1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩጋንዳ አማጽያን መሪ ታሪካዊ የሰላም ውል ይፈርማሉ መባሉ፧

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 2 2000

The Lord’s Resistence Army የተሰኘው የዩጋንዳ አማጺ ኃይል መሪ Joseph Kony ፧ በሱዳንና በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ድንበር፧ ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ በምትገኘው ሪ-ክዋንግባ በተሰኘችው ከተማቸው፧ ዛሬ፧ የሰላም ውል ይፈርማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/E0Z1
ተገደው ታጣቂዎች ከሆኑት ትንንሽ ልጆች አንዱ፧
ተገደው ታጣቂዎች ከሆኑት ትንንሽ ልጆች አንዱ፧ምስል AP
ከ 5 ቀን በኋላ ደግሞ የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ፧ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዳቸው እንደማይቀር ነው የሚነገረው። የሁለቱ ሰዎች የሰላም ውል መፈረም፧ አፍሪቃ ውስጥ ረዘም ያለ ጊዜ መውሰዱ የሚነገርለትን አሰቃቂ የእርስ በርስ ጦርነት እንዲያከትም ያደርጋል የሚል ተስፋ አሳድሯል።
ጆሰፍ ኮኒ፧ በጠየቁት መሠረት፧ በዛሬው ዕለት፧ ሸምጋዮች በሄሌኮፕተር ከወሰዱላቸው የቅርብ ዘመዶቻቸው፧ ከእህታቸው፧ አጎታቸውና ከቀድሞ ሚስታቸው ጋር ተገናኝተዋል። የሰላም ውል ለሚፈረምበት ሥነ ሥርዓት፧ ጫካ ተመንጥሮ በተተከለ ድንኳን ዙሪያ አረንጓዴ መለዮ የለበሱና አውቶማቲክ ካላሽኒኮቭ ደግነው በተጠንቀቅ ላይ ያሉ የ LRA አባላት ታይተዋል።
የዩጋንዳ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ሩሃካና ሩጉንዳ የሚገኙበትን የሰላም ውል የመፈረም ሥርዓት በሊቀመንበርነት ሊመሩ በዚያ የሚገኙት ሸምጋይ፧ የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት Riek Machar ናቸው።
የመጨረሻው የሰላም ውል፧ ሳይፈረም ሲሸጋሸግ የቆየ ሲሆን፧ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ጉዳይ መርማሪ ፍርድ ቤት፧ በጠቅላላ ከ ጆሰፍ ኮኒ ጋር፧ ሁለት ምክትሎቻቸው፧ በጠቅላላ ከኮኒ ጋር አምስት የደፈጣ ተዋጊው ድርጅት መሪዎች፧ እንዲያዙ፧ እ ጎ አ በ 2005 ዓ ም፧ ማዘዣ ጥሪ ማቅረቡም ሁኔታውን አወሳስቦታል ነው የሚባለው። ፍርድ ቤቱ፧ LRA ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ልጆችን፧ አስገድዶ ለውጊያ በመመልመል፧ እንዲሁም ሲቭሎችን አስገድዶ በመድፈርና በግድያ ወንጀለኛ ነው ሲል ነው የከሰሰው። ይህ ጉዳይ እልባት አግኝቶ እንደሁ፧ በተጠቀሰው አካባቢ ተሠማርታ የምትገኘው ጀርመናዊ ጋዜጠኛ Mareike Schomerus ተጠይቃ ስትመልስ፧......
«መፍትኄ ተገኝቶለታል ማለት እንኳ አዳጋች ነው። ሙከራ ነው፧ የመጨረሻው የሰላም ስምምነት፧ ዩጋንዳ ውስጥ ልዩ ፍርድ ቤት ተቋቋሞ፧ የጦር ወንጀል ነክ ጉዳዮችን ይመረምራል ነው የሚለው። በተለይ፧ LRA እና የዩጋንዳ መንግሥት የፈጸሟቸውን በደሎች ነው፧ ፍርድ ቤቱ የሚመለከተው። ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መርማሪ ፍርድ ቤት፧ ያደረገው ቢኖር፧ የ LRA መሪዎች ብቻ እንዲያዙ ማዘዣ ደንብ ማውጣት ሲሆን፧ ይህም ነቀፌታ ካስከተሉት ጉዳዮች መካከል አንዱ ሆኖ ተገኝቷል።«
በደን ኻኽ፧ ኔደርላንድ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መርማሪ ፍርድ ቤት፧ የተጠቀሱትን የ LRA አመራር አባላት ይክሰስ እንጂ፧ ከተከሳሹ መካከል ሁለቱ ጫካ ውስጥ መገደላቸው ታውቋል። የደፈጣ ተዋጊውን ድርጅት ምክትል አዛዥ፧ Vincent Otti ን ራሳቸው ጆሰፍ ኮኒ ናቸው ባለፈው መስከረም 21 ቀን 2000 ዓ ም የገደሏቸው። ጋዜጠኛ ማራይከ፧ የ LRA ታጣቂዎች፧ ስለዛሬው ዕለትና ስለ ምክትል አዛዣቸው ቪንሰንት ኦቲ መገደልም ምን እንደሚሰማቸው ጠይቃ እንደሁ ራሷ ተጠይቃ፧ እንዲህ የሚል ምላሽ ነው የሰጠች።
«እነርሱም፧ ከዚህ ዕለት በመደረሱ በጣም ነው ደስ ያላቸው። ከእነርሱ ጋር ያሉት ፕሬዚዳንትም እንዲሁ። ስለተገደሉት ምክትል መሪ ቪንሰንት ኦቲ፧ ለመናገር አይዳዱም፧ እንደሚመስለኝ፧ የዛሬዋ ዕለት በልዩ ሁኔታ እንድትታይ ነው የሚፈልጉት። ሁሉም የዛሬዋን ዕለት ታላቅነት በልዩ ስሜት በማሰብ ረገድ እንዲጋራ ይሻሉ። ይህችን ቀን ሲጠባባቁ ረጅም ጊዜ ነው የወሰደባቸው።«
በሰሜናዊው ዩጋንዳ ከ ኻያ ዓመት በላይ ሲካሄድ በቆየው የእርስ በርስ ጦርነት፧ 100,000 ያህል ሰዎች መገደላቸውና ከ 1.5 ሚልዮን በላይ ህዝብ መፈናቀሉ ታውቋል።