1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የያሕያ ጃሜሕ ዘረፋ እና ፍትኅ የጠማት ጋምቢያ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 12 2011

ጋምቢያ የቀድሞ መሪዋ ያሕያ ጃሜሕ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የተመዘበረው የገንዘብ መጠን እና የተፈጸመው በደል መንግሥት ባቋቋመው የዕርቅ እና እውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ይፋ እየሆነ ነው። የዛሬዎቹ ሹማምንት በጃሜሕ ዘመን ሥልጣን ላይ የነበሩ በመሆናቸው ዜጎች እምነት አጥተዋል።

https://p.dw.com/p/3H6Li
Gambia Yahya Jammeh
ምስል picture alliance/AP Photo

በጋምቢያ በተደረገ ምርመራ በጃሜሕ ዘመን 975 ሚሊዮን ዶላር ተመዝብሯል

ከአንድ ፕሬዝዳንት ቤተ-መንግሥት ጋራዥ ምን ሊገኝ ይችላል? በሌሎች ዜጎች መኖሪያ ቤቶች የማይገኙ ቁሳቆሶች መኖራቸው አይጠረጠርም። የቀድሞው የጋምቢያ ፕሬዝዳንት ያሕያ ጃሜሕ በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. በምርጫ ተሸንፈው ከአገራቸው ሲሸሹ ቅንጡ ተሽከርካሪዎቻቸው ግን ከጋራዣቸው ቀርተዋል። ቅንጡዎቹ ቤንትሌይ እና ሮልስ ሮይስ በዚያ ይገኛሉ። መኪኖቹ የሚያሽከረክራቸው ባይኖርም በየሁለት ቀኑ ይወለወላሉ። እነዚህ ቅንጡ ተሽከርካሪዎች ጋምቢያን ከሁለት ዐሥርተ-ዓመታት በላይ ያስተዳደረው መንግሥት ቅሪቶች ናቸው። ጃሜሕ ይኸን ሁሉ ሐብት ሲያግበሰብሱ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ለዜጎቿ መሰረታዊ ግልጋሎቶች እንኳ የማቅረብ አቅም አልነበራትም።

ጃሜሕ በመሯት አገር የከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈጸም ነበር የሚል ውንጀላ ይደመጣል። ያሕያ ጃሜሕ ሥልጣን ላይ በነበሩባቸው ዓመታት የተወሰኑ ተቃዋሚዎቻቸው ተገድለዋል፤ አሊያም ደብዛቸው ጠፍቷል።

ጃሜሕ ከሥልጣናቸው ወርደው ከአገራቸው ቢሸሹም እርሳቸው እና ባልደረቦቻቸው በመዘበሩት ገንዘብ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆነዋል። የጋምቢያ ዜጎች ተቆጥተዋል፤ ለድርጊቱም ፍትኅ ይሻሉ።

አንዲት ጋምቢያዊት  “ለጋምቢያ ዜጎች ዘለፋ ነው። በሙስና ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች የሚገባቸውን ዋጋ እንዲከፍሉ እንፈልጋለን። በትክክለኛው መንገድ ለፍትኅ ቀርበው ሕግ ይዳኛቸው” ስትል ተናግራለች።

Gambia Luxusautos des Ex-Präsidenten Yahya Jammeh
የያሕያ ጃሜሕ ቅንጡ ተሽከርካሪ ግልጋሎት ባይሰጥም በየሁለት ቀኑ ይወለወላልምስል DW/F. Facsar

ለመሆኑ ምን ያኽል ገንዘብ ተመዝብሯል? በተደራጁ ወንጀሎች እና ሙስና ምርመራ ፕሮጀክት መሰረት ጃሜሕ እና ግብረ አበሮቻቸው ከመንግሥት ካዝና 975 ሚሊዮን ዶላር ዘርፈዋል። የጋምቢያ የፍትኅ ሚኒስቴር እንደሚለው ግን የተዘረፈው ገንዘብ 304 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው። ጋዜጠኛ ሙስጠፋ ዳርቦ ግን የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚሉትን መቀበል ይቸግረዋል።

 “ከመንግሥት ይልቅ የምርመራ ፕሮጀክቱ ላይ የበለጠ እምነት አለኝ። ምክንያቱም መንግሥት ራሱን ሊቆጣጠር አይችልም” ይላል ሙስጠፋ ዳርቦ ፈርጠም ብሎ።

ጋዜጠኛው አሁን በሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት ላይ የበረታ ጥርጣሬ አለው። አገሪቱ በየትኛው አቅጣጫ እየነጎደች እንደሆነም ግራ ገብቶታል።

 “በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. ይኽቺን አገር ለመለወጥ ያገኘነውን ታላቅ ዕድል ሳንጠቀምበት አልፏል። ያለፈውን መለወጥ አልቻልንም። አሁንም እንደ አገር ወዴት እየተጓዝን እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም። ይኸ ደግሞ አደገኛ ነው” የሚለው ሙስጠፋ ዳርቦ ድምፁ ውስጥ ቁጭት ይነበባል።

በ1994 ዓ.ም. በተካሔደ መፈንቅለ-መንግሥት ሥልጣን የጨበጡት ጃሜሕ በአገራቸው የሰብአዊ መብት ጥሰት ከፍቷል፤ ሙስናም በርትቷል የሚል ወቀሳ በበረታባቸው ዓመታት እርሳቸው ግን በዓለም አቀፍ መድረክ 'እንኳን ደህና መጡ' የሚባሉ እንግዳ ነበሩ።

በምርጫ ተሸንፈው እንኳ ተተኪያቸው የዛሬው ፕሬዝዳንት አዳማ ባሮው ሥልጣን እንዳይጨብጡ ያልተሳካ ሙከራ ያደረጉት ጃሜሕ ወደ ኤኳቶሪያል ጊኒ የተሰደዱት በጎርጎሮሳዊው 2017 ነበር። ሰውየው በእቃ መጫኛ አውሮፕላን ሲሸሹ ዕዳ ካጎበጣት አገራቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ይዘው ሔደዋል የሚል ጭምጭምታ ይደመጣል።

USA-Afrika-Gipfel in Washington
ምስል reuters

የጃሜሕ መኖሪያ ቤቶች ተበርብረዋል። ከባንጁል አቅራቢያ የመቃብር ሥፍራ ሳይሆን አይቀርም በተባለ ቦታ ምርመራ እየተደረገ ይገኛል።

ጃሜሕ አገር እና ሥልጣን ለቀዋል፤ አብዛኞቹ ግብረ-አበሮቻቸው ግን በነበሩበት እንዳሉ ናቸው። ሞሞዱ ሳባሊ በጃሜሕ መንግሥት በምኒስትርነት አገልግለዋል።

ሞሞዱ ሳባሊ “ጋምቢያ ትንሽ አገር ነች፤ ሕዝቧም ትንሽ ቢሆንም ውስብስብ ነች። ለሁሉም ችግሮች መፍትኄ መፈለጉ ጥረት እንዲህ ቀላል አይሆንም” ሲሉ የአገራቸውን ፈተና ይገልጹታል።

የጋምቢያ ጥሪት ስለመዘረፉ አውቃለሁ የሚሉት ሳባሊ ራሳቸውን ግን ከደሙ ንጹህ ያደርጋሉ። ስለ ቀድሞ መሪያቸው ጃሜሕ ግን ምን ይላሉ?  “ጃሜሕ የመመለስ እድል አላቸው። መቼ እና እንዴት እንደሚመለሱ ግን አላውቅም። ፓርቲያቸው ዛሬም ከፍተኛ ተቀባይነት አለው። እርሳቸውም በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ታዋቂ ናቸው”  ሲሉ ሞሞዱ ሳባሊ ተናግረዋል።

ጋምቢያውያን ጃሜሕ አገር ጥለው ከሸሹ ጀምሮ አዲስ የነፃነት አየር ተንፍሰዋል። ይሁንና በርካታ የቀድሞ ባለሥልጣኖቻቸው በአዲሱ መንግሥት ተመልሰው ወንበር አግኝተዋል። አገሪቱም በባለፈው መንግሥት ለተፈጸሙ ጥፋቶች ዛሬም ፍትኅ ትጠብቃለች።

ቤኒታ ፋን አይሰን/እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ