘቷ ብቻውን ግን አሁን ከሩስያ ጋ የተፈጠረውን ውዝግብ ማብቃቱን ከአሜሪካውያኑ መከላከያ ሚንስቴር ጋ ቅርበት አለው የሚባለው «ራንድ» የተሰኘው የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ ኬይት ክሬን ይጠራጠሩታል። አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር በሀገራቸው የተስፋፋውን ሙስና ማብቃት እና ፖለቲካዊ ተሀድሶ ማነቃቃት ይኖርባቸዋል።

« ዩክሬይን ቃል እንደገባችው በፀደይ ምርጫ ማካሄድ ይኖርባታል። እንደሚመስለኝ፣ ይህ፣ አዲስ የሚመረጠው መንግሥት የዩክሬይንን ሕግ እና ሕገ መንግሥት የተከተለ መሆኑን ሩስያውያኑን ማሳመኑን ቀላል ያደርገዋል። »

Angela Merkel Regierungserklärung zur Ukraine 13.03.2014
ምስል Odd Andersen/AFP/Getty Images

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ዛሬ በምክር ቤት ባሰሙት ንግግር በዩክሬይን በቀጠለው ውዝግብ ላይ የሩስያን ሚና በጥብቅ አውግዘዋል።

» ሩስያ በዩክሬይን የፈፀመችው መሠረታዊ ዓለም አቀፍ መመሪያዎችን በግልጽ የሚጥስ ነው። ሌሎች ዓለም አቀፍ ሕግ ጣሱ ቢባል እንኳን፣ ይህ የሷን ርምጃ ትክክለኛ አያደርግላትም። »

ተቀናቃኞቹ ውዝግቡን በውይይት ያበቁ ዘንድ ጀርመን አንድ አገናኝ ቡድን እንዲቋቋም ሀሳብ አቅርባለች። የቡድኑ ዓላማ፣ ይላሉ ሜርክል፣

« የአገናኚው ቡድን ዓላማ በዓለም አቀፍ ሸምጋይነት በኺየቭ እና በሞስኮ መካከል አን የውይይት መስመር መክፈት ነው። በንዲህ ዓይነት ውይይት ላይ አሁን ወደተፈጠረው ውዝግብ ያመሩ ወይም ወደፊት ሊያባብሱ የሚችሉ ጉዳዮች በጠቅላላ መቅረብ ይኖርባቸዋል። »

ሩስያ ግን ዓለም አቀፍ ሕግ ጥሷል በሚል እውቅና ካልሰጠችው የዩክሬን አመራር ጋ እስካሁን ለመወያየት ፈቃደኛ አይደለችም። እና የአውሮጳ ህብረት እና ሌሎች ምዕራባውያት ሀገራት ሩስያ የአገናኚ ቡድኑ ሀሳብ ለመቀበል ዝግጁ ካልሆነች በአንፃሯ ሊጎዱዋት የሚችሉ ፖለቲካዊ እና የባንክ ንብረት እንቅስቃሴ እና የጉዞ እገዳ የመሳሰሉ ኤኮኖሚያዊ የማዕቀብ ርምጃዎች ለመጣል መዘጋጀታቸውን ሜርክል ቢያመለክቱም፣ በሩስያ ላይ ወታደራዊ ርምጃ እንደማይወሰድ ግልጽ አድርገዋል።

አንትየ ፓስንሀይም/ አርያም ተክሌ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ