1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩጋንዳ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የመጨረሻ ቅስቀሳ

ረቡዕ፣ የካቲት 9 2008

ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ለአምስተኛ የስልጣን ዘመን በእጩነት የቀረቡበት የዩጋንዳ ምርጫ ነገ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለታል። በምርጫው ስምንት እጩ ተወዳዳሪዎች ቀርበዋል። የአገሪቱ ፖሊስ በመጨረሻው የምረጡኝ ዘመቻ ቀን የዩዌሪ ሙሴቬኒ ጠንካራ ተፎካካሪ ናቸው ከተባሉት ኪዛ ቤሲጄ ደጋፊዎች ጋር ተጋጭቷል።

https://p.dw.com/p/1HwxK
Uganda Präsidentschaftswahlen Kandidaten Mbabazi Besigye Museveni
ምስል DW/Reuters/picture-alliance/dpa

[No title]

ገዢው 'ናሽናል ሬዚዝተንስ ሙቭመንት' ወይም «ብሄራዊ የመከላከያ ንቅናቄ» ባካሄደው የምረጡኝ ዘመቻ ሁሉ የዩጋንዳ ስመ-ጥር ድምጻውያንን ቀጥሮ ህዝቡን ሲያዝናና ቆይቷል።ዩዌሪ ሙሴቬኒ በመጨረሻው የምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ለንግግር ወደ መድረክ ከማምራታቸው በፊት ድምጻውያኑ በሚያቀርቡት ሙዚቃ ህዝቡ እየተዝናና እየደነሰም ነበር።
ምርጫውን ያሸንፋሉ የሚል ቅድሚያ ግምት የተሰጣቸው ዩዌሪ ሙሴቬኒ ቀደም ብለው በጸሃይ ብርሃን የሚሰራ አውቶቡስ መርቀው ተቀባይነታቸውን ከፍ ለማድረግ ጥረዋል። አውቶቡሱ ከውጭ አገራት በገቡ ጥቂት ቁሳቁሶች በማካራሬ ዩኒቨርሲቲ የተፈበረከ ነው። ሙሴቬኒ ጥቂት ቆይተው በኮሎሎ የአውሮፕላን መንደርደሪያ ወደሚገኙ ደጋፊዎቻቸው አምርተው ባደረጉት ንግግር የካምፓላ ነጋዴዎች የገጠማቸውን የአቅርቦት ችግር አንስተው ንግግር አድርገዋል። ሙሴቬኒ በምርጫው ወቅትም ይሁን ከምርጫው በኋላ በአገራቸው ሰላም እንደሚሰፍን ለደጋፊዎቻቸው አስረግጠው ተናግረዋል።
«ይህንን ልደግመው እፈልጋለሁ። ማንም ሊያስፈራራችሁ አይገባም። ብጥብጥ ለመፍጠር በሚሞክሩት ላይ ምን ዓይነት እርምጃ እንደምንወስድባቸው ታያላችሁ። ብጥብጥ ከፈለጉ ዩጋንዳን ጥለው ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ይኖርባቸዋል።»
ሙሴቬኒ በምረጡኝ ዘመቻቸው በመላ አገሪቱ ስለ ልማት እና በቤተሰብ ደረጃ ያስፈልጋል ስላሉት ብልጽግና በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
«የ'ናሽናል ሬዚዝተንስ ሙቭመንት' 'ናሽናል ሬዚዝተንስ ሙቭመንት' መልዕክት አንድነት ጥንካሬ፤ጥንካሬ ደግሞ ሰላም ያመጣል። ሰላም ካለ እድገት እና ሃብት ይፈጥራል። የስራ እድል ይፈጠራል። ስራ ለማግኘት ግን ክህሎት ያስፈልጋል። ለዚህም የቴክኒክ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር እናሳድጋለን።»
በዚህ ምርጫ የሙሴቬኒ ጠንካራ ተቀናቃኝ የሆኑት የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ምክክር መድረክ ተወካይ ኪዛ ቤሲጄ በመላ አገሪቱ እየተዘዋወሩ የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን አካሂደዋል። የቅስቀሳው አስተባባሪዎች ከፖሊስ ጋር በመተባበር ከጦር ሰራዊቱ ሳይገናኙ ዘመቻውን ለማካሄድ የሚያስችሏቸውን እቅድ ነድፈዋል። ኪዛ ቤሲጄየምረጡኝ ቅስቀሳ ባደረጉባቸው ቦታዎች ሁሉ ህዝቡ እንዲመርጣቸው ብሎም ድምጹን እንዲጠብቅ ወትውተዋል። ቤሲጄ የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ባድሩ ኪጉንዱ ወገንተኛ መሆናቸውን ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
«ፕሮፌሰር ኪጉንዱ እና የምርጫ ኮሚሽኑ ቃል-አቀባይ የተቃዋሚ እጩዎችን ያለ አግባብ በመተቸት በስልጣን ላይ ላለው መንግስት ያላቸውን ወገንተኝነት በተደጋጋሚ አሳይተዋል። ፕሮፌሰር ኪጉንዱ በቴሌቭዥን እኔን ከእጩነት ከመመረጥ ያሚያግዱበት መንገድ ቢኖር ኖሮ ያደርጉት ነበር ሲሉ ተናግረዋል። ይህ በዩጋናዳውያን እምነት ተጥሎበት ምርጫ ሊያከናውን ኃላፊነት ከተሰጠው ተቋም ሊቀ-መንበር መደመጡ በጣም ያስቆጫል።»
የሙሴቬኒ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አማማ ምባባዚ ሶስት የምረጡኝ ዘመቻዎች የነበሯቸው ሲሆን የመጨረሻው የተካሄደው በማካራሬ ዩኒቨርሲቲ ነበር። ምባባዚ ምርጫውን ካሸነፉ በፕሬዝዳንትነት አምስት አመታት ብቻ እንደሚቆዩ እና ስልጣናቸውን ለወጣቶች እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል።
የአገር ውስጥ ታዛቢዎች የአገሪቱ ፖሊስ የመብት ጥሰት ስለመፈጸሙ እና እጩ ተወዳዳሪዎች ድምጽ ሰጪዎችን በገንዘብ ስለ መደለላቸው የሚያሳይ ማስረጃ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የሲቲዝንስ ምርጫ ታዛቢዎች ኔትወርክ አባል የሆኑት ሊቪንግስተን ሴዋንያና አስፈላጊ ከሆነ ማስረጃውን ለፍርድ ቤት ለማቅረብ እንደሚችል ይናገራሉ።
«ህጉን የሚጥስ ማንኛውም ሰው ተጠያቂ ነው። እንደ ታዛቢ በምርጫው ላይ አለመግባባቶች ከተፈጠሩ በእጃችን የሚገኙትን የመብት ጥሰቶችን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ከመጠቀም አናመነታም። ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ለሚፈልግ ማንኛውም አካል የተሰነዱ ማስረጃዎች ለማቅረብ ዝግጁ ነን።»
የቀድሞው የታንዜኒያ ፕሬዝዳንት ሓሳን ምዊኒ እና የናይጄሪያው ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከዩጋንዳ ምርጫ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች መካከል ይገኙበታል።
አሌክስ ጊታ /እሸቴ በቀለ
ሒሩት መለሰ

Uganda Wahlen 2016
ምስል Simone Schlindwein
Uganda Protest der Opposition
ምስል Reuters/J. Akena